Monday, 05 January 2015 08:44

ለውስጥ ደዌ ችግሮች ቁልፍ ምልክት - ሰውነት ማሳከክ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(17 votes)

ማሳከክ ካንሰርን ጨምሮ ለጉበት፣ ለኩላሊትና ለደም መርጋት ችግሮች ቁልፍ ምልክት ነው

       በአርባዎቹ መጨረሻ የዕድሜ ክልል ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ አብሮአት በዘለቀው የስኳር ህመሟ ሳቢያ ሁለቱም ኩላሊቶቿ ከጥቅም ውጪ ሆነው የኩላሊት እጥበት ህክምና (ዳይላሲስ) ማድረግ ከጀመረች አስር ወራት አልፈዋታል፡፡ በሳምንት ለሁለት ቀናት እየሄደች ዳይላሲስ በምታደርግበት የቤቴል ሆስፒታል ውስጥ አግኝቼ ኩላሊቶቿ እዚህ ደረጃ ላይ እስከሚደርሱ ድረስ ህክምና ልታደርግ ያልቻለችበትን ምክንያት ጠየቅኋት፡፡
 ምላሿ  ሀዘንና ፀፀት የተሞላበት ነበር፡፡ በስኳር ህመምተኛነቷ ምክንያት ከህክምና ተቋማትና ከሃኪሞች የራቀ ህይወት አልነበራትም፡፡ በየጊዜው የህክምና ክትትል የሚያደርጉላት ሃኪሞች የጤንነቷ ሁኔታ አሳሳቢ ከሚባል ደረጃ ላይ አለመድረሱንና ስኳሯን በአግባቡ እየተከታተለች ሰላማዊ ህይወቷን መቀጠል እንደምትችል እየነገሩ ይመልሷት ነበር፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ግን መላው ሰውነቷን እያሳከከ፣ ቀንና ሌሊት እረፍት የሚነሳ የጤና ችግር ገጠማት፡፡ በተለይ እጇንና ውስጥ እግሯን እያቃጠለ የሚያሳክካት ነገር እጅግ አሳሰባት፡፡ ወትሮ ህክምናዋን ታደርግት የነበረውን ተቋም ትታ ወደ ቆዳ ሃኪሞች ዘንድ ሄደች፡፡
ሃኪሞቹ ተደጋጋሚ ምርመራ ቢያደርጉላትም ይሄ ነው ብለው ስም የሚሰጡት የቆዳ በሽታ ሊያገኙባት አልቻሉም፡፡ የሰውነት ማሳከክ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል፣ ማሳከክ በራሱ በሽታ አለመሆኑን ነገር ግን ለሌሎች የውስጥ ደዌ ችግሮች መገለጫ ምልክት ሊሆን እንደሚችል ነግረው፣ ምርመራና ክትትል እንድታደርግ በመምከር አሰናበቷት፡፡
በዚህ ምክንያትም በውስጥ ደዌ ህክምና ጥሩ ስም ወዳለው አንድ የጤና ተቋም ሄዳ ሙሉ ምርመራ አደረገች፡፡ ምርመራ ያደረጉላት ሃኪሞች ሁለቱም ኩላሊቶቿ ስር የሰደደ የጤና እክል እንደገጠማቸውና ሁለቱም ስራቸውን ሙሉ በሙሉ ለማቆም ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሯቸው መሆኑን አረዷት፡፡ ኩላሊቶቿን በህክምና እርዳታ ወደነበሩበት ለመመለስ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውንና ያላት ብቸኛ አማራጭም የኩላሊት እጥበት ህክምና መጀመር መሆኑንም ነገሯት፡፡ እውነታው እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡
ችግሩ በድንገትና በአጋጣሚ የደረሰ ሊሆን እንደማይችልና የስኳር በሽታዋ በኩላሊቶቿ ላይ ያስከተለው ሂደታዊ ለውጥ ለዚህ እንዳደረሳትም አልደበቋትም፡፡ በህክምና ክትትል ሰበብ እድሜ ልኳን ስትመላለስባቸው የነበሩት የጤና ተቋማት፣ ስለኩላሊቶቿ ችግር ቀደም ያለ መረጃ ሰጥተዋት ቢሆንና ችግሩ በጊዜው ቢደረስበት ኖሮ ለዚህ ሳትበቃም ችግሯ መፍትሔ ሊያገኘ እንደሚችልም ነገሯት፤ ግን ምን ዋጋ አለው ጊዜው ረፍዷል፡፡ እናም የኩላሊት እጥበት ህክምናዋን ከመጀመር ውጪ አማራጭ  አልነበራትም፡፡
ለሰውነት ማሳከክ ችግሯ መፍትሔ ፍለጋ የሄደችው ትዕግስት፤ ዕድሜ ዘመኗን በሙሉ ተከትት ለሚዘልቅ ስር የሰደደ የጤና ችግር ተጋለጠች፡፡ ላለፉት አስር ወራትም በሳምንት ለሁለት ቀናት የኩላሊት እጥበት ህክምና እያደረገች ሕይወቷን ለማቆየት ተገድዳለች፡፡
የሰውነት ማሳከክ በተለያዩ የቆዳ በሽታዎች ሳቢያ ሊከሰት የሚችል ቢሆንም ስር ሰደድ ለሆኑና በቀላሉ ሊድኑ ለማይችሉ የውስጥ ደዌዎችም መገለጫ ምልክት ይሆናል፡፡
 የቆዳ (የሰውነት) ማሳከክ ችግሮችን ያለ ላብራቶሪ ምርመራ ምንነታቸውን ማወቅና በዚህ መነሻነት የተከሰቱ ችግሮች ናቸው ብሎ መደምደም እንደማይቻል የሚናገሩት የቆዳና የአባላዘር በሽታዎች ስፔሻሊስቱ ዶክተር ቴዎድሮስ ገዛኸኝ፤ ችግሩ በውጫዊና በሰውነታችን ውስጣዊ ችግሮች ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የሰውነት ማሳከክን ከሚያስከትሉ ውጫዊ ችግሮች መካከል ላብ፣ የቆዳ ድርቀት፣ በትንኞች መነደፍ፣ የሰውነታችን ቆዳ ከኬሚካልና መሰል ነገሮች ጋር ንኪኪ በሚያደርግበት ጊዜ የሚከሰቱ ችግሮች፣ አለርጂዎች ማለትም የምግብ፣ የመድኀኒት፣ የአልባሳትና መሰል ነገሮች አለርጂዎች፣ ኢንፌክሽኖች (በባክቴሪያ፣ በፈንገስና በፓራሳይት የሚከሰቱ)  የቆዳ በሽታዎችና ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የሰውነት ማሳከክ ከሚከሰትባቸው ውስጣዊ ችግሮች መካከል የተለያዩ የካንሰር ህመሞች፡- (የጉበት፣ የማህፀን፣ የሆድ ዕቃ፣ የአንጎል፣ የጡንቻና የደም ካንሰሮች)፣ የደም መርጋት፣ የሃሞት ከረጢት ችግር፣ የኩላሊት መድከም፣ የስኳር በሽታ፣ ሄፒታተስ ቢ እና ሲ፣ ሪህና የአይረን ንጥረ ነገር እጥረት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ማንኛውም ሰው ለቀናት የዘለቀና እረፍት የሚያሳጣ አይነት የሰውነት ማሳከክ ችግር ሲገጥመው ጉዳዩን በቸልታ እንዳያልፈውና በባለሙያ የታገዘ ምርመራና የምክር አገልግሎት ማግኘት እንደሚገባው ዶክተሩ አስገንዝበዋል፡፡
 በውስጥ ህመም ሳቢያ የሚከሰቱ የቆዳ ማሳከክ ችግሮች ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፉ ናቸው ያሉት ዶክተሩ፤ ህመምተኛውን ሰው ግን ፍፁም እረፍት አልባ የሚያደርጉና የማቃጠል ስሜትንም የሚያስከትሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዓለማችን ከሶስት ሺህ የሚበልጡ የቆዳ በሽታዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶክተር ቴዎድሮስ፤ በአገራችን በብዛት የሚታዩት ሰውነት በሽታን የመከላከል አቅሙ በተለያዩ ምክንያቶች በሚደክምበት ጊዜ የሚመጡ የቆዳ በሽታዎች መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
 ሽታና ቀለም ባላቸው የመፀዳጃ ወረቀቶች መጠቀም፣ ብልትና ፊንጢጣ አካባቢ ለሚከሰቱ የቆዳ ህመሞችና ማሳከክ እንደሚያጋልጥም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ሰውነት ማሳከክ በራሱ በሽታ አለመሆኑን፣ ነገር ግን እጅግ ለተወሳሰበና ጠንከር ላለ የጤና ችግር መገለጫ ሊሆን ስለሚችል እንዲህ አይነት ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ ቸል ሳንል ልንከታተለውና በወቅቱ ተገቢውን ሕክምና ልናገኝ የምንችልበትን መንገድ መፈለግ እንደሚገባን ዶክተር ቴዎድሮስ አበክረው አስገንዝበዋል፡፡


Read 19698 times