Print this page
Saturday, 27 December 2014 16:17

የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም ባለ 11 ፎቅ ህንፃ ሊገነባ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

     በ21 ኢትዮጵያዊያን የተመሰረተውና ነዳጅ በማከፋፈል የመጀመሪያው አገር በቀል ድርጅት የሆነው የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም አክሲዮን ማህበር ለዋና መስሪያቤትነት ባለ 11 ፎቅ ህንፃ ሊገነባ ነው፡፡ ድርጅቱ ከትናንትና በስቲያ ሲኤምሲ በሚገኘው ማደያ ግቢ ውስጥ የተመሠረተበትን 10ኛ ዓመት በዓል ከባለ አክሲዮኖቹ ጋር በድምቀት ያከበረ ሲሆን የመስኖ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ የህንፃውን የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡ 50 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተገመተው ህንፃ፤ ከዋና መስሪያ ቤትነት በተጨማሪ ለተለያዩ አገልግሎቶችም ይውላል ተብሏል፡፡ 261 ባለአክሲዮኖችና የተከፈለ 135 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያለው የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም፤ በመላ አገሪቱ መቶ ያህል ማደያዎች ያሉት ሲሆን ከአንድ ሺህ በላይ ለሆኑ ቋሚና ጊዚያዊ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩን የድርጅቱ ዋና የስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መኮንን በእለቱ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጥራት ያለው ነዳጅ ከማከፋፈሉም በላይ ጥራት ያላቸው የብሪቲሽ ፔትሮሊየምን የሞተር ዘይቶች በብቃት እንደሚያከፋፍል የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ የነዳጅ ማደያ ምልክቱንም ቢሆን በአንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ አሰርተው ማስገጠማቸውን ተናግረዋል፡፡ የውሃ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ባደረጉት ንግግር፤ አገር በቀል ድርጅቶች ነዳጅ ቢያከፋፍሉ ለአገር ጠቀሜታ ያለውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት በጥቅምት ወር 1996 ዓ.ም በሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ብሔራዊ ፔትሮሊየም ወደ ዘርፉ በመግባት ከፍተኛ እድገት እንዳመጣ ገልፀው ለመስራቾቹ፣ ለባለአክሲዮኖችና ለድርጅቱ ሰራተኞች ለዚህ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡ ድርጅቱ የ10ኛ ዓመት ምስረታውን አስመልክቶ ባዘጋጀው በዓል የተለያዩ አስተዋፅኦዎች ላበረከቱ ወገኖችና ሠራተኞች ሽልማት አበርክቷል፡፡ ለዋና መስሪያ ቤትነት የሚገነባው ህንፃም በሁለት ዓመት ተጠናቅቆ ስራ እንደሚጀምር ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

Read 2290 times