Monday, 05 January 2015 08:46

ኢንተር ኮንቲኔንታል - በአፍሪካ የመጀመሪያው ተሽከርካሪ ካፌና ሬስቶራንት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ለሰራተኞቹ ከ40 በመቶ በላይ የደሞዝ ጭማሪ አደረገ
     በዓይነ ኅሊና ጥቂት ወደፊት ልውሰዳችሁ 6 ወራት ያህል፡፡ ከጓደኛዎ፣ ከባለቤትዎ፣ ከፍቅረኛዎ ወይም ከስራ ባልደረባዎ ጋር ሆነው ካዛንቺስ እምብርት 15ኛ ፎቅ አናት ላይ በሚገኘው ካፌና ሬስቶራንት አዲስ አበባ ከተማን 360 ዲግሪ ዙሪያ ገባዋን እየቃኙ እየበሉ፣ እየጠጡ … እየተዝናኑ እየተደሰቱና እየተጫወቱ፣ … ነው፡፡
በደራው ጨዋታ መሃል “መጣሁ” ብለው ተነስተው መታጠቢያ ወይም መጸዳጃ ቤት ደርሰው ሲመለሱ የነበሩበት ጠረጴዛና አብረዎት የነበሩትን ሰው ትተው በሄዱበት ስፍራ አጡ፡፡ “ምን ጉድ ነው? “ተሳስቼ ወደ ሌላ ጠረጴዛ ሄድኩ‘ዴ” ብለው ትንሽ ደንገጥ አሉና አካባቢውን መቃኘት ያዙ፡፡ ከነበሩበት ስፍራ ትንሽ ፈቀቅ ብሎ ወዳጅዎ መመለስዎን አይተው ፈገግ ሲሉ፣ ድንጋጤው ጠፋና ወደ ስፍራው አመሩ፡፡
የነበሩበት ስፍራ የጠፋዎት ሬስቶራንቱ በዝግታ ስለሚሽከረከር ነው፡፡ “እንዴት ሕንፃ ይሽከረከራል?” በማለት ሊገረሙ ይችላሉ፡፡ የሚሽከረከረው መላው ሕንፃ ሳይሆን ሰገነቱ መጨረሻ ላይ ያለው ባርና ሬስቶራንት ብቻ ነው፡፡ ይህ አዲስ አበባ ከተማን ቀንም ሆነ ምሽት 360 ዲግሪ በማየት የሚዝናኑበትና የሚደሰቱበት ቴክኖሎጂ፣ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የመጀመሪያው ነው፡፡ ይህ አስገራሚና አስደናቂ ትዕይንት የሚቀርበው የት ነው? በማለት ማወቅ እንደምትፈልጉ እገምታለሁ፡፡
ትዕይንቱ ያለው ባለፈው ረቡዕ በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን 2014 ዓመት፣ ከአፍሪካ ምርጥ 10 ሆቴሎች (Top 10) አንዱ ሆኖ ባለፈው ሳምንት World Luxury Hotel Award በተሸለመው ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ነው፡፡
ይህ ተሽከርካሪ ካፌና ሬስቶራንት የኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል የማስፋፊያ ውጤት ነው ያሉት የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪጅ አቶ ዜናዊ መስፍን፣ ግንባታው ከመቶ 90 የተጠናቀቀ ስለሆነ በሚቀጥሉት 4 እና 5 ወራት እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል፡፡
ማስፋፊያው 500 ሚሊዮን ብር (ግማሽ ቢሊዮን ብር) መፍጀቱን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ 1,500 ሰዎች የሚይዝ ትልቅ አዳራሽ፣ 200 ሰዎች የመያዝ አቅም ያላቸው አራት አነስ ያሉ አዳራሾች፣ ከ400 እስከ 500 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል ሬስቶራንት፣. 200 መኪኖች መያዝ የሚችል ሁለት ፎቅ የመኪና ማቆሚያ፣  እጅግ ዘመናዊ የሆኑ 80 ሆቴል አፓርትመንት ክፍሎች፣ የተለያዩ ሱቆች፣ … እንዳሉት ገልፀዋል፡
በአሜሪካ - በዋሽንግተን ዲሲ ስካይ ዶም፣ በአትላንታ ዌስቲን ሆቴል (westin), በሂልተን ሆቴል ስር Double Tree Hotel ተሽከርካሪ ሬስቶራንት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ዜናዊ፤ እነዚህን ሆቴሎች ለመጎብኘት በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ወደ ስፍራው እንደሚጓዙ ገልፀዋል፡፡
አቶ ዜናዊ፣ እነዚያ ተሽከርካሪ ሬስቶራንት ያላቸው ሆቴሎች በየዓመቱ ከጎብኚዎቻቸው ብዙ ሚሊዮኖች ዶላር እንደሚያፍሱ ጠቅሰው፣ ሆቴላቸው ከዓለም አቀፍ ሆቴሎች ጋር ተወዳድሮ ማሸነፍ መቻሉ በመላው ዓለም እየናኘ ስለሆነ “ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟሉ ሆቴሎች የላትም” ለሚለው ምላሽ ከመስጠቱም በላይ ተሽከርካሪ ሬስቶራንቱን ለመጎብኘት ከሚመጡ በርካታ ቁጥር ካላቸው ኢትዮጵያውያንና የውጭ ቱሪስቶች፣ የቢዝነስ ሰዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ … ዳጎስ ያለ  ገቢ በመሰብሰብ ታሪክ እንደምንሰራ ፅኑ እምነት አለኝ ብለዋል፡፡ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ተሽከርካሪ ሬስቶራንት መስራታችና በዓለም ታዋቂ ከሆኑ 10 ሆቴሎች አንዱ መሆን፣ የአገሪቷን ገጽታ ከመንገባት አኳያ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አቶ ዜናዊ ገልጸዋል፡፡ ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሽልማት የበቃው ለመታወቅ ብሎ ተንቀሳቅሶ ሳይሆን የዘወትር ተግባሩን እያከናወነ ነው፡፡
ሴኩሪቲው፣ ወደሆቴላቸው የመጡት እንግዶች እነሱን ለመገምገም መምጣታቸውን በፍፁም አያውቅም፡፡ የአንደኛው ገምጋሚ ጃኬት ቆሻሻ ነክቶት ነበር፡፡ ጃኬቱ ቆሻሻ እንደነካው ነግሮት ለማፅዳት እንዲሰጠው በትህትና ጠየቀው፡፡ እንግዳውም ጃኬቱን አውልቆ ሰጠው በአጭር ጊዜ ላውንደሪ ወስዶ ቆሻሻውን አስለቅቆ አምጥቶ ሰጠው፡፡    
ወደ ውስጥ ሲገቡ የተቀበሏቸው ሰራተኞች ያሳዩዋቸው ፈገግታና የአክብሮት አቀባበል፣ በሻይ  ቡና መስተንግዶ ወቅት ያደረጉት መስተንግዶ ማረካቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ክፍላቸው ከገቡ ከ15 ደቂቃ በኋላ ደውለው፣ ሆቴሉን እንዴት እንዳገኙት፣ የተስማማቸው መሆኑንና የሚፈልጉት የጎደለ ነገር እንዳለ ጠየቁ፡፡ አንደኛው ገምጋሚ ያስመዘገበውን የልደት ቀን አስታውሰው፣ አራት ሴቶች Happy Birthday በማለት ሰርፕራይዝ አደረጉት፡፡ በእነዚህና በሌሎችም መስተንግዷቸው እጅግ መርካታቸውን በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደነገሯቸው አቶ ዜናዊ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዜናዊ መስፍን በ1997 (እ.ኤ.አ) ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከሃንጋሪ ቡዳፔስት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳይንስ ያገኙ ሲሆን የመጀመሪ ዲግሪያቸውን በ1992 ከዚያው አገር በሆቴል ምግብ ዝግጅትና በቱሪዝም ማኔጅመንት አግኝተዋል፡፡
ከሰሩባቸው 17 ዓመታት 8ቱን ዓመት ያሳለፉት የከፍተኛ ሆቴሎች ሥራ አስኪያጅ ሆነው ነው፡፡ ኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል፤ ሂልተን (ጋርደን ኢን)፣ ሂልተን ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሂልተን ዋሽንግተን ፕላዛ፣ በሥራ አስኪያጅነት ከሰሩባቸው ትላልቅ ሆቴሎች ጥቂቱ ናቸው፡፡

Read 3236 times