Monday, 29 December 2014 07:47

“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣‘ወየት’ ነህ!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው አእምሮ ሀኪም ዘንድ ይሄድና…“ዶክተር፣ መጥፎ ተግባራት እየፈጸምኩ ህሊናዬ እየረበሸኝ ነው…” ይለዋል፡፡
ዶክተሩም… “እና መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም የሚከላከል ህክምና እንዳደርግልህ ነው የምትፈልገው?” ይለዋል፡፡ ሰውየውም… “አይደለም…”  ይላል፡፡
ዶክተሩም… “ታዲያ ምን ፈልገህ መጣህ?” ይለዋል፡፡
ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው…“ህሊናዬን ከሥሩ ነቅለህ አውጣልኝ!”
‘አልሰሜን ግባ በለው’ አሉ…እኛ ዘንድ ቢመጣ ህሊና እያለም እንዴት ‘ህሊናቢስ’ መሆን እንደሚቻል ‘በስምንተኛ ዲግሪ’ ደረጃ እናሰለጥነው ነበር፡፡ የምር ግን የህሊና ነገር እኮ እኛ አገር የሆነች ተረስታ ከአሮጌ አንሶላ ጋር የተጠቀለለች ነው የምትመስለው፡፡  
እናላችሁ…“ትንሽ ህሊና እንኳን የለህም!” ብሎ አማረኛ ቀረ፡፡ ህሊና የሰው ስም ብቻ የሚመስለን እየበዛን ነዋ! (“ህሊና ቢኖረኝ እዚህ አገር ታገኙኝ ነበር ወይ…” ያልከን ወዳጃችን በእግርህ አስነካኸው እንዴ!)
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ነገርየው እንዴት ነው…‘ጉልቤ’ ነገሮች በዙብና! ልክ ነዋ…ጉልቤነት ማለት እኮ የግድ ‘አገጭ ማጣመም’፣ ጥርስን ‘በመሀረብ ማስቋጠር’ ምናምን ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የዘንድሮ ‘ጉልቤነት’… አለ አይደል…መአት መልክ አለው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ…የሆነ ሚኒባስ ታክሲ ላይ ያየነው ‘ጥቅስ’ ነው…‘ጥቅሱ’ ምን ይል መሰላችሁ… (ምንም ደስ ባይልም መነገር አለበት፣) “አፍህን ከምትከፍት ሱቅ ክፈት” ይላል፡፡
እናላችሁ…እንዲህ አይነት በህዝብ መገልገያ ላይ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጸጉር ‘ሙልጭ የምንደረግበት ዘመን ላይ ደርሰንላችኋል፡፡ የምር ግን… እንደዚህ አይነት ነገር መጀመሪያ ስናይ ፈገግ እንደ ማለት ይቃጣናል፡፡ ግን… እኛም ተሰዳቢዎች መሆናችን ሲገባን…
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” እንላለን፡፡  
ምን መሰላችሁ…‘የቤትሽን ዓመል እዛው’  ‘አትንጣጪ’ ምናምን ሲባል ዝም ተብሎ ተከረመና አሁን ደግሞ “አፍህን አትክፈት…” ወደ መባል ደርሰናል፡፡
የምር እኮ…ነገርየው በዚሁ ከቀጠለ …ቀስ ብሎ…በአንድ ወቅት እዚች ዋና ከተማችን ጎራ ያለ የገጠሩ ሰውዬ… “አዲስ አበባ ገዳይ ጠፋ እንጂ ሟች ብዙ ነበር!”  ያለበት አይነት ስድብ ነገ ተነገ ወዲያ የማይለጠፍበት ምክንያት የለም፡፡ እነማ…እንደዚህ አይነት ነገር ሲበዛብን፣
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” እንላለን፡፡  
የምር አስቸጋሪ ጊዜ ነው፡ የደንብ ልብስ የለበሱ በከተማው ጎዳናዎች በበዙበት ጊዜ፣ ማስቲካና መፋቂያ ሻጮች ሲሯሯጡ በምናይበት ጊዜ… አንዳንድ አካባቢ ተረጋግቶ መገበያየት እንኳን እያስቸገረ ነው፡፡ እኔ የምለው… እግረ መንገዴን…የገበያተኛ መዋከብ ‘የደንብ ጥሰት’ ለመሆን ያንሳል እንዴ!
በቀደም መርካቶ ዕቃ ቢጤ ለማየት ወጣ ብለን… “አይ መርካቶ!”  ብለን ተመለስን እላችኋለሁ፡፡ የምር እኮ… የምንጣፍ ሱቆች በበዙበት አካባቢ መራመድ እስኪያቅታችሁ ድረስ ትከበባላችሁ፡፡  ‘የደላላው’ ብዛት! የሆነ ሱቅ ውስጥ ለመግባት ስታስቡ ወጣት ደላሎች እየተከተሉ… “መጋዘኑ እዛ’ጋ ነው፣ ቅናሽ አለው…” “እዛ ሱቅ ያለው አሪፍ ነው…” ምናምን እየተባለ እስኪሰለቻችሁ ድረስ የሚቀባበሏችሁ ወጣቶች ብዛታቸው… አለ አይደል… ያበሳጫል ብቻ ሳይሆን ‘ያስፈራል’ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
እንግዲህ ይህ ሁሉ ሲሆን በአካባቢው የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ውር፣ ውር ይታያሉ— የሚያስጥል የለም እንጂ፡፡ እናላችሁ… ገበያተኛ ሲጉላላ፣ ደንብ አስከባሪውም ዝም፣ ነጋዴውም ዝም፣ ሁሉም ዝም ሲሆን… አለ አይደል…
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” እንላለን፡፡  
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚህ አገር መድረክ ላይም ‘ሙልጭ’ ተደርጎ መሰደብ እየተለመደ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰብሳቢው…“መሀላችን የተሰገሰጉ የራሳቸው ዓላማ ያላቸው…” ምናምን እያለ ‘ሆረር’ ምናምን ነገር ይለቅባችኋል፡፡
‘አስተያየት ሰጪው’ ተነስቶ… “በተባለው ላይ የምጨምረው የለኝም…” ይልና  “ዕድገታችንን ለመግታት የሚፍጨረጨሩ አንዳንድ የስብሰባው ተካፋዮች ላይ እርምጃ ለምን እንደማይወሰድ…” በቁጭት ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እከሌ፣ እከሌ ተብሎ እስካልተጠቀሰ ድረስ አንዳንድ “…የስብሰባው ተካፋዮች…” የሚለው ሁላችንንም ስለሚመለከት…አለ አይደል…
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” እንድንል ያደርገናል፡፡
አሀ… ማን በበላው ማን ‘ራዳር’ ውስጥ ይገባል! ልጄ ዘንድሮ ‘…ሁሉም እንደ የሥራው…” ምናምን የሚል አባባል፣ ‘ጥቅስ’…ነገር አይሠራም፡፡ ልጄ…ዘንድሮ ሰው ‘ባልሠራው’ የሚበላበት፣ ‘ባልሠራውም’ የሚበላውን የሚያጣበት ዘመን ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…የመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ…አንዱ ሠራተኛ አካፋ አልነበረውም፡፡ ታዲያ…አለቃውን፣ “አካፋ የለኝም…” ይለዋል፡፡ አለቅየውም…“ታዲያ ምን ያነጫንጭሀል! አካፋ ከሌለህ ሥራ አትሠራ!” ይለዋል፡፡ ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “ታዲያ እንደ ሌሎቹ ሠራተኞች ምን ተደግፌ ልቁም?” ብሎ አረፈላችሁ፡፡
እናማ…በየቢሮው፣ በየሥራ ቦታው ‘አካፋ ተደግፈን’ የምንቆም መአት ነን፡፡
ይቺን አሪፍ ነገር ስሙኝማ…ሰውየው ለጓደኛው ሲደውል ከጀርባ ድምጽ ይሰማል፡፡ “የምን ጫጫታ ነው የምሰማው?” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም… “የእህቴን ልደት ዓመታዊ በዓል እያከበርን ነው…” ይለዋል፡፡ ሰውየውም ግራ ይገባዋል፡፡ “የእህቴን ልደት ዓመታዊ በዓል ብሎ ነገር ምንድነው? ወይ ልደት ታከብራለህ፣ ወይ ዓመታዊ በዓል ታከብራለህ፡፡ ሁለቱ የሚገናኙ አይደሉም…” ይለዋል፡፡
ጓደኛየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“አይ ሞኞ…የእህቴን አሥራ ስምንተኛ ዓመት ልደት አሥራ አምስተኛ ዓመታዊ በዓል እያከበርን ነው…” ብሎት አረፈ፡፡ አሪፍ አይደል!
የዕድሜ ነገር ከተነሳ… ይቺን ስሙኝማ…“በቀደም ሀያ ዘጠነኛ ዓመቴን ሳከብር ለምንድነው ስጦታ ያልሰጠኸኝ?”  ብትለው እሱዬው… “ረሳሽው እንዴ! የዛሬ አምስት ዓመት ሀያ ዘጠነኛ ልደትሽን ስታከብሪ ሽቶ አልሰጠሁሽም?” ብሏት አረፈ፡፡
እናላችሁ…ጉልቤነት መልኩን እየለዋወጠ መከራችንን እያበላን ነው፡፡ ቤት አከራይ በቀን ሁለት ባሊ ውሀ ብቻ እየፈቀደ፣ መብራት በሦስት ሰዓት ላይ እያጠፋ፣ “ከአንድ ሰዓት በኋላ ማምሸት ክልክል ነው…” አይነት ክፉ ሚስት እንኳን የማታስበው ‘ህግ እያረቀቀ’ ይቆይና አንድ ቀን ማታ በር ይንኳኳል፡፡ እናንተም ስትከፍቱ አከራያችሁ ተኮሳትረው ቆመዋል፡፡ እናንተም…“ደህና አመሹ፣ ምነው ደህና!” ስትሉ ምን ትባሉ መሰላችሁ…“ኪራዩ ላይ ከሰኞ ጀምሮ አንድ ሺህ ብር ጨምረናል፡፡
 ካልተስማማችሁ በሁለት ቀን ውስጥ ቤቱን ልቀቁልን፡፡” የምር ያበሳጫል፡፡ ስሙኝማ…የብስጭት ነገር ከተነሳ … “እንትናዬው ምን ያህል ብታበሳጨው ነው ሴቶችን እንደዚህ ጠምዶ የያዛት!” የሚያሰኝ ንግግር ገጥሟችሁ አያውቅም!
ሰውየው ጓደኛውን… “ሬድዮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረው በገነት ውስጥ ነው ሲሉ ሰማኋቸው፡፡
ምን ማለታቸው ነው?”  ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝዬውም ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“እሱን የነገሩህ ሰዎች ፈጣሪ አዳምን ፈጠረ፡፡ ከዚያም ከጎኑ የጎድን አጥንት አወጣና የመጀመሪያውን ድምጽ ማጉያ ፈጠረ ማለታቸው ነው፣”  ብሎት አረፈ፡፡‘ጉልቤነትን’… አለ አይደል… ሲሆን ያስወግድልን፣ ካልሆነም የምንሸከምበትን ትከሻ ያደንድንልን፡፡
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” የምንልበትን ጊዜ ያሳጥርልን፡፡  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4036 times