Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Friday, 06 January 2012 11:46

ዓለምን የለወጡ እጅግ የላቁ ፈጠራዎች

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ትራንዚስተር ባይፈጠር ኖሮ ኢንተርኔትና የጠፈር ጉዞ አይኖሩም ነበር

እጅግ ኋላ ቀር ዘመን የነበረው የዛሬ 1ሺ ዓመት…

የኤሌክትሪክ ኃይል፡- ዘመናዊው ዓለም በኤሌክትሪክ ኃይል የተንቆጠቆጠ ነው፡፡ ከበርካታ የኤሌክትሪክ መገልገያ ቁሶች መካከል ማንኛውም ቁስ፣ ከተጠናቀቀው ሚሌኒየም (20ኛው ክፍለ ዘመን) እጅግ በጣም ጠቃሚ ፈጠራዎች ዝርዝር ውስጥ ሊካተቱ ይገባል ብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል፡፡ በተለይም አምፑል የሌሊቱን ጨለማ ሞገስ ነስቶ የብርሃን ፀዳል በማጐናፀፍ የሰው ልጆችን እንቅስቃሴ ምቹ በማድረግ ሕይወትን እጅግ በላቀ ደረጃ ቀይሯል፡፡ ነገር ግን አምፑል፣ ቴሌቪዥን፣ ስቴሪዮ፣ የልብና የሳንባ ሌዘር መሳሪያዎችና እጅግ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ጠቃሚ አገልግሎት መስጠት የቻሉት የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማዕከል በመኖሩ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ መሳሪያዎች ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል ምንም ጥቅም የላቸውም፡፡

የኤሌክትሪክሲቲን ሞገድ ፈጥሮ፤ በየቤቱ፣ በየፋብሪካውና በየኢንዱስትሪው ማከፋፈል ዓለምን የለወጠውን ኃይል አንድም የኤሌክትሪክ መሳሪያ አለወጠም፡፡ በእርግጥ ቶማስ ኤድሰን ሲሞቅ እንደፍም በሚግልና በሚያብረቀርቅ አምፑሉ በጣም ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እሱ ያወረሰን እጅግ ጠቃሚ ነገር ምናልባትም የኤሌክትሪክ ኃይል ኢንዱስትሪው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ኤድሰን በአሜሪካ፣ የመጀመሪያ የሆነውን ትልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በኒውዮርክ የመሠረተው በ1882 ዓ.ም ነበር፡፡

ኤሌክትሪሲቲን ለመፍጠር ጥናት የተጀመረው በ1600 መጀመሪያ አካባቢ ነበር፡፡ በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አሜሪካዊው ባለሥልጣንና ሳይንቲስት ቤንጃሚን ፍራንክሊን የተከበረውን የኤሌክትሪክ ምርምር አካሄደ፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው የመብራት ኃይል የመጀመሪያዎቹና ያልተሻሻሉት ጥንታዊ ባትሪዎች በተወሰነ ደረጃ የሚያመርቱት ኃይል ብቻ ነበር፡፡ ለምሳሌ በ1840ዎቹ ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መድረክ ብቅ ያለው ቴሌግራፍ በባትሪ ኃይል የሚሠራ ነበር፡፡

ኤሌክትሪሲቲ በከፍተኛ መጠን ለሰው አገልግሎት እንዲውል ያደረገው የዲናሞ መፈጠር ሲሆን ዲናሞ፣ በመሳሪያ እንቅስቃሴ የተፈጠረን መካኒካል ኃይል ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀይር መሳሪያ ነው፡፡ ዲናሞ፣ እንግሊዛዊው ሳይንቲስት ሚካኤል ፋራዳይ በ1831 ዓ.ም ባፈለቀው ግኝት ላይ ተመሥርቶ የተሠራ መሳሪያ ነው፡፡ የፋራዳይ ግኝት የማግኔት ሞገድ ባለበት ስፍራ ሽቦ ቢጠመጠም የኤሌክትሪክ ሞገድ ሽቦው ላይ ይፈጠራል የሚል ነው፡፡ ይህም በእንፋሎት እየተሽከረከረ ኤሌክትሪክ የሚፈጥረውን የብረት ምሰሶ በቀጥታ በዚህ ዘዴ መተካት አስቻለ፡፡ ኤሌክትሪኩ አንዴ ከተፈጠረ በኋላ የሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ ኃይሉን በየቤቱ፣ በየፋብሪካውና በየቢሮው የሚያደርስ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ሽቦና የትራንስፎርመር ሲስተም ብቻ ነው፡፡

በዚህ ዓይነት ማብሪያና ማጥፊያ በመጫን ብቻ ርካሽና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት በአብዛኛው የዓለም ዙሪያ የአኗኗር ደረጃን ከፍ አደረገ፡፡ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለመገንዘብ በተለያየ ምክንያት መብራት ሲጠፋ፣ ምን እንደሚፈጠር እስቲ አስቡት፡፡ ክብሪት ለማግኘት በጨለማ ይደናበራሉ፤ ኮምፒዩተርን ጨምሮ አብዛኛው የቤት ዕቃ አይሠሩም፤ ያለ መብራት ምንም ጥቅም በማይሰጠው ማቀዝቀዣ ውስጥ የተቀመጠ ምግብ ይበላሻል፡፡ ሕይወት ለጊዜውም ቢሆን ቀጥ ትልና መብራት ሲመጣ ዑደቷን ትቀጥላለች፡፡

ቴሌግራፍ፡- በአብዛኛው  የሰው ልጅ ታሪክ በረዥም ርቀት መልዕክት (ኢንፎርሜሽን) መለዋወጫ ዘዴ፣በዋነኛነት፣ በሰው በመላላክ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ተወዳጅ ከሆኑት የአትሌቲክስ ስፖርቶች አንዱ ማራቶን በጥንታዊት ግሪክ ፊዲፕዲስ የተባለ ወታደር 42ኪ.ሜ ከ195 ሜ ርቀት ሮጦ፣ ታላቁን ጣፋጭ ድል ያበሰረበትን ድርጊት ለማሰብ ነው፡፡ መልዕክተኛው የድሉን ዜና ከተናገረ በኋላ ተዝለፍልፎ ወዲያውኑ እንደሞተ አፈ-ታሪክ ይነግረናል፡፡

መጀመሪያ ፈረሶች ቀጥሎም የእንፋሎት ሞተር መልዕክቱ በጉዞ የሚያጠፋውን ጊዜ ቢያሳጥሩትም ያደረጉት መሻሻል መጠነኛ ነው፡፡  ከዚያም በመቀጠል ቴሌግራፍ መጣ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዓለም ሙሉ በሙሉ ተለወጠች፡፡

በቴሌግራፍ መልዕክት የማስተላለፊያ ዘዴ ቀላል ነው፡፡ መልዕክቱ በታይፕ ሲጻፍ የሚፈጠረው የኤሌክትሪክ ሞገድ ንዝረት በሽቦ አማካይነት ይላካል፡፡ ንዝረቱ መቀበያው ጋ ሲደርስ ማግኔት ይፈጥርና በመቀበያው ላይ የተጠቀለለውን ወረቀት በመርፌ ይበሳሳል፡፡ የተበሳሳውንም ምሥጢራዊ ወረቀት በሚያነብ መሳሪያ ውስጥ እንዲያልፍ ሲደረግ የተላከውን መልዕክት ያትማል፡፡ በዚህ ዓይነት፣ ቴሌግራፍ በጣም በተራራቁ ቦታዎች መካከል መልዕክት በቀላሉ ማስተላለፍ አስቻለ፡፡

በ1830ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት በርካታ ሳይንቲስቶችና ዕቃ አዳሾች የቴሌግራፍ ናሙናዎች ሠርተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሳሙኤል ኤፍ.ቢ ሞርስ የተባለ አሜሪካዊ ሠዓሊና ቀራፂ፣ በ1843 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲ.ሲ እና በባልቲሞር-ሜሪላንድ መካከል የቴሌግራፍ መስመር ለመዘርጋት የአሜሪካ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግለት እስካሳመነበት ጊዜ ድረስ፣ ቴክኖሎጂው እውን አልሆነም፡፡

ሞርስ፣ በሽቦ የሚተላለፈው መልዕክት በየትኛውም የዓለም አካባቢ፣ ወጥ የሆነ ተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው የሚረዳና በአሁኑ ወቅት በስሙ የሚጠራውን ሥርዓተ-ነቁጥ የነጥቦችና የሰረዝ (ዶትስ ኤንድ ዳሽስ) ዘዴም ፈጥሯል፡፡ ከዋሽንግተን እስከ ባልቲሞር ያለው የቴሌግራፍ መስመር ዝርጋታ በ1844 ዓ.ም ሲጠናቀቅ ሞርስ “what hath God wrought” የሚሉትን ቃላት በታይፕ ጻፈ፡፡ ያ መልዕክት ወዲያውኑ በቅፅበት ማለት ይቻላል፣ 60ኪ.ሜ ያህል ርቀት ተጉዞ በተሳካ ሁኔታ በደረሰበት ወቅት የቴሌኮሙኒኬሽን አብዮት ተጀመረ፡፡

የመጀመሪያዎቹ የቴሌግራፍ ኦፕሬተሮች፣ የሞርስን ሰረዞችና ነጥቦች በድምፅ መለየት ስለቻሉ የኮዶቹን መጻፊያ ጥቅል ወረቀት መጠቀም ተው፡፡ ከ30 ዓመታት ጥቂት ዘግየት ብሎ፣ አሌክሳንደር ግራሃም ቤል፤ ቴሌግራፍን አሻሽሎ በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ የተለመደውን ቴሌፎን ይዞ ብቅ አለ፡፡ ከመቶ ዓመት በላይ የዘለቁ ማሻሻያዎች ኢንተርኔትን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸውን መገናኛዎች አስገኙ፡፡ በዚህ ዓይነት ቴሌግራፍ፣ ከየትኛውም ፈጠራ በበለጠ መልኩ፣ ዓለምን ወደ ትንሽ መንደርነት አጠበባት፡፡

ሽቦ አልባ መገናኛ፡- በ1000 ዓ.ም በዚች ዓለም የኖረ ሰው በተአምር ቆይቶ 2000 ዓ.ም ደረሰ እንበል- ለጨዋታ ያህል፡፡ ያ ሰው የቱንም ያህል ድንገተኛ አድናቆትና አክብሮት ወይም ፍርሃት ቢሰማውም፣ እስካሁን የተገለፁት በርካታ ፈጠራዎች የተፈለሰፉበትን መንገድና መመሪያ ወይም ብልሃት ሊገነዘብ ይችል ይሆናል፡፡

ነገር ግን ያለ አንዳች ሽቦ ወይም ምንም በማይታይ ማስተላለፊያ ዘዴ፤ ኢንፎርሜሽን በኅዋ ውስጥ የማሰራጨት ችሎታ፣ ምትሃታዊ መስሎ ሊታየው ይችላል፡፡ የዛሬዎቹ ዓለም ዓቀፍ ግንኙነቶች የሚተማመኑት በሽቦ ወይም በሌላ ዘዴ ሳይሆን ተከታታይነት ያላቸው የኤሌክትሪክ ወይም የራዲዮ ሞገዶች (ሲግናልስ) በኅዋ ውስጥ ረዥም ርቀት በመላክና በመቀበል ነው፡፡ ለበርካታ ሰዎች በተመሳሳይ ቅፅበት መልዕክት ማስተላለፍ (ብሮድካስቲንግ) የሚቻለው በራዲዮ ሞገዶች ብቻ ነው፡፡

የራዲዮ ሞገዶች ልክ እንደ ፀሐይ ብርሃን፣ ኢንፍራሬድ፣ አልትራቫዮሌትና እንደ ኤክስ-ሬይ ላይት ሁሉ የኤሌክትሪክና የማግኔት (ኤሌክትሮማግኔቲክ) ጨረሮች ናቸው፡፡ በ1889 ዓ.ም የታወቁትን የራዲዮ ጨረሮች በመፍጠር ለይቶ ያወቀውና የሚጓዙትም በብርሃን ፍጥነት መሆኑን ያረጋገጠው፣ ሄኒሪች ሄርዝ ነው፡፡ ዛሬ፤ ይህ ጀርመናዊ የፊዚክስ ባለሙያ፣ ለዚህ በጣም ጠቃሚና በሌሎች ግኝቶቹ ላበረከተው አስተዋጽኦ በአንድ ሰኮንድ የሚደረግ የአንድ ዙር የኤሌክትሪክ ሽክርክሪት፣ በስሙ ሄርዝ (Hz) በመባል ይታወቃሉ፡፡

የሄርዝን የቤተ-ሙከራ ምርምር ወደ ቴሌኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የለወጠው ኢጣሊያዊው ኢንጂነር ጉግሊለሞ ማርኮኒ ነው፡፡ በ1894 ዓ.ም ማርኮኒ፤ የሄርዝን ሥራ ከተገነዘበ በኋላ ለምን አገልግሎት ሊውል እንደሚችል ወዲያውኑ ተረዳ፡፡ ከዚያም በቀጣዩ ዓመት መጨረሻ፣ ማስተላለፊያና መቀበያ ሠርቶ በ 2ኪ.ሜ ተኩል ርቀት የራዲዮ መልዕክት (ሲግናል) አስተላለፈ፡፡ ማርኮኒ በ1901 ዓ.ም ቴክኖሎጂውን በማሻሻል የራዲዮ መልዕክቶችን ከአትላንቲክ ውቅያኖስ አሻግሮ ማስተላለፍ ቻለ፡፡

አብዛኛው ሰው በመጀመሪያ ስለ ራዲዮ ያወቀው ከእንቅልፉ በቀሰቀሰው አሳዛኝ መርዶ ነበር፡፡ ኤፕሪል 1912 ዓ.ም ቅንጡዋ ታይታኒክ ከግግር በረዶ ቋጥኝ ጋር ስትጋጭ መርከቧ በአዲሱ ቴክኖሎጂ የድረሱልኝ የጣር ጥሪ አስተላለፈች፡፡ በዚያ አሳዛኝና አስደንጋጭ አደጋ፣ ካሳፈረቻቸው 2,200 ሰዎች መካከል 700 ሰዎች ያህል ብቻ ናቸው የተረፉት፡፡ የዕርዳታውን ጥሪ ሰምተው ሌሎች መርከቦች ባይደርሱ ኖሮ፣ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በጣም ያነሰ ይሆን ነበር፡፡

መጀመሪያ አካባቢ ራዲዮ ይሠራ የነበረው እንደቴሌግራፍ የሞርስን የንዝረት ኮድ በመላክ ነበር - ያለ ምንም የሽቦ መስመር፡፡ ከዚያም ካናዳ የተወለደው አሜሪካዊ የፊዚክስ ባለሙያ ሬጂናልድ ፈሰንደን፤ የራዲዮ ሞገዶችን የሚያስተካክል (modulating) ዘዴ አበረከተ፡፡ በዚህ ዘዴ ነው እንግዲህ መጀመሪያ ድምፅን ቀጥሎ ደግሞ ምስልን በጥራት ማስተላለፍ የተቻለው፡፡ ፈሰንደን በ1906 ዓ.ም የመጀመሪያውን የራዲዮ ስርጭት አደረገ፡፡ የመጀመሪያው የቴሌቪዥን መቀበያ የተሞከረው ደግሞ በ1928 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚህና በሌሎች በርካታ መንገዶች ሽቦ አልባ የመገናኛ ቴክኖሎጂ፤ ዜናና መረጃዎች በመላው ዓለም እየተሰራጩ፣ ከፋሽን ትርኢት እስከ ፖለቲካ ሹም ሽር ያሉ ጉዳዮችን ከአንዱ ጫፍ ወደሌላው በማድረስ ዓለምን እየለወጣት ነው፡፡

ፀረ-ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ)፡- በአብዛኛው የሰው ልጅ ታሪክ ተላላፊ በሽታዎች ሳያሰልሱ ሕዝቦችን በጭካኔ ገድለዋል፤ ፈጅተዋል፡፡ በቅርቡ እንኳ ከ1914 እስከ 1918 ዓ.ም በተደረገው አንደኛው የዓለም ጦርነት አብዛኛው የጦር ሜዳ አሰቃቂ እልቂት በጥይት ሳይሆን በተላላፊ በሽታዎች የተፈጠረ ነው፡፡ ሐኪሞች፤ ኮሌራ፣ የሳንባ ምች፣ መንጋጋ ቆልፍ፣ ጨብጥ፣ ቲ.ቢ ወይም ማንኛውንም ዓይነት ገዳይ በሽታ ለመዋጋት የነበራቸው መሳሪያ በጣም ጥቂት ነበር፡፡

በ1896 ዓ.ም ፈረንሳዊው የሕክምና ተማሪ ኤርነስት ዱቼ፤ ሳያስበው በድንገት ባክቴሪያ የመሰለ ሻጋታ አገኘ፡፡ ይሁን እንጂ የግኝቱ ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ከዚያም በ1928 ዓ.ም የስኮትላንዱ ተመራማሪ አሌክሳንደር ፍሌሚንግ፤ በባክቴሪያ ማራቢያ ሳህን ውስጥ የነበረ አንድ የማይታወቅ የሻጋታ ዝርያ፣ የባክቴሪያዎችን ዕድገት እንደሚያቆም አስተዋለ፡፡ ያ ሻጋታ፣ ከፔኒሲሊየም ቤተሰቦች የመጣ መሆኑን ስለተገነዘበ፣ ፔኒሲሊን በማለት ጠራው፡፡

የፍሌሚንግ የምርምር ውጤት፣ ምናልባትም ፈጠራ ከማለት ግኝት ቢባል ይሻላል፡፡ ምክንያቱም የእሱ ፔኒሲሊን ያልተረጋጋ ከመሆኑም በላይ ለማጣራትም አስቸጋሪ ነበር፡፡ የኬሚስትሪ ባለሙያ የሆኑት ኤርነስት ቼይን እና ሄዋርድ ፍሎረይ በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ቀጣይ ሥራ፣ በትልቅ ጋን በተጠራቀመ ፈሳሽ ውስጥ ሻጋታውን የሚያሳድጉበት ዘዴ አገኙ፡፡

በ1941 ዓ.ም መጨረሻ፣ ፔኒሲሊን በብዛት የሚመረትበትን ዘዴ ለማግኘት፣ በአሜሪካ መንግሥት በኢንዱስትሪና በትምህርት ተቋማት መካከል ትብብር በስፋት ተጠናከረ፡፡ በ1944 ዓ.ም መድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተባበረው ኃይል (Allied force) ጁን 6 ቀን 1944 ዓ.ም አውሮፓን በወረረበት የኖርማንዲ ዲ.ደይ ጦርነት የቆሰሉ ወታደሮችን ሁሉ ማከም ያስቻለ በቂ ፔኒሲሊን ማምረት ችለዋል፡፡

የፔኒሲሊን መመረትና በቀጣይም የሌሎች በርካታ ፀረ-ተህዋስያን መፈጠር በሕክምና ታሪክ ከምንም የበለጠ ለሰው ልጅ ጤና የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበሩት ጥቂት አስርት ዓመታት በአንድ ወቅት፤ እጅግ አደገኛ ወይም ሕይወት ቀጣፊ የነበሩትን ሁሉንም የበሽታ ዓይነቶች በሕክምና ማዳን ተቻለ፡፡ የፀረ-ተህዋስያን ዕድገት የሰው ልጅ፣ ከበሽታ ስቃይ ራሱን የሚከላከልበት እጅግ ጠቃሚ ጋሻ ሆነው፡፡

ትራንዚስተር፡- የእንፋሎት ሞተር የ18ኛና የ19ኛ ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮትን እንዳቀጣጠለው ሁሉ፣ ትራንዚስተር ደግሞ የ20ኛውን ክፍለ ዘመን አጋማሽ የኢንፎርሜሽን አብዮት አንቦገቦገው፡፡ በአብዛኛው ሁሉም ማለት ይቻላል፤ ኢንፎርሜሽን የሚያከማች፣ የሚያስተላልፍ፣ የሚያሳይ ወይም የሚቆጣጠር ትንሽ መሳሪያ በእምብርቱ ኤሌክትሪክ በሚተላለፍበት መስመር የተሞላ የሲልከን ቺፕ (chip) አለው፡፡ እነዚህ ቺፕሶች እያንዳንዳቸው በሺዎች ወይም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብዙ ትራንዚስተሮች ይዘዋል፡፡

የትራንዚስተር አሠራር በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም፡፡  በሙያው አካባቢ ላለ ሰው እንጂ ለሌላው ውስብስብ ስለሆነ ወደ ዝርዝር ጉዳይ አላመራም፡፡ ነገር ግን የትራንዚስተርን መሠረታዊ አሠራር በቀላሉ ለማስረዳት ያህል፣ መሳሪያው፣ ትንሽ ኤሌክትሪካዊ ኃይል (ቮልቴጅ) የኤሌክትሪክ ሞገድ ፍሰትን (እንቅስቃሴ) እንዲቆጣጠር ያደርጋል፡፡

በኮምፒዩተር ውስጥ ትራንዚስተሮች በጣም ፈጣንና በጣም ትንሽ ማብሪያና ማጥፊያ ሆነው ነው የሚያገለግሉት፡፡ ኮምፒዩተር የሰዎች ቋንቋ አያውቅም፤ ፊደልም አያነብም፡፡ ቋንቋው፣ ባይነሪ ዲጂታል የተባሉት 1 እና 0 ናቸው፡፡ ኮምፒዩተሩ ጽሑፍ ወይም የሙዚቃ ኖታ ወይም የፎቶግራፍ ቀለም፣ … እንዲሠራ ሲታዘዝ ትራንዚስተሮች (ማብሪያና ማጥፊያው) ትዕዛዙን ወደ 1 እና 0 ቀይረው (ተርጉመው) ይነግሩታል፡፡ ኮምፒዩተሩም ፕሮሰስ አድርጐ ውጤቱን በቋንቋው ይሰጣል፡፡ ከዚያም ትራንዚስተሮች በ1 እና በ0 የተሰጠውን ምላሽ በተጠየቀው መንገድ ተርጉመው ያቀርባሉ፡፡ እጅግ በርካታና የተለያዩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረታዊ ወደ ሆነ ኮድ (1 እና 0) የማሳጠር ችሎታ ነው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲያብብ እንዲመነደግ ያደረገው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ፣ የትራንዚስተር ተግባር፣ ቀደም ሲል የቫኪዩም ቲዩብ ቴክኖሎጂ ይሠራ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ቲዩቦቹ የኤሌክትሪክ ሞገድን እንቅስቃሴና ኮምፒዩተሩ የሚጠቀምበትን የ1 እና 0 ኮዶች የሚቆጣጠር ትንሽ የውስጥ ኤሌክትሪክ ኃይል (ቮልቴጅ) አላቸው፡፡ ነገር ግን በየጊዜው የሚበላሸውንና የማያስተማምነውን ግዙፉን ቫኪዩም ቲዩብ የተካው ትራንዚስተር ባይፈጠር ኖሮ የኮምፒዩተር አብዮት የትም አይደርስም ነበር፡፡

የመጀመሪያ ምዕራፍ ኮምፒዩተሮች፣ እንደ ዛሬዎቹ ቀላልና ትንሽ አልነበሩም፡፡ 30 ቶንስ (3000 ኪ.ግ) የሚመዝኑና 19ሺ ቫኪዩም ቲዩቦች የሚጠቀሙ ነበር፡፡ ለምሳሌ በ1946 ዓ.ም የቀረበው ኤሌክትሮኒክ ኑሚሪካል ኢንተግሬተር ኤንድ ኮምፒዩተር በመባል የሚታወቀው (ኢ.ኤን አይ ኤ ሲ) ኮምፕዩተር ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ከመፈለጉም በላይ፣ ቲዩቦቹ በየጊዜው ይበላሹ ወይም ይቃጠሉ ነበር፡፡ ትራንዚስተር፣ በፊዚክስ ባለሙያዎቹ ጆን ባርደን፣ ዋልተር ብራቴይንና ዊሊያም ሾክሊይ የቡድን መሪነት፣ በ1948 ዓ.ም በቤል ቤተ-ሙከራዎች ተፈጠረ፡፡ መጀመሪያ ላይ ይህ ትንሽ መሳሪያ፣ሊጠቅም ይችላል ተብለው ከተገመቱት ዕቃዎች ዝርዝር ውስጥ ኮምፒዩተር አልነበረም፡፡ ይህ ምንም አያስደንቅም፡፡ ምክንያቱም ኮምፒዩተር በ1940ዎቹና በ1950ዎቹ ዓመት ሲሠራ በጥቂት አሥርት ዓመታት ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ ባለ የሰው ልጅ ሕይወት የሚሰራጭ የቴክኖሎጂ ፍሬ (ዘር) በውስጡ እንዳለ ያዩ ሳይንቲስቶች ጥቂት ነበሩ፡፡ ዲጂታል ቴክኖሎጂ በመላው ዓለም ከመስፋፋቱ በፊት እንደ ራዲዮና ስቴሪዮ ላሉ ሲስተሞች መሻሻል ትራንዚስተር በጣም ጠቃሚ መሳሪያ ነበር፡፡

ነገር ግን፣ ትራንዚስተር፣ ኮምፒዩተር ውስጥ ሲደረግ ለቴክኖሎጂው መስፋፋት ዋነኛው አካል ሆነ፡፡ እንዲሁም ከፊል ኤሌክትሪክ አስተላለፊ የሆነ የብር ቅብ የሲልከን ቺፕሶች በብዛትና በሚሊዮኖች ማምረት ተቻለ፡፡ እነዚህምና ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትራንዚስተሮች ከቺፕስ ጋር መዋሃድ ነው የኢንፎርሜሽን ዘመን ዕድገትን ያቀጣጠለው፡፡

ዛሬ፣እነዚህ ቺፕሶች የኮምፒዩተር አካል ብቻ አይደሉም፡፡ እንደ ቪዲዮ ካሜራ፣ ሞባይል ስልክ፣ ፎቶኮፒ መሳሪያዎች፣ ጃንቦ ጄቶች፣ ዘመናዊ  አውቶሞቢሎችና ቪድዮ ጌሞች ለመሳሰሉ በርካታ መሳሪያዎችም በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡ ያለ ትራንዚስተር ኢንተርኔት የለም፤ የጠፈር ጉዞም አይኖርም ነበር፡፡ ትራንዚስተር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ፈትል ውስጥ በጥልቀት የተቀበረ ዘር ነው፡፡ መጪውን ዘመን መፍጠር፡- ያለፈው ሺህ ዓመት ያመጣውን ለውጥ ከዛሬው ጋር ማነፃፀር ባይቻልም 1000 ዓ.ም እጅግ ኋላ-ቀርና የተለየ ዘመን ነበር፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች የሕይወት ዘመናቸውን የሚያሳልፉት ከተወለዱበት ስፍራ ጥቂት ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነበር፡፡ ኮሙኒኬሽን በጥቂት መንደሮች ዙሪያና አልፎ-አልፎ በዚያ በሚያልፉ ሰዎች ዘንድ ብቻ የተገደበ ነበር፡፡ በሽታዎች ብዙ ጊዜ ምንም መከላከያ በሌለው ሕዝብ ላይ አስከፊና ተደጋጋሚ ጉዳት ያደርሱ ነበር፡፡ ከጥቂት ቄሶችና ምሁራን በስተቀር ሕዝቡ ማሃይም፣ የሚነበበውም ነገር በጣም ጥቂት ነበር፡፡ ከሺህ ዓመት በፊት የነበሩ ሰዎች ጊዜን የሚለኩት በፀሐይና በጨረቃ ነበር፡፡ ሳይንሳዊ እይታና ግንዛቤ (ያለ ቴሌስኮፕ ማይክሮስኮፕ)  በባዶ ዓይን ላይ ብቻ የተገደበ ነበር፡፡

ዛሬ፣ ለሚሌኒየሙ ሳይንሳዊ ፈጠራዎችና ግኝቶች ምሥጋና ይግባና የሰዎች ሕይወት ተለውጧል፡፡ ከዓለም አጋማሽ ወዲያ የተከሰቱ ድርጊቶች እየተከናወኑ ባለበት ቅፅበት ማየት ይቻላል፡፡ ውጭ አገር ካለ ጓደኛ ወይም ዘመድ ጋር ስልክ ብድግ አድርጐ በሰኮንዶች ውስጥ መነጋገር እውን ሆኗል፡፡ ከመኪና አስከ ጄት ያሉ የሞተር ትራንስፖርቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰዎችን ረዥም ርቀት እያጓጓዙ ነው፡፡ ኤሌክትሪሲቲ እጅግ በርካታ ጉልበት ቆጣቢና የመዝናኛ መሳሪያዎችን እያንቀሳቀሰ ነው፡፡ ጋዜጦችና መጻሕፍት በርካሽ ዋጋ ከመሸጣቸው በላይ አቅርቦታቸው አስተማማኝ ነው፡፡ የሕክምና ሳይንስ የበርካታ በሽታዎችን መንስኤና ሕክምና በማወቁ የሰዎች በሕይወት የመኖር ዕድሜ ጨምሯል፡፡

ለሥራ፣ ለፈጠራና ለኮሙኒኬሽን ሁነኛ መሳሪያ አለ - ኮምፒዩተር፡፡ ይህ የታላላቅ ጠቃሚ መሳሪያዎች ፈጠራ በቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡ በስፋት ያየን እንደሆን የሰው ልጅ ባለፈው 1000 ዓመት ሌሎች እጅግ በርካታ ጠቃሚ ነገሮችንም ፈጥሯል፡፡ አንዱ ዘመናዊ ዲሞክራሲ ነው - ከመሠረታዊ የሰው ልጅ መብቶች ጋር፡፡ ሌላው የሲንፎኒ ሙዚቃ ቅንብር ነው፡፡ የቤዝ ቦል ወይም የእግር ኳስ ጨዋታ (ሶኮር)  ሌላው ሊሆን ይችላል፡፡ ያለፈው 20ኛ ክፍለ ዘመን የፈጠራ ውጤቶች ከሳይንስና ከኢንጂነሪንግ በተጨማሪ፣ በየራሳቸው ታላላቅ የሆኑ የዕድገትና የፈጠራ መስኮች እጅግ በርካታ ናቸው፡

 

 

Read 12915 times Last modified on Friday, 06 January 2012 11:53

Latest from