Monday, 05 January 2015 08:06

“እንደ አባይ ግድብ ልጆቻችንን እንገድብ” (አንዲት እናት)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(17 votes)

የግብጽን ነገር በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ብቻ አንወጣውም!

    በሳምንቱ አጋማሽ ላይ አንድ ወዳጄ የነገረኝ ቀልድ ፈረንጆቹ Bitter (መራራ ቀልድ) የሚሉት ዓይነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ፈርዶብን መራራ ቀልዶች ይቀሩናል (ያልተኖረ እኮ አይቀለድም!) ለማንኛውም ቀልዱን ከመራራ ወይም ከጣፋጭ የመመደቡን ሃላፊነት ለእናንተ ትቼ በቀጥታ ወደ ቀልዱ ልግባ፡፡ (ኮፒራይቱ  የህዝብ መሆኑን እንዳትዘነጉ!)
“ኢሳያስ አፈወርቂ፤ 8100 ልኮ ምን እንደደረሰው ታውቃለህ?” አለኝ ወዳጄ - በሞባይል ስልኬ ደውሎ፡፡ (ፕሬዚዳንትም እንደ አርቲስት “አንተ” ይባል ጀመረ እንዴ!)
“ ኧረ አላውቅም …” አልኩት- ግራ በተጋባ ስሜት፡፡ (ከምሬ ነበር!)
“ ሄሊኮፕተር ከእነ አብራሪዎቹ!!” አለኝና ሳቄን ተጋራኝ፡፡
ይሄው ወዳጄ እንደነገረኝ፤ ቀልዱ “የፌስቡክ የዓመቱ ምርጥ ቀልድ” ተብሏል፡፡ (እንግዲህ Bitter ቢሆንም ተደንቋል ማለት ነው!) ወደ ቁምነገሩ ስንመጣ … ሀበሻ እንግዲህ መቼም ቢሆን በራሱ ከመቀለድ ቦዝኖ አያቅም፡፡
(የቀልድ ተሰጥኦ ከተቸራቸው ጥቂት ህዝቦች አንዱ ሳንሆን አንቀርም!) ለዚህ እኮ ነው የአገራችን ኮሜዲያን በሙያቸው ልቀው መውጣት ያቃታቸው (መሪም ተመሪም ኮሜዲያን ሊሆኑ የሚችሉባት ብቸኛ አገር ጦቢያ ናት!) የሚገርመው ግን ምን መሰላችሁ? ወዲ አፈወርቂ ይሄን የሚያህል ዕጣ አሸንፈውም አልደነቃቸውም፡፡(አልበረዳቸው አልሞቃቸው!) ምናልባት እርጅና ተጫጭኗቸው ሊሆን ይችላል፡፡
(የዕድሜ ብቻ ሳይሆን የሥልጣን እርጅናም ይጫጫናል!) በነገራችን ላይ --- አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች የዕድሜና የሥልጣን እርጅና (መጫጫን) ሰለባዎች ናቸው፡፡ በህይወት ካሉት እነ ሙጋቤ፣ በህይወት ከሌሉት ደግሞ እነ ጋዳፊ ይጠቀሳሉ፡፡  
 እኔ የምለው ግን --- የሄሊኮፕተሯን ጉዳይ በተመለከተ እነ ቢቢሲና ሮይተርስ እንዴት ሳይዘግቡ ቀሩ? (የኒዮሊበራል ነገር ይሄው እኮ ነው!) እንዲያም ሆኖ --- አስመራ ገብታለች የተባለችውን ሄሊኮፕተር በተመለከተ ውስጤ ጥርጣሬ ማደሩ አልቀረም፡፡ እስካሁን ከወደ አስመራ ምንም የተሰማ ወሬ እኮ የለም፡፡ በቃ ዝም ጭጭ ነው፡፡ እናላችሁ ---- “ሄሊኮፕተሯ አስመራ አላረፈች እንደሆነስ?” ማለት ሁሉ ጀምሬአለሁ፡፡ (የመረጃ ድርቀት ውጤት ነው!) በነገራችን ላይ የአውሮፕላን ዘር በወጣበት መቅረት መጀመሩንም መዘንጋት የለብንም፡፡ የማሌይዢያ የመንገደኞች አውሮፕላን እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ፣ የኢንዶኔዥያ አውሮፕላንም ተደገመ አይደል? (ቢያንስ የአሁኑ ጠፍቶ አልቀረም!) ሰሞኑን የሰማሁትን ሌላ ቀልድ ደግሞ እነሆ፡፡ ይሄኛውም ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ (አይዟችሁ በ“ፀረ-ልማት”ነት አያስፈርጅም!) እናላችሁ---አንዱን የሸገር ወጣት አንድ ፍሬሽ ካድሬ አላስቆም አላስቀምጥ ይለዋል -- ለህዳሴው ግድብ በቂ ድጋፍ አላደረግህም በሚል፡፡  ወጣቱ ውትወታው ትክት ሲለው፤ “ድርሻዬን  ስጡኝና … ራሴ እገድበዋለሁ” ብሎት እርፍ አለ፡፡ (ማሳመንና ማታከት ለየቅል ናቸው!)
ባለፈው ረቡዕ ምሽት EBC በድሬዳዋ ወላጅ አልባ ህጻናትን ከማሳደጊያ ተቋም (ጉዲፈቻ) በመውሰድ ከልጆቻቸው ጋር በሚያሳድጉ ቤተሰቦች ዙሪያ አንድ ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡ የጉዲፈቻ ህፃን ከወሰዱ የከተማዋ ነዋሪዎች አንዷ አስተያየት ሲሰጡ ምን አሉ መሰላችሁ? “እንደ አባይ ልጆቻችንን እንገድብ… ወደ ስደት…. ወደ ባዕድ  አገር እንዳይሄዱ!” ግሩም አባባል አይደል! ሴትየዋ ከተናገሩት ተነስቼ እኔ ደግሞ እንዲህ እላለሁ፤ “ልክ ለአባይ ግድብ እንደምናደርገው ሁሉ  ወላጅ አልባ ህፃናትን ለማሳደግና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር የቦንድ ግዢ ቢዘጋጅስ?” (ዜጐች ካልተገደቡ የስደት ባህር ያሰጥማቸዋል!!)በነገራችን ላይ ግብፅ ደርሶ የተመለሰው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አንዳንድ አባላት እንደነገሩኝ፤ አባይ ከኢትዮጵያ እንደሚነሳ የማያውቁ ግብጻውያን አሉ (ለእነዚህ አይነቶቹ ከዲፕሎማሲ በፊት ትምህርት ነው የሚያስፈልገው!) ይሄ የሚያመለክተው የአባይን ግድብ ከመገንባት ያልተናነሰ ብዙ የአመለካከት ግንባታ እንደሚጠብቀን ነው፡፡ እናም---የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የግብጽን ነገር በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ብቻ እንደማንወጣው ተገንዝቦ ---- አዳዲስ የዲፕሎማሲ ዘርፎችን መፍጠር ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ ለምሳሌ  ካልቸራል ዲፕሎማሲ፣ አርት ዲፕሎማሲ፣ ኢጁኬሽናል ዲፕሎማሲ፣ ሪሊጂየስ ዲፕሎማሲ፣ ፉድ ዲፕሎማሲ፣ ሜሬጅ ዲፕሎማሲ --- ወዘተ-- ይጠቀሳሉ፡፡ በደንብ ሲያውቁንና በተለያዩ ዘርፎች ትስስራችን ሲጎለብት ጥርጣሬያቸው እየደበዘዘ፣ እምነታቸው እንደሚፈካ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ መልካም የመውሊድ በዓል! መልካም የገና በዓል!

Read 6672 times