Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Friday, 06 January 2012 12:15

ቴዲ አፍሮ ምን ይዞልን ይመጣ ይሆን?

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ለፋሲካ ይወጣል ለተባለው አልበም 4ሚ. ብር ተከፍሎታል

የቴዲ አፍሮ አልበም ለገና አልደረሰም

ነጠላ ዜማዎቹ አነጋጋሪ ሆነዋል

ቴዲ አፍሮ ከየት ወዴት?

አንጋፋውና ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ሙሉ አልበም ካሰማን ረዘም ያለ ጊዜ ያስቆጠረ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ ቴዲ አልበም በጥድፊያና ቶሎ ቶሎ በመልቀቅ አይታወቅም፡፡ ሥራዎቹ የታሹና በጥንቃቄ የሚሰሩ ስለሆነ ዓመታት ይፈጃሉ፡፡ ድምፃዊው ይሄን የሚያካክሰው ነጠላ ዜማዎች በመልቀቅ ይመስላል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ቴዲ “የነጠላ ዜማዎች ጌታ” ነው -  በየጊዜው በርካታ ዜማዎችን ለቋል፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ ጊዜ የወጡ 6 ነጠላ ዜማዎችን አግኝቼ አድምጫለሁ፡፡ ለነገሩ ሙሉ አልበም ይወጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው ነጠላ ዜማዎቹ የተለቀቁት፡፡ ምንጮች እንደሚሉት አዲስ ለሚያወጣው አልበም ድምፃዊው ከፍተኛ ገንዘብ በመከፈል በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ታሪክ ሪከርድ ሰብሯል - ለአንድ አልበም 4ሚ. ብር ተከፍሎታል ተብሏል፡፡ እነዚሁ ምንጮች ቅድምያ ክፍያም (ቀብድ) መውሰዱንም ይናገራሉ፡፡ ይሄን ያህል መረጃ ከነገርኳችሁ ይበቃል፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ ወደተለቀቁት የቴዲ ነጠላ ዜማዎች ልውሰዳችሁ፡፡ ቴዲ አፍሮ አዲስ የዘፈን አልበም እንደሚያወጣ መነገር ከጀመረ በርካታ ወራትን አስቆጥሯል፡፡ አርቲስቱ ራሱ ባለፈው ዓመት መዝጊያ ላይ በአርቲስት ግርማ ተፈራ የአልበም ምርቃት ላይ ተገኝቶ ሥራውን ለገና በዓል እንደሚለቅ ተናግሮ ነበር፡፡  በሙሉ አልበም የተጠበቀው አርቲስት፤ የማታ ማታ በአርቲስት ኩኩ ሰብስቤ ‹‹የበረሃ አገር ስደተኛ›› ነጠላ ዜማ ላይ አጃቢ በመሆን ‹‹ቆሜ ስነቃ›› በማለት ድምጹን አሰማ፡፡  የአርቲስት ቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ግን ለገና አልደርስ ብሎ ለፋሲካ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ በምትኩ ታዲያ ‹‹ውዴ›› የተሰኘ አንድ ነጠላ ዜማ መሰረቁን በብዙሃን መገናኛ ይፋ አድርጐ ነበር - አርቲስቱ፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ሬዲዮ ጣቢያዎች ይህንን ነጠላ ዜማ እንዳያስተላልፉ የጹሑፍ ማሳሰቢያ ልኮ ነበር - ቴዲ፡፡ ጥቂት ቀናት ቆይቶ ደግሞ እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥመው መፍትሔ ከሚሰጥበት መንገድ አንዱ፣ ዘፈኑን አሻሽሎ ማቅረብ መሆኑን በመግለጽ ተሻሽሏል ያለውን አስደመጠ፡፡ እኔ በበኩሌ ግን የጃፓኖችን ኢንስትሩመንታል የመሰለ ሙዚቃ በየመሃሉ ከማስገባቱ በቀር ምንም የተሻሻለ ነገር አላየሁበትም፡፡  “ውዴ” በሚል የሰራው ዜማ ከመጽሐፍ ቅዱሱ “መሐልዬ መሐልዬ ዘ ሰለሞን” እና ከተለያየ ምዕራፍ በተወሰዱ “ውዴ፣መስክ፣የወይን ሥፍራ፣የዐይን ጫፍ፣የወይን አጥር ጋራ፣አጥሩም ድንበሩም፣ባለጸጋ፣የወይን ቦታ ጠባቂ፣የጸደይ ወራት”  …..የመሳሰሉ ቃላት የተሞላ ግጥም ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ‹‹ውዴ›› የተሰኘው ዘፈን ከመሰረቅ አልዳነም፡፡ ለነገሩ የቴዲ ዘፈን “ተሰረቅሁ” ስሞታ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ለመጪው አልበም የጉጉት መፍጠሪያ ቴክኒክ ይሁን አሊያም የአድማጭ አስተያየት መመዘኛ ከጥርጣሬ በቀር ምንም ለማለት አልቻልኩም፡፡ እውነቱን የሚያውቅ እሱ ብቻ ነው - ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዲ፡፡ ወህኒ ቤት ሳለም ተሰረቅሁ ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡ የዘፈኑ አጠቃላይ ሐሳብ ድምፃዊ ጸጋዬ እሸቱ ከረዥም ዓመት በፊት ‹‹ለሰርጓ ተጠራሁ›› ሲል ጥርት አድርጎ የዘፈነውን ዘፈን በእጅጉ ይመሳሰለዋል፡፡

ሰሞኑን ከተቀለቁት ዜማዎች የሚጠቀሱት ‹‹ፊዮሪና” እና “ልረሳሽ አልቻልኩም›› የሚሉት ሁለት ዘፈኖች ዜማ ደግሞ ተስፋይ ተክለእዝጊ ከተባለ ኤርትራዊ ድምጻዊ የተቀዳ ወይም የተኮረጀ ይመስላል፡፡ ዜማው የተኮረጀ ቢሆንም ግን ግጥሙ አዲስ ነው፡፡ሐሳቡም ቀደም ሲል ቴዲ ካቀነቀነው  ‹‹ብንለያይም ልረሳሽ አልቻልኩም›› ዜማ ጋር ይመሳሰላል፡፡

ከራሱ ዜማ የተኮረጀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹አይደነግጥም ልቤ፤ ለሌላ ልቡን አይሰጥም›› የሚለው ሦስተኛው ዜማ ጭብጥ ከዚህ ቀደም ከሰማኋቸው የበርካታ አርቲስቶች ተደጋጋሚ ዘፈን አንድም የተለየ ነገር የለውም፡፡  አጠቃላይ ሐሳቡም ‹‹ልቤ ምንም ሌላ ቆንጆ ቢመለከት አይደነግጥም፤ አንቺን በጣም እወድሻለሁ››የሚል ነው፡፡ ቴዲ የኢትዮጵያ ዘፋኞች የድምፅ መሞረጂያ የሚመስለውን የፈረደበትን ‹‹ዓባይ›› በነጠላ ዜማ ልሞክረው በሚል በአባይ ዙሪያ አቀንቅኗል፡፡ የቴዲ‹‹ዓባይ››ም ግን ከቀደሙት የተለየ አዲስ ነገር ይዞ አልመጣም፡፡ በአጠቃላይ ነጠላ ዜማዎቹ ኦሪጂናሊቲ (አዲስነትና ፈጠራ) ይጐድላቸዋል፡፡  ንግዲህ ቴዲ አዲሱን አልበምን የሚያወጣው ለፋሲካ በዓል ነው ተብሏል፡፡ ይሄን ያህል ጊዜ የጠበቀ አድማጭ ደግሞ ከድምፃዊው የላቀ ሥራ ቢጠብቅ ሊፈረድበት አይችልም፡፡ ካሁኖቹ ነጠላ ዜማዎች እንደምናየው ከሆነ ግን ቴዲ ቀላል የማይባል ፈተና ይገጥመዋል፡፡ በእርግጥ የተሻሉ የጥበብ ሥራዎችን ለመስራት ጊዜ አለው፡፡ የአድማጭን አንጀት የማያርሱ ዜማዎች ከማውጣት ደግሞ መዘግየቱ ይመረጣል፡፡  አርቲስቱ በእስካሁኑ ሥራዎቹ የአድማጭን ቀልብ በመቆጣጠር ዝናንና ተወዳጅነትን በአጭር ጊዜ መቀዳጀቱን ማንም ሊክድ አይችልም፡፡ ለዚህ የበቃው ደግም ሙያውን አክብሮና ለሥራው ተጨንቆ ተጠቦ ምርጥ ሥራዎች ይዞ ስለሚቀርብ ነው፡፡ በቀጣዩ አዲስ አልበሙም ተመሳሳይ ጥረት ይጠበቅበታል፡፡ ለነገሩ ነጠላዎቹን የለቀቀው አንዳንዶች እንደሚሉት የሥራዎቹን ተቀባይነት ለመመዘን ከሆነ ጥሩ አድርጓል፡፡ እኔም በግሌ ታዲያ በእንዲህ ዓይነት ሥራዎች ከመጣህ የሚያዋጣህ አይመስለኝም፤ የተሻሉና የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ዜማዎች ሰርተህ ተመለስ ልለው እወዳለሁ፡፡ መልካም የገና በዓል - ለሁላችንም!!

 

 

Read 15383 times Last modified on Friday, 06 January 2012 12:23