Print this page
Monday, 29 December 2014 08:26

ፑቲን ለሚኒስትሮቻቸው የአዲስ ዓመት እረፍት የለም አሉ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ሚኒስትሮቻቸው የአዲስ ዓመት እረፍት እንደማይወስዱ ሰሞኑን አስታወቁ፡፡ በሩሲያ ትልቁ በዓል እንደሆነ በሚነገርለት የፈረንጆች አዲስ ዓመት፤ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የሩሲያ ኩባንያ ሰራተኞች ለበዓሉ የ12 ቀናት እረፍት ይወስዳሉ፤ ከጃንዋሪ 1 እስከ 12፡፡
ፑቲን ባለፈው ሐሙስ በቴሌቪዥን በተሰራጨ የመንግስት ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ፣ በዚህ ዓመት የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው እረፍት መውሰድ እንደማይገባቸው ተናግረዋል፡፡ “ቢያንስ ለዚህ ዓመት መንግስት ይሄን ረዥም የበዓል ዕረፍት መስጠት አይችልም - መቼም የምለው ይገባችኋል” ብለዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡
የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በበኩላቸው፤ በበዓሉ ወቅትም ጭምር (ከዓመቱ የመጀመሪያ ቀናት አንስቶ) የኢኮኖሚውን ሁኔታ እንዲከታተሉላቸው እንደሚፈልጉ ለሚኒስትሮቹ ነግረዋቸዋል፡፡
በነዳጅ ዋጋ መቀነስና በምዕራብ አገራት ማዕቀብ ክፉኛ የተጎዳው የሩሲያ ኢኮኖሚ፤ ከስድስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪ ጊዜ በቀጣዩ ዓመት “ድቀት” ውስጥ የሚገባ ሲሆን፣ የአገሪቱ ገንዘብ ሩብልም በአሁኑ ሰዓት ከዋጋው ግማሽ በታች ወርዷል፡፡ ከያዝነው ወር መጀመሪያ አንስቶ አንድ ዶላር በ80 ሩብል ሲመነዘር የቆየ ሲሆን፣ ባለፈው ሐሙስ የ2 በመቶ መጠነኛ መሻሻል አሳይቶ አንድ ዶላር በ52 ሩብል መመንዘሩ ታውቋል፡፡
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ የአገሪቱ መጠባበቂያ ገንዘብ ከ2009 ዓ.ም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ400 ቢሊዮን ዶላር በታች መውረዱን አስታውቋል፡፡ ዋጋው እጅግ ያሽቆለቆለውን የአገሪቱን መገበያያ ሩብል ማረጋጋት፣ የሩሲያ የገንዘብ ኃላፊዎች ተቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሏል፡፡ ከዩክሬን ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ፣ በርካታ የሩሲያ ኩባንያዎችን ከምዕራብ አገራት የፋይናንስ ገበያ እንዳስወጣቸው ተዘግቧል፡፡

Read 2858 times
Administrator

Latest from Administrator