Saturday, 27 December 2014 16:25

ዛሬም ይዞረኛል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ሄደ … አለፈ ብዬ ትንሽ ፋታ ሳገኝ፣
የተጫነኝ ችግር የጠፋ ሲመስለኝ፣
ተመልሶ መጥቶ ጎንተል ያደርገኛል፣
የራቀ ሲመስለኝ ዳግም ይቀርበኛል፣
ከጋለው ሊጥደኝ መልሶ ይዞረኛል፡፡
እኔ ቀርቤው ነው? ወይ እሱ እየመጣ፣
የማንለያየው - የማንተጣጣ፡፡
አንዴ እየራቀ፣ ዳግም እየመጣ …
        ይሽከረከረኛል፣
ቁራኛዬ ሆኖ አልለቅህም ብሎ …
        ያንዣብብብኛል፡፡
ከዚህ ችግር ዕዳ - ከእንቶ ፈንቶ ጣጣ፣
ሊያድነኝ ከሁሉም ከማጡ ሊያወጣ፣
ዳግም ወደ መሬት ክርስቶስ አይመጣ፣
ታዲያ እንዴት ልሁነው?
እንዲሁ እንዳለሁ ፍግም ልበለው!?
        … ኧረ አሳዝናለሁ፣
        … አፈር እከብዳለሁ፡፡
ይህ መንገራገጩ ጠቅልሎ አልሄድ ያለው፣
እንዴት ቢያፈቅረኝ ነው ከኔ የማይለየው!?
ፊትም፣ አምና፣ ዛሬ አልተውህ ብሎኛል፣
ነገሩ ምንድነው? - ዛሬም ይዞረኛል፡፡

ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
ታህሣሥ 2007 ዓ.ም

Read 3809 times