Saturday, 20 December 2014 12:49

ለአዕምሮአዊ ንብረት ጥበቃ በ40 ሚ.ብር ዘመናዊ አሰራር ተዘረጋ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በንግድ ምልክት፣ በአዕምሮ ፈጠራና በዲዛይን (ንድፍ) ላይ ጥበቃ ለማድረግ በዓለም አቀፉ የአዕምሮ ንብረት ድርጅት (World Intellectual Property Organization) WIPO ትብብር አዲስ የዲጂታል አሰራር መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም በማኑዋል የአዕምሮ ንብረቶችን ይመዘግብና ይቀበል የነበረው መስሪያ ቤቱ፤ ከተባበሩት መንግስታት ስፔሻላይዝድ ድርጅቶች አንዱ በሆነው “ዋይፖ” በተደረገለት ድጋፍ በ2.ሚሊዮን ዶላር የተገዙ ሶፍትዌሮችን፣ ሰርቨሮችን፣ ኮምፒዩተሮችንና ፕሪንተሮችን በማስገባት Intellectual Property Automation System (IPAS) ሲስተምን ይፋ አድርጓል፡፡ በእለቱ የዋይፖ ተወካዮች በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በመገኘት የዘረጉትን ሲስተም ለጋዜጠኞችና ለጽ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች አስጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር ናፍቆት ዮሴፍ፤ በተዘረጋው ሲስተም፣ በጠቀሜታውና በዋይፖ ትብብር ዙሪያ ከጽ/ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

       የተዘረጋው አውቶሜሽን ሲስተም ጠቀሜታው ምንድን ነው?
እንግዲህ የዚህ ሲስተም በአገራችን መዘርጋት ጠቀሜታው በርካታ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው በአዕምሮ ፈጠራ (ፓተንት)፣ በንግድ ምልክትና በዲዛይን (ንድፍ) ባለቤትነት  ጥበቃ ላይ አስተማማኝና ዘለቄታ ያለው ስራን ለመስራት ያስችላል፡፡
 ይህ ሲባል እስከዛሬ አመልካቾች በወረቀት ይዘው የሚመጡት የባለቤትነት ጥያቄ አንድ ጊዜ በዚህ ሲስተም ውስጥ ከገባ ካልተፈለገ የይገባኛል ጥያቄዎች፣ ከመጥፋት ጭቅጭቅና ከመሰል ጉዳዮች ተጠብቆ ይቀመጣል፡፡
ሁለተኛ አመልካቾችን ከጊዜ ብክነትና ከመጉላላት ይጠብቃል፡፡ ባሉበት ሆነው ጉዳያቸውን መከታተል እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ማለት ነው፡፡ አንድ አመልካች ፈጠራውን፣ የንግድ ምልክቱን ወይም ዲዛይኑን ይዞ ሲመጣ ኮድ ይሰጠዋል፤ ፋይል ይከፈትና የፋይሉ ቁጥር ሲስተሙ ውስጥ ይመዘገባል፡፡ ሌላ ጊዜ ሲፈለግ ኮዱን ኮምፒዩተሩ ላይ አስገብቶ  በፍጥነት ለማግኘት ያስችላል፡፡ ይህ ቀልጣፋ አሰራርን ይፈጥራል፡፡ ባለንብረትነትን ያረጋግጣል፡፡ አንድ ምርትም በፓተንት፣ በንግድ ምልክትና በዲዛይን ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ጥቅሞቹ ናቸው፡
ይህን ሲስተም ለመዘርጋትና ስራ ላይ ለማዋል የዓለም አዕምሮ ንብረት ድርጅት “WIPO” ወደ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉ፣ ሰራተኞቹን በራሱ ወጪ እዚህ ድረስ መላኩና ሲስተሙን መዘርጋቱ ተገልጿል፡፡ ይህን ድጋፍ ያደረገው ለምንድን ነው?
የዓለም የአዕምሮ ንብረት ድርጅት ከUN ስፔሸላይዝድ ድርጅቶች አንዱና በአዕምሮ ንብረት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ያደረገው ይህ ድርጅት፤ በ60 የዓለም አገራትና በ20 የአፍሪካ አገራት ይሰራል፡፡ ድርጅቱ ከሚሰራባቸው የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ድርጅቱ ሰራተኞቹን ሲልክ ይህ ሶስተኛ ጊዜው ነው፡፡
 ድርጅቱ በተለይ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን ለማገዝ በያዘው ፕሮጀክት፣ ታዳጊ አገሮችን አግዘን የአዕምሮ ንብረት ጥበቃቸውን ማጠናከር አለባቸው ብሎ በማመኑ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ በዚህ መሰረት ሰራተኞችን ወደዚህ ሲልክ፣ የአውሮፕላን ትኬት፣ ሆቴል… ሁሉን ነገር ችሎ ነው፤ ከእኛ የሚጠበቅ ነገር የለም፡፡
በማንኛውም ጊዜ ድጋፍ ስንጠይቅ ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ይህ የድጋፋቸው አንዱ ክፍል ነው፡፡
ሲስተሙን ለመጫን የሚያስፈልጉ ከላይ የጠቀስሻቸውን ንብረቶች ለመግዛት ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርገዋል፡፡ በቀጣይ የቅጅ መብት ላይ ለምንሰራውም ድጋፍ ለማድረግ ሌላ ፕሮጀክት አላቸው፡
ከዚህ በፊት ምን ምን ድጋፎችን አድርገዋል?
እስካሁን ብዙ ፕሮጀክቶችን ሰጥተውናል፡፡ ለምሳሌ የብሔራዊ አዕምሮ ንብረት ፖሊሲ ድራፍት ይደረግ ብለን ጠይቀናቸው፣ አማካሪ በመቅጠር ድጋፍ ስለሰጡን አሁን ድራፍቱ አልቋል፡፡ እስካሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ይህ ፖሊሲ የለም ነበር፤ ሁለት አማካሪ በመቅጠር ጥናቱን ጨርሰዋል፡፡
 በሚቀጥለው ጥር መጨረሻ ላይ ለውይይት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሌላው የአዕምሮ ንብረት አካዳሚ (If Academy) ነው፡፡ ይህንንም ፕሮጀክት ቀርፀን አቅርበን ፈቅደውልናል፡፡ ይህ አካዳሚ በቅርቡ ስልጠናና የማስተርስ ስራ ይጀምራል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የቅጅ መብትን አስመልክቶ የፊልም፣ የሙዚቃና የድርሰት ኢንዱስትሪው እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው እየጠቀመ ያለው ምን ያህል ነው የሚለውን እንዲጠናልን ጠይቀናቸው 70 ሺህ ዶላር አውጥተው አማካሪ ቀጥረውልን እየተጠና ነው፡፡ ጥናቱም የመጨረሻ ሪፖርት ላይ ደርሷል፡፡ እናም ድጋፍ በጠየቅን ቁጥር ፕሮጀክቶችን ይሰጣሉ፡፡ በተለይ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን በጣም ነው የሚያግዙት፡፡
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ተወካዮቹን ሲልክ ለሶስተኛ ጊዜ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት የመጡባቸው ሁለት ምክንያቶች ምን ምን ነበሩ፤ የአሁኑ አመጣጣቸውስ በዋናነት ምን ላይ ያተኩራል?
ከዚህ በፊት ይህንኑ ሲስተም በተመለከተ ስራዎች ነበሯቸው፡፡ አሁን ግን ሶፍትዌሩን ጭነው ባለሙያዎች አሰልጥነውና አስፈላጊውን ነገር አሟልተው፣ ሲሰሙ ስራ ላይ መሆኑን ይፋ ያደረጉበት የመጨረሻ ቀን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የአዕምሮ ፈጠራ የንግድ ምልክትና የዲዛይን ባለቤቶች ሲያመለክቱ፣ በዚህ ሲስተም ነው የሚስተናገዱት ማለት ነው፡፡ በወረቀት የምንቀበልበት አሰራር አብቅቷል፡፡ ይህ አሰራር የመጨረሻ ተጠቃሚ የሚያደርገውም ባለንብረቱን ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ፋይል እየጠፋና እየተበላሸ መጉላላቶች ይደርሱ ነበር፡፡ አሁን ግን የወረቀት ምልልስ ቀርቶ አውቶሜትድ ሲስተም ስለምንጠቀም፣ ከሁሉም አቅጣጫ ጠቀሜታው የጎላ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ሲስተሙ ሌላ ክልል አለ ወይስ እዚሁ ዋናው ጽ/ቤት ብቻ ነው?
እዚህ  ዋናው ጽ/ቤት ነው ሲስተሙ ያለው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራው እዚሁ ነው፤ ነገር ግን አሁን አሰራሩ ኤሌክትሮኒክ ስለሆነ የትኛውም አመልካች የአዕምሮ ፈጠራውን፣ የንግድ ምልክቱንና ዲዛይኑን (ንድፉን) ካለበት ሆኖ በኤሌክትሮኒክ ሲስተም መላክና መመዝገብ እንዲሁም መከታተል ይቻላል፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በክልል ከፍቶ ለመንቀሳቀስ የታሰበ ነገር አለ?
በቅርቡ በክልሎች ቅርንጫፎችን ለመክፈት ሃሳብ አለን፡፡ አማራና ደቡብ ክልሎችን መርጠናል፡፡ ሌላው አካባቢም በሂደት ለመክፈት ሃሳብ አለ፡፡
ሁለቱ ክልሎች ቅድሚያ ያገኙበት ምክንያት ምንድን ነው?
ሁለቱን ከሌሎች በቅድሚያ የመረጥንበት ምክንያት የሚይዙትን የአካባቢ ስፋት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
ለምሳሌ አማራ ክልልን ብትወስጂ አብዛኛውን የሰሜኑን ክፍል፤ እነ ትግራይን፣ ከፊል ቤኒሻንጉልንና ከአፋርም የተወሰነውን ክፍል ይዞ  እንዲሰራ በማሰብ ነው፡፡ የደቡቡ ደግሞ የደቡብን አካባቢ አጠቃልሎ እስከ ድሬደዋ ወደ ምዕራብ ጭምር ተንቀሳቀሶ እንዲሰራ ታስቦ ነው፡፡ ለወደፊቱ ግን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹን ወደ አራት ከፍ ለማድረግና ስራችንን የበለጠ ለማቀላጠፍ እቅድ አለን፡፡
የቅጅ መብትን በተመለከተ ከዓለም አቀፍ የአዕምሮ ንብረት ድርጅት ጋር ልትሰሩ ያሰባችሁት ምንድን ነው?
ቅድም እንደገለፅኩት የቅጅ መብት አዋጅ በቅርቡ ፀድቋል፡፡ ይህ አዋጅ ባለ መብቶችን ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ እንግዲህ አዋጁን ተከትለን የቅጅ ባለመብቱን ጥቅም ለማስከበር በምን መልኩ ይሰራ የሚለውን የሲስተምና መሰል ድጋፎች ከዋይፖ ጠይቀናል፡፡
እነሱም ፕሮጀክቱን ፈቅደዋል፡፡ የሚሰሩት ስራዎች ወደፊት በሂደት በግልፅ  የሚታዩ ይሆናሉ፡፡ ዋናው ነገር እነሱ አሁንም በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ለመርዳት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው ነው፡፡

Read 2298 times