Saturday, 27 December 2014 16:07

ጠ/ሚኒስትሩ ከአዳዲስ መረጃዎች ጋር አስተዋወቁን!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(16 votes)

አውሮፓ ህብረት ምርጫውን የማይታዘበው በገንዘብ ችግር ነው
ተቃዋሚዎች ባይነግሩንም  ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተው ነበር
እነ “ኤፈርት” ከአውራው ፓርቲ  ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም ተባለ

    ባለፈው ማክሰኞ በቀድሞው ኢቴቪ (በአዲሱ EBC) በምርጫ ዙሪያ የቀረበው ዘገባ አስደምሞኛል (ሌላ ምርጫ የለኝማ!) ለነገሩ ዘገባ ከማለት ይልቅ ያፈጠጠ የምርጫ ቅስቀሳ ቢባል ይቀላል (መተቸቴ እኮ አይደለም?!) ቢያንስ ግን በEBC ጋዜጠኛ ባይሰራ ይመረጥ ነበር (ልማታዊ ጋዜጠኛ መሆኑ አልጠፋኝም!)
እኔ የምለው ግን… EBC በቢቢሲ ሞዴል ይዋቀራል የተባለው ቀረ እንዴ? (ኧረ እንኳንም ቀረ!)፡፡ ለምን አትሉም? ለልማታዊ መንግስት አይመችማ! (ኒዮሊበራሎች እጅ ጠምዛዞች “arm twister” ናቸው!)
እናላችሁ… የEBC ጋዜጠኛ ስላለፉት ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫዎች በቃሉ የፃፈውን ስክሪፕት ትንሽ ካነበነበ በኋላ “በግንቦቱ ምርጫ ዙሪያ ያሰባሰብኩትን የነዋሪዎች አስተያየት ተከታተሉኝ” አለ፡፡ (አስተያየት ሰጪዎቹ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች”ን አስታወሱኝ!) አይገርማችሁም… እነዚህ “ነዋሪዎች” ሁሌም ምርጫ ሲደርስ ከተፍ ይላሉ፡፡ እናም “ይሆነኛል… ይበጀኛል… የምለውን …”፣ “ልማቱን ያስቀጥልልኛል ያልኩትን …”፣ “ልማታዊ መንግስት የምለውን --” ወዘተ-- እንመርጣለን እያሉ አስተያየት ሰጡ፡፡ አንዳንዶቹም “ህዝቡ በምርጫው እንዲሳተፍ በመቀስቀስ የዜግነት ግዴታዬን እወጣለሁ” አሉ፡፡ (ግዴታና ውዴታ ተምታታብን እኮ!) እኔ የምላችሁ … EBC የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ እንደሆንን አልሰማም እንዴ? (የነፃ ገበያ አቀንቃኞች ሃሳብ አልተስተናገደም ብዬ እኮ ነው!)
በነገራችን ላይ--ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ “የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከሌለ፣ ዕጣ ፈንታችን የሶማሊያ ዓይነት ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ (የEBC ጋዜጠኞችን ይመለከታል!) ለማንኛውም ግን  የምርጫ ቅስቀሳው ተጀምሯል፡፡ የጀመረው ግን ኢህአዴግ አይደለም፤ EBC ነው፡፡ (“ያለ ዕዳው ዘማች” አሉ!)
ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ምን እንደታዘብኩ ልንገራችሁ? ከስልጣናቸው ጋር በደንብ መለማመዳቸውን፡፡ (ፈጣን ተማሪ ናቸው ማለት ነው!) ቢሆኑማ ነው--- ሰሞኑን “የዓለማችን ምሁር መሪዎች” በሚል ከእነ ኦባማ ተርታ መሰለፍ የቻሉት፡፡ (ለአገር ገፅ ግንባታ ማለፊያ ግብዓት አገኘን!)
እናላችሁ … የማይለመድ የለም-- ሥልጣኑን በደንብ ተለማምደውታል፡፡ ለዚህ እኮ ነው በሰሞኑ መግለጫ  ከሌላው ጊዜ በተለየ ተረጋግተው… በልበሙሉነት… ቁጣና ፍረጃ ሳያበዙ… ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ያየነው፡፡ (አሁን ተረብ ብቻ ነው የቀራቸው!)  በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተመለከተ የተናገሩት ያልተጠበቀ ነው (ተቃዋሚዎች ራሳቸው መገረማቸው አይቀርም!) ጋዜጣዊ መግለጫቸውን የቋጩት፤ “ለጋራ አገራችን በጋራ እንወያይ የሚል ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ” በሚል መልዕክት ነው፡፡  (“ባንዳፍ” ብለናቸዋል!)
ብዙዎች ግን አንድ ጥያቄ አላቸው፡፡ “ይሄ አቋም የግላቸው ነው የፓርቲያቸው? ወይስ የመንግስታቸው?” የሚል፡፡ ለእኔ ግን ለውጥ የለውም፡፡ ዋናው ከአንጀታቸው መሆኑ ነው፡፡ ከባለፈው ምርጫ የዞረው የፈረደበት “የሥነምግባር ደንብ” ግን አሁንም አልቀረም፡፡ (ፊርማ ከሌለ፤ ውይይት የለም!) እኔ ተቃዋሚዎችን ብሆን ግን --- የአበሽነት እልሄን ዋጥ አድርጌ፣ የተባለውን ግጥም አድርጌ እፈርም ነበር (“ኩራት እራት አይሆንም” አለ አበሻ!)በሰሞኑ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ጠ/ሚኒስትሩ ከአዳዲስ መረጃዎች ጋር አስተዋውቀውናል፡፡ ከአንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር በግል የመወያየት ዕድል እንደገጠማቸው አስታውሰው፤ አመራሮቹ የሥነምግባር ኮዱን ፈርመው የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤትን እንዲቀላቀሉ አሳምነው ከላኳቸው በኋላ ሌሎቹ አልተስማሙም ብለው እንደቀሩ ተናግረዋል፡፡ (ተቃዋሚዎች ውይይቱን ምስጢር ማድረጋቸው ግን ያስተዛዝባል!) ስንቱን ነገር ሲነግሩን ከርመው …  እንዴት ይሄን ይደብቁናል?! ለነገሩ አይፈረድባቸውም፡፡  (ከ”ኢህአዴግ ጋር ተሞዳሞዱ” የሚል ውግዘት ፈርተው ይሆናል!)
ጠ/ሚኒስትሩ ሌላም የነገሩን መረጃ አለ፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ለውይይት ሲጋበዙ “እነ እገሌ ካሉ (እነ እገሌ እኮ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው!) አንሳተፍም” እንደሚሉ ጠቁመው፤ ከዚህ አቋማቸው ወጥተው በጋራ ለመወያየት መዘጋጀት እንዳለባቸው መክረዋቸዋል (ተቃዋሚዎች የባህርይ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል!) እኔ የምለው … ኢህአዴግ ለየብቻችን ካላነጋገረን የሚሉት በልማት መወጠሩን ዘንግተውት ነው ወይስ ልማቱን ለማደናቀፍ? (መቼም ልማቱን ትቶ ሲወያይ አይከርምም!)
እንዲያም ሆኖ… የደቡብ ሱዳን ፓርቲዎችን ለማደራደር እሳቸውና ፓርቲያቸው ካሳዩት ጥረትና ትዕግስት  አንጻር ለአገራቸው ፓርቲዎች ገና ብዙ ጥረትና ትዕግስት ይቀራቸዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ፤ አሁንም በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ተስፋ እንደማይቆርጡም ተናግረዋል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ---- በአገራቸው ተቃዋሚዎችም ተስፋ አይቆርጡም፡፡
ከጠ/ሚኒስትሩ የሰማነው ሌላ አዲስ መረጃ ምን መሰላችሁ? … የኢህአዴግ ናቸው ሲባሉ የነበሩት የንግድ ድርጅቶች - ኢንዶውመንትስ- (እነ ኤፈርትን ለማለት ነው!) ከኢህአዴግ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ነግረውናል፡፡ ይሄ ትንሽ ግራ ያጋባል፡፡ የኢህአዴግ ካልሆኑ የማን ናቸው? (የተቃዋሚዎች እንዳይሆኑና  እንዳይገርመኝ!) ከመጪው የግንቦት አገራዊ ምርጫ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ውዥንብሮችንም ጠ/ሚኒስትሩ አጥርተዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት በምርጫው በታዛቢነት የማይሳተፈው መንግስት ሳይጋብዘው ቀርቶ ሳይሆን በራሱ የገንዘብ ችግር እንደሆነ ነግረውናል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ግን ለአውሮፓ ህብረት ግብዣው የቀረበለት ባለቀ ሰዓት ነው ይላሉ፡፡ (“እንዳያማህ ጥራው---” ሆኗል ለማለት እኮ ነው!) የሆኖ ሆኖ ግን  ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ “ምርጫው በእጃችን ነው፡፡” ሰናይ ሰንበት!

Read 4368 times