Saturday, 20 December 2014 12:31

‘እኛና ካሜራ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ይሄ ‘ፎርቹን’ የሚባለው የዓለም ሀብታሞችና ታዋቂዎችን የሚያወጣው መጽሔት …ምነው እኛን ረሳንሳ! ነው…ወይስ ይህቺም ቁም ነገር ሆና ‘ተመቀኙን’ አሀ…የ‘ሴሌብሪቲ’ አገር ሆነናላ! ከሲቪል ሰርቫንቱ ይልቅ ታዋቂው በቁጥር ባይበዛ ነው! የምር እኮ…እንደ ዘንድሮ ‘ሴሌብሪቲ’ የመሆን ዕድል በቀላሉ የሚገኝበት ኖሮም አያውቅም፡፡ ልጄ የጨዋታውን ህግ አውቆ መሮጥ ነው…ወይ ‘ሲንግል’ መልቀቅ፣ ወይ የሆነ ፊልም ላይ ‘ብልጭ’ ብሎ መጥፋት፣ ወይ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ’ ነዋሪ መሆን! በኋላ…“ተጠራሩብኝ…” “ባቡሩ አመለጠኝ” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡
እኔ የምለው እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በድሮ ጊዜ ፊውዳል፣ ወዛደር ምናምን የሚባሉ የመደብ ክፍልፍሎች ነበሩ፣፡፣ እንክት አድርጌ ነዋ ‘ድሮ’ የምለው! ነገርዬው እኮ የሌኒን ሀውልት ከተገነደሰ በኋላ አብቅቶለታል! ታዲያ የሌኒን ሀውልት ከተገነደሰ ‘ድሮ’ ሆነ አይደል!  (ቂ…ቂ…ቂ…) በነገራችን ላይ እሱ ሰውዬ ወዛደሮቹ… “አንተ ሁልጊዜ ሽክ እንዳልክ ነው…” ምናምን ብለው ሲያጉረመርሙ… “የምታገለው እኔ ወደ እናንተ ለመውረድ ሳይሆን እናንተን ወደ እኔ ለማምጣት ነው…” አለ የተባለችው ነገር ልክ ለዘንድሮ ዘመናችን በእውቅ ሰፊ በልክ የተሰፋች አትመስልም! ልክ ነዋ…ይኸው ስንቱ ሽክ፣ ቂቅ ያለ አይደል እንዴ ስለ እኛ ቺስታነት የሚያወራው! ከሌኒን ዘመን የሚለየው እኛም… “አንተ ሽክ ብለህ…” ምናምን አለማለታችን፣ እነሱም… “እኔ የምታገለው እናንተን ወደ እኔ ለማምጣት ነው… አለማለታቸው፡፡ (አንዲት ካሬ ሜትር ሦስት መቶ ምናምን ሺህ ገባች በሚባልበት ዘመን!) የምር አንዳንዴ… “እውነት እንደሚሉን ‘ስትሬንጅ’ ሰዎች ነን እንዴ!” አያሰኛችሁም! የምር ግን… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…መሬት በእንዲህ አይነት ዋጋ መግዛት የሚችሉ ብዙ ሰዎች ካሉ… አለ አይደል… ያ ‘ፎርቹን’ የተባለ መጽሔት በእኛ ‘ዓይኖቹ ቀልተዋል’ ማለት ነው፡፡ የሆነ መሥሪያ ቤት እኮ አምስት መቶ ካሬ ሜትር ምናምን መግዛት ከፈለገ ሠራተኞቹን ለአንድ ዓመት ያለ ደሞዝ የግዳጅ እረፍት ማስወጣት አለበት፡፡ አሀ…ታዲያ ምን ይቀልባቸው! ከጥቂት ዓመታት በፊት… “አንድ ካሬ ሜትር ሦስት ሺህ ብር አወጣ!” ተብሎ ሰበር ዜና በነበረበት አገር…እዚሀ ሲደረስ… “ይሁን ብለን ዝም አልን…” አይነት ነገር ከማለት በቀር ምን ማለት ይቻላል!  ስሙኝማ…ከተጫወትን አይቀር… ወይ ዜና፣ ወይ ልዩ ፕሮግራም ምናምን ነገር ላይ…“በካሬ ሜትር ከፍተኛ የሊዝ ዋጋ በማስከፈል አገራችን ከዓለም ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች…” ምናምን የሚባል ነገር እንዳንሰማ ነው፡፡ እናላችሁ…በሆነ ነገር ‘ሴሌብሪቲ’ ምናምን ነገር ለመሆን አሁን አሪፍ ጊዜ ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙ ዓመት በትዳር በመቆየት አይነት ነገር ‘ሴሌብሪቲ’ መሆን ይቻላል፡፡ እድሜ ለካሜራ! ጉድ የሚመጣው ካሜራ ፊት ሲኮን ነው፡፡ ካሜራው ተደቅኗል፡፡ ሁለቱ በአገር ልብስ ተንቆጥቁጠው ተኮፈሰዋል፡፡
“ራሳችሁን ብታስተዋውቁን…” ይላል ‘ጥያቄ መጠየቅ’ ሥራው የሆነው ጋዜጠኛ፡፡ (ስሙኛማ…እግረ መንገዴን ትዝ ባለኝ ቁጥር የማነሳው ነገር ነው…“ሪፖርተራችን በቀደም በእንትን ማራቶን ሦስተኛ ከወጣው እከሌ እከሌ ከተባለ አትሌት ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ተከታተሉ…” ይባልና እኛም “በእጄ… እንላለን፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው መጀመሪያ ምን ብሎ ‘ይጠይቀዋል’ መሰላችሁ …“ስምህን ብታስተዋውቀን…” እንዴት ነው ነገሩ! ቀጥሎ የሚመጣው ‘ጥያቄ’ ምን መሰላችሁ ….‘በበቀደሙ የእንትን ማራቶን ስንተኛ ነው የወጣኸው…?” ኧረ ልብ ይባል! እናላችሁ…እነሱ ራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ አባወራው ይናገራሉ፡፡ “ይኸው በትዳር ስንኖር ሀያ ስምንት ዓመት ሞላን፡፡ በመሀላችን አንዲትም ቀን ኮሽታ ተሰምቶ አያውቅም…” ምናምን ይላሉ፡. የቲቪ ካሜራ ተደቅኗላ! ሴትዮዋ ደግሞ…“እሱ ሥራውን ጨረሰ ሮጦ ወደ ቤቱ ነው፡፡ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ እየተባባልን ነው የኖርነው፡፡”
ካሜራ ፊት ለፊት ተደቅኗላ!
ይሄን ጉድ የአንዳቸው የነፍስ አባት ቢሰሙ እኮ በትንታ አንድ ነገር ሆነው ‘ለሰው ጦስ’ ይሆኑ ነበር፡፡ ሁለቱ በተጣሉ ቁጥር ማስታረቁና መገዘቱ ቢሰለቻቸው እኮ…አለ አይደል…ከአንዴም ሁለቴ… “አምላኬ እንደው ምን ብበደልህ ነው እነኚህን ጉዶች አምጥተህ እላዬ ላይ የጣልክብኝ!”…ምናምን ብለው አቤቱታ አቅርበዋል፡፡፡  የሰፈሩ ዕድርማ ተሰፋ ከቆረጠ ከረመ፡፡ እንደውም ዋና ጸሀፊው ከሁለት አንዳቸውን መንገድ ላይ ባዩ ቁጥር ፊት ለፊት ላለመገናኘት ወደ ማዶ ሲሻገሩ የስንት ሚኒባስ ጥሩምባ አስደንግጧቸዋል፡፡ እናላችሁ…ሁለቱም አላጠፉም…
ካሜራ ፊት ለፊት ተደቅኗላ!
የምር ግን እኔ አሁን፣ አሁን ምን እል መሰላችሁ (ባልልም እንዳልኩ ቁጠሩት)… “ይቺ አገር እንዲህ የበዙ በፍቅሯ አንጎላቸው ዞሮ ቃላት የሚያጥራቸው ዜጎች አሏት እንዴ!” እላለሁ፡፡ አንዳንዴ እኮ “ይሄ ነገር ከልብ የሆነ ነገር ነው…ወይስ ስለ ‘አጤ እከሌ’ የሚሠራ ፊልም ልምምድ ነው!” ብሎ ግራ የሚገባው ሊኖር ይችላል፡፡ እንደውም…አንዳንዴ ለማን ታዝናለህ አትሉኝም… ቃለ መጠይቅ ለሚያደርጉት ጋዜጠኞች! የእንጀራ ነገር ሆኖባቸው ነዋ! አለ አይደል…“የአገሬን ነገር ሳስብ ሳምንት እንቅልፍ አይወስደኝም…” የሚመስል ነገር የሚናገር አርቲስት፣ ወይም ሌላ አይነት ‘ሴሌብሪቲ’ ሲገጥማቸው በሆዳቸው “አሁንስ አልበዛም እንዴ! ከዚህ አይነት እንጀራ ለምን በቆሎ ብቻ እየቆረጠምኩ አልኖርም! እነ ዶስቶቭስኪ በህይወት ቢኖሩ ይቀኑባቸው ነበር፡፡ እነሱ እንዲህ ‘ፊክሺን’ ፈጥረው አያውቁማ!” ምናምን ሳይሉ አይቀርም፡፡
እናላችሁ…በ‘ሴሌብሪቲነት’ ካሜራ ፊታችሁ ሲደቀን አስቸጋሪ ነው፡፡ እኛ፣ እኛ እንኳን ‘ሴሌብሪቲም’… ‘ፎቶጄኒክም’ ስላልሆንን እንኳን ሊቀርጹን ለመብራት ያዥነት አያስቡንም፡፡ (እነ እንትና ለካሜራ አለመመቸት ጥቅሙን አያችሁት አይደል!) እናላችሁ…ካሜራ ፊት ለፊት ሲደቀን ካሜራ ሲደገን… አለ አይደል…‘ተፋቅን’ ማለት ነው.፡ ልክ ነዋ… በየድራፍቱ ላይ…“ምን አለ በሉኝ ይቺ አገር ልክ በላጲስ እንደጠፋ ጽሁፍ እልም ባትል…” ምናምን እያለ የሆነ ‘ሊበራሊዝም’ ምናምን ነገር ሲለን የነበረው ‘አክቲቪስት’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ልክ ካሜራ ፊቱ ሲደቀን ምን ይል መሰላችሁ… “እውነቱን ለመናገር አሁን ሲንጋፖር፣ ዱባይ እያልን የምናደንቀው በአሥር ዓመት ውስጥ ይቺ አገር ሁሉንም ባታስከነዳ! ምን አለ በሉኝ፤ ዓለም ሁሉ ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ አገራችን ባይጎርፍ…” ይላል፡፡
ካሜራ ፊት ለፊት ተደቅኗላ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ካሜራ ፊት ለፊት ሲደቀን ‘መከራቸውን ከሚበሉት’ የንግግር ክፍሎች አንዱ ምን መሰላችሁ…ቅጽል! ምን አለፋችሁ…ከንግግሮቹ መሀል ቅጽሎቹ ተለቅመው ቢወጡ የሃያ አምስት ደቂቃ ቴፕ ወደ አምስት ደቂቃ ይወርዳል፡፡ እጅግ…እጅግ… ምናምን የሚለው ይበዛና ጋዜጠኛም አሳጥሮ የሚለው ነገር ግራ ይገባዋል፡፡ “አስተያየት ሰጪው የነገሩን ክብደት ለመገንዘባቸው ‘እጅግ’ ለሚለው ቃለ የሰጡት ልዩ ትኩረት ምስክር ነው…” ምናምን ሊል ይችላል፡፡ ግራ ሲገባውስ!
ሀሳብ አለን… “እጅግ፣ እጅግ…” የሚለውን ከመደጋገም… አለ አይደል… “እጅግ…” ካልን በኋላ “…ቱ ዘ ፓወር ኦፍ ምናምን…” የሚል መጨመር ነው፡፡ እንዲህ አይነት ግልግል እያለ ለምን እንቸገራለን፡
ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ካሜራ ፊት ለፊት ሲደቀን ለሚወሩት ነገሮች… አለ አይደል …የቃለ መጠይቁ መልእክት የታሰበላቸው ሰዎች ሲሰሙ የሚስቁት ሳቅ ይታያችሁ፡፡ ልጄ ‘ቦተሊከኛም’ ሆነ አድማጭ/ተመልካች በሉት ሁሉም በየቤቱ ‘ነቄ’ ነው፡፡ ይሄ እየጠፋቸው ለሚባዝኑ አንድዬ ልቦናውን ይስጣቸውማ!
ስሙኝማ…የዘንድሮ ሰዎች ስንትና ስንት መልክ እንዳለን አንድዬ ይወቀው! እንደ ፈጣን ሎተሪ እኮ አንዴ ብቻ ‘ተፍቀን’ የሚበቃን አይደለንም፡ እኛ ‘ስንፋቅ’ አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ…ምናምን ባህሪያት ብቅ፣ ብቅ ይላላ፡፡ በተለይማ ካሜራ ፊት ለፊታችን ሲደቀን!
‘እኛና ካሜራ…’ የሚል ፊልም ይሠራልን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3385 times