Print this page
Monday, 29 December 2014 08:14

መኪና ሲያሽከረክሩ የተያዙ የሳኡዲ ሴቶች በሽብርተኝነት ሊከሰሱ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መኪና ሲያሽከረክሩ የተያዙ ሁለት የሳኡዲ ሴቶች ለአንድ ወር ገደማ ከታሰሩ በኋላ ባለፈው ሳምንት ጉዳያቸው ሽብርተኝነትን ለሚመለከት ልዩ ፍ/ቤት እንደተላለፈ ተገለፀ፡፡
የ25 ዓመቷ ሎዩጄይን አል ሃትሎል እና የ33 ዓመቷ ማይላ ይሳ አል - አሙዲ ጉዳይ ወደ ልዩ ፍ/ቤት የተላለፈው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጡት አስተያየት ነው ብለዋል - የመብት ተሟጋቾች፡፡ ሳኡዲ በዓለም ላይ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ የምትከለክል ብቸኛ አገር ናት፡፡
ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ በፅሁፍ የተቀመጠ ህግ ባይኖርም የመንጃ ፈቃድ የሚሰጠው ግን ለወንዶች ብቻ ነው፡፡ ሴቶች በአደባባይ ሲያሽከረክሩ ከተገኙም በፖሊስ ተይዘው ከመታሰርም ባሻገር ይቀጣሉ፡፡
የሳኡዲ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ የተጣለባቸው እገዳ እንዲነሳላቸው ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ የተለያዩ ተከታታይ እንቅስቃሴዎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡
አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ ሚስ ሃትሎል የተያዘችው ከጐረቤት አገር፣ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ እያሽከረከረች ወደ ሳኡዲ ለመግባት ስትሞክር ነው፡፡
ነዋሪነቷን በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ያደረገችው የሳኡዲ ጋዜጠኛ ሚስ አላሙዲም የተያዘችው ሚስ ሃትሎልን ለመርዳት ድንበር ላይ ስትደርስ ነው ብሏል - የዜና ወኪሉ፡፡
ሁለቱም ሴቶች በትዊተር እጅግ በርካታ ተከታይ ያሏቸው ሲሆን ሚስት ሃትሎል ወደ አገሪቱ ለመግባት አንድ ቀን ሙሉ ያችውን ውጣ ውረድ በትዊተር ገጿ ላይ እንዳሰፈረች ተዘግቧል፡፡ ባለፈው ሐሙስ በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኘው አል - አህሳ ፍ/ቤት፤ የሁለቱ ሴቶች ጉዳይ በሪያድ የሽብርተኝነት ክሶችን ለመከታተል በተቋቋመው ልዩ ፍ/ቤት እንዲዳኙ በይኗል፡፡ የሴቶቹ ጠበቆች ግን ይግባኝ ለመጠየቅ ማሰባቸውን የመብት ተሟጋቾች ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ጠቁመዋል፡፡

Read 2649 times
Administrator

Latest from Administrator