Saturday, 03 January 2015 10:32

“የዘመራ ምሽት” የስነ-ግጥም ፕሮግራም ዛሬ በባህር ዳር ይጀምራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

       በባህር ዳር ከተማ በካስትል ኩሪፍቱ ወይን ሃውስ በየወሩ የሚሰናዳ “የዘመራ ምሽት” የተሰኘ ግጥም ዝግጅት ዛሬ እንደሚጀመር ከፕሮግራሙ መስራቾች አንዱና ስራ አስኪያጁ አቶ ደምስ አያሌው ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በመጀመሪያው “የዘመራ ምሽት” ፕሮግራም ላይ አንጋፋው ፀሀፌ ተውኔትና ገጣሚ ጌትነት እንየው በክብር
እንግድነት እንደሚገኝም አቶ ደምስ አያሌው ተናግረዋል፡፡ በየወሩ ይካሄዳል በተባለውና ዛሬ ማታ በሚጀምረው የስነ-ግጥም ፕሮግራም ላይ በወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን የሚቀርቡት ስራዎች በማሲንቆ፣ በክራርና በዋሽንት የሚታጀቡ ሲሆን እያንዳንዱን ግጥም ተዋንያን ከጀርባ በተውኔት እንደሚያጅቡትም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በየወሩ በሚካሄደው የዘመራ ምሽት ላይ ከግጥም በተጨማሪም መነባንቦች፣ ትውፊታዊ ድራማዎችና ሌሎችም የኪነ-ጥበብ ስራዎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ የዘመራ ምሽት ዋና አላማ የክልሉን ባህልና ትውፊት የበለጠ ማጉላት፣ ማህበረሰቡን እያዝናኑ ማስተማር፣ የገጣሚያን ስራዎች በመፅሀፍና በሲዲ ታትመው አድማጭና አንባቢ እጅ እንዲደርሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና የግጥምን አቀራረብ ከተለመደው አሰራር ወጣ ባለመልኩ በማቅረብ አዝናኝነትና አስተማሪነቱን መጨመር እንደሆነ አቶ ደምስ ገልፀው፤ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ስራዎቻቸውን በካስትል ኩሪፍቱ ዋይን ሃውስ ተገኝተው እንዲያቀርቡ አሊያም ስራዎቻቸውን በመላክ እንዲሳተፉ
ጥሪ ቀርቧል፡፡

Read 1442 times Last modified on Saturday, 03 January 2015 11:05