Saturday, 27 December 2014 16:13

ቢጂአይ ኢትዮጵያ የወይንና የቢራ ፋብሪካዎችን አስጎበኘ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

“ቢራ ሃንግኦቨር የሚፈጥረው ፈርሜንቴሽኑን ካልጨረሰ ነው”

    ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ከየሚዲያው የተውጣጡ ጋዜጠኞች፣ የአዲስ አበባ የጤና ቡድን አመራሮችና ሌሎች እንግዶች ቢጂአይ ኢትዮጵያ ባደረገላቸው ግብዣ መሰረት፣ የዝዋይን የወይን ጠጅ እርሻና ፋብሪካ እንዲሁም የሀዋሳን የቢራ ፋብሪካ ጎብኝተው ነበር፡፡ እኔም ከጐብኚዎቹ አንዱ ነበርኩ፡፡በመጀመሪያ የጎበኘነው ዝዋይ የወይን እርሻና ፋብሪካ ነው፡፡ ወይን የሚመረተው በዓመት አንዴ ስለሆነ ጠመቃውም አንድ ጊዜ ነው፡፡ የዕለት ተዕለት የሥራ ሂደት ያለው ቢራው ስለሆነ በዚያ ላይ አተኩራለሁ፡፡ እናንተ! ይኼ በየመጠጥ ቤቱ የምንጠጣው ድራፍትና ቢራ በርካታ ሂደቶች አልፎ ነው ለካ የሚቀርብልን፡፡ ውሃው በተለያዩ ኬሚካላዊ ሂደት ውስጥ አልፎና ተጣርቶ፣ መጥመቂያ ጋኖቹም በኬሚካሎች ታጥበው፣ ንፁህ መሆናቸው በላብራቶሪ ፍተሻ ተረጋግጦ ነው ቢራ ጠመቃው የሚጀመረው፡፡
ለቢራ ምርት የሚያስፈልጉት አራት ነገሮች ውሃ፣ የቢራ ገብስ (ብቅል) ጌሾና እርሾ ናቸው፡፡ የትኛውም የቢራ ፋብሪካ የሚያስፈልጉት ዋነኛ ንጥረ ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡ ልዩነት የሚፈጠረው በአቀማመም ሂደት ነው፡፡ የቢራ ጠመቃ የሚጀመረው ገብሱን (ብቅሉን) በመፍጨት ነው፡፡
 የሃዋሳው ቢጂአይ ቢራ ፋብሪካ ለአንድ ጊዜ ጠመቃ 5,950 ኪሎ የገብስ ብቅል እንደሚፈጭ የፋብሪካው የፕሮዳክሽን ቺፍ ሊደር አቶ ደገፋው ማዘንጊያ ገልፀዋል፡፡ ወፍጮው አውቶማቲክ ስለሆነ ገብሱን ራሱ በማበጠር ጠጣር ነገሮችን (አፈር፣ ብረት…) እንዲሁም ገለባ ይለያል፡፡ ከዚያም ዱቄቱ በ13.500 ሊትር ይቦካና በተለያዩ የሙቀት ደረጃዎች እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ የቢራ ጥራት የሚወሰነው፤ በገብሱ ሽርክትና መጠን እንደሆነ አቶ ደገፋው ይናገራሉ፡፡ ፋብሪካው 12 ጋኖች ሲኖሩት እያንዳንዱ ታንክ 200ሺ ሊትር ሃይ ግራቪቲ ቢራ እንደሚይዝ፣ ፈርሜንቴሽን (ማብላያ) ጋን ውስጥ ከ15-20 ቀን እየተብላላ እንደሚቆይ፣ በመጀመሪያው ፈርሜንቴሽን ለ7 ቀናት በ12 ዲግሪ ሙቀት፣ በሁለተኛው በ16 ዲግሪ ሙቀት ለ72 ሰዓታት እንደሚቆይና ከሦስት ቀናት በኋላ ተጣርቶ ለገበያ እንደሚቀርብ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡
የድራፍትና ቢራ የአመራረት ሂደት አንድ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ልዩነት የሚመጣው በፓስቸራይዜሽን ሲስተሙ፣ በመያዣ ዕቃ (ፓኬጂንግ) በርሜልና ጠርሙስ መሆንና በካርቦንዳይ ኦክሳይድ ይዘት እንደሆነ ገልጿል፡፡ ድራፍት የሚቀቀለው (ፓስቸራይዝ የሚደረገው) በ94 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲሆን ቢራ ደግሞ በ62 ዲግሪ ረዘም ላለ ጊዜ ነው፡፡ ድራፍትም ሆነ ቢራ የሚቀቀሉት (ፓስቸራይዝድ የሚደረጉት) ሳይበላሹ የመቆያ ጊዜያቸውን ለማራዘም እንደሆነ የጠቀሱት ሺፍ ኃላፊው፤ ፓስቸራይዝድ የተደረገ ቢራ ሳይበላሽ ለአንድ ዓመት፣ ድራፍት ደግሞ ለአንድ ወር ይቆያሉ ብለዋል፡፡
የቢራ ሃንግኦቨር (በማግስቱ ራስ ምታት) የሚፈጠረው በፈርሜንቴሽን ጊዜ ቆይታ ማነስ ወይም መብዛት እንደሆነና ጊዜውን በመቆጣጠር ማስቀረት እንደሚቻል አቶ ደገፋው አስረድተዋል፡፡ ለምሳሌ ቢራው ውስጥ ብዙ ጉሉኮስ (ስኳር) እያለ የፈርሜንቴሽኑ ጊዜ አጭር ከሆነ (በደንብ ካልተብላላ) ከፍተኛ አልኮሎች ይመረቱና ቢራው ሲጠጣ ራስ ምታት ያመጣል፡፡ ፈርሜንቴሽን በጣም እንዲዘገይም ሆነ እንዲፈጥን አይደረግም፡፡ ከገበያ አኳያ እንዲዘገይ፣ ከጥራት አኳያ እንዲፈጥን ማድረግ ጥሩ አይደለም፡፡ ሲዘገይም ሆነ ሲፈጥን የሚፈጠር ነገር (ያልተፈለገ ምርት) አለ፡፡ ያ ነው ራስ ምታት የሚፈጥረው በማለት አስረድተዋል፡፡
ሴላር የሚባለው ፈርሜንቴሽኑን ያልጨረሰና የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ያልያዘ በጣም ወፍራም ቢራ ነው ይላሉ - አቶ ደገፋው፡፡ የአልኮል መጠኑ ከፍተኛ፣ እንዲሁም በጣም ወፍራምና ያልተጣራ ስለሆነ ገበያ ላይ ቢወጣ ብዙ ሰው አይጠጣውም፡፡ ስለዚህ አልኮሉ እንዲቀንስ (ዳሊዩት) ይደረጋል፤ ይጣራና ተገቢውን የውፍረት መጠን ይዞ ወደ ገበያ ይወጣል ብለዋል፡፡
ሴላር መጠጣት ወይም አለመጠጣት የደንበኛው ፍላጎት ነው፡፡ ነገር ግን ሴላር ገበያ ሲወጣ ከቢራ እኩል አይሸጥም፤ ዋጋው ወደድ ይላል፡፡ ፓስቸራይዝድ ስላልሆነ ለጤናማም ጥሩ አይደለም፡፡ ሴላር ወዲያው ካልተጠጣና ሁለት ሦስት ቀን ከቆየ ይበላሻል፡፡ ስለዚህ ሴላር መጠጣት ካለበት ፋብሪካው አካባቢ፣ የሚጓጓዝበትም መኪና ማቀዝቀዣ ያለው መሆን አለበት በማለት አቶ ደገፋው ማዘንጊያ አብራርተዋል፡፡  


Read 2090 times