Saturday, 20 December 2014 12:12

ቦታ ቦታችሁ ግቡ ቢባል - አሎሎ ወደ ጅረት፣ ኩበት ወደ አክንባሎ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

አንድ ንጉሥ የመሞቻቸው ሰዓት ሲደርስ ሁለት ወንዶች ልጆቻቸውንና አንዲት ሴት ልጃቸውን ጠርተው፤ “ልጆቼ፤ እንግዲህ ዕድሜዬ እየገፋ፣ ጉልበቴ እየላመ፣ አቅሜም እየደከመ የመጣበት ሰዓት ነውና ከመንግሥቴ የት የቱን መውረስ እንደምትመርጡ ሀሳብ እንድትሰጡኝ እፈልጋለሁ” አሉ፡፡
ታላቅ ወንድም ምንም ሀሳብ ሳይሰጥ ዝም አለ፡፡
ሁለተኛው ወንድም፤
“አባቴ ሆይ! እርስዎ ራስዎ ይሄን ለትልቁ፣ ይሄን ለትንሿ፣ ይሄን ለትንሹ አውርሻለሁ ቢሉን አይሻልም ወይ?” ሲል ሃሳቡን አቀረበ፡፡
ሴቷ ልጅ ደግሞ፤
“አባቴ ሆይ! እኔ የምመኘውንና የማስበውን ብናገር፣ ሌሎቹም የሚያስቡትን ባውቅ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ስለሆነም አባቴ ያሉትን እደግፋለሁ” አለች፡፡
ንጉሡም፤
“አያችሁ ልጆቼ፤ አሁን ከተናገራችሁት የተረዳሁት ሦስት ነገር ነው፡፡
ከመጀመሪያው ልጄ - ዝምታን አየሁ፡፡
ከሁለተኛው ልጄ - ኃላፊነትን ለሌሎች መጣልን አየሁ፡፡
ከሦስተኛው ልጄ - በራስ መተማመንን ነው ያነበብኩት፡፡
በእርግጥ ያየሁዋቸው ሦስት ነገሮች የየራሳቸው ዋጋ አላቸው፡፡ ዝምታ ወቅቱን ከጠበቀ ዋና  ነገር ነው፡፡ ኃላፊነትን ለሌሎች መስጠት አቅምን ከማወቅና የሌሎችን ዋጋ ከማወቅ የመነጨ ከሆነ እጅግ ጠቃሚ እሴት ያለው ነው! በመጨረሻም በራስ መተማመን ከሁሉም የላቀ እሴት ነው፡፡ ያለራስ መተማማመን፤ መንግሥቴን ወዴትም ልታዘልቁት አትችሉም፡፡ በራስ መተማመን የሚመጣው ዕውቀት ሲኖር ነው፡፡ ዕውቀት የሚመጣው ለመማር ፈቃደኛ ከመሆን፣ ከልምድ ራስን ከማሻሻል፤ ሁልጊዜ ለለውጥ ዝግጁ ከመሆን ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ አጢኜና መርምሬ ሳስተውል፣ መንግሥቴን መውረስ ያለባት ሴቷ ልጄ ናት” ሲሉ ደመደሙ፡፡
***
የአንድ ህብረተሰብ ዋና ኃይል ልበ - ሙሉነትና በራስ መተማመን ነው! የሀገራችንን የህብረተሰብ አወቃቀር ስናስተውል፤ በተለይ አሁን በደረስንበት የዕድገት ደረጃ፤ የሴቶችን ከባድ ሚና፣ ከባድ ጫና እና ከባድ የሀገር እናትነት ስሜት ማጤን አይሳነንም፡፡ ከተረቶቻችን፣ ከምሳሌዎቻችንና ከጥቅሶቻችን በሰፊው እንደምንረዳው፤ የሴትን የበታችነት አጠንክረው የሚያሰምሩ ቃለ - ኃይሎች እንዳሉ አይካድም፡፡
“በለው በለው ሲል ነው የወንድ አብነቱ
ሴትም ትዋጋለች ከረጋ መሬቱ”
የሚለውን አንድ ምሣሌ ብናይ እንኳ፣ ጉዳችንን በቀላሉ ይነግረናል፡፡ “ለፍታ ለፍታ ሴት ወለደች”ን ስናይ፣ ከንቀታችን ሶስት አራት እጥፍ የሴቶች ጫንቃ ላይ እያሳረፍን እንደከረምን ለማወቅ አያዳግትም፡፡ “ምን ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ” የሚለውን አደገኛ ካንሠር አከል በሽታ ማስወገድ ይገባናል!! ሴቶችን የረሳ፣ ሴቶችን የናቀ፣ ሴቶችን ተሳታፊ ያላደረገ ሥርዓት ይዞ የትም አያደርስም፡፡ “እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች” የሚለው ተረትም አሁንም በሴት ጫንቃ ላይ የተንተራሰ ይሁን እንጂ ቁምነገሩን አንስተውም፡፡
ሀገራችን በተለያዩ የሥራና የህይወት ዘርፎች ያለ ሴት በሣልና ጠንካራ ተሳትፎ ካለመችበት ልትደርስ አትችልም፡፡ ከዚህ አንፃር ሴቷን የለውጥ መዘውር ለማድረግ ለአፍታም ሳንታክት ማሰብና ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በመፈክር ላይ በመንጠልጠልና በቀለም በማድመቅ ብቻ የትም እንዳልደረስን አይተነዋል፡፡ በሌላ በኩል ራሳቸውን ለትግል ያበቁ፣ የታገሉና ያሸነፉ ሴት ፋና - አብሪዎች፣ ለድል የበቁት አደራጅተው እንደሆነ እናውቃለን፡፡  በተለያዩ የሙያ ዘርፎች፣ በንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም በባህላዊ ትሥሥር ዙሪያ ገፍተው ብቅ ብቅ ያሉቱ ምን ያህል ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ እያየን ነው፡፡ ገና ግን ብዙ ማደግ፣ በየዘርፉ ብዙ መብቀል፣ ብዙ ማፍራት፣ ብዙ ማልማት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል እንቅስቃሴያቸውን ከአንጀቱ ማገዝና ማጐልበት፣ ትልቅ አስተዋፅዖ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በሙያና በብዙሃን ማህበራት፣ በቤተሰብና በግል ህይወት ውስጥ ሚናቸውን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ብርቱ ጉዞ ይጠብቀናል፡፡ በህብረተሰባችን ውስጥ ሁሉም ቦታ ቦታ እንዳለው አንርሣ! “ቦታ ቦታችሁ ግቡ ቢባል አሎሎ ወደ ጅረት፣ ኩበት ወደ አክንባሎ” የሚባለውም በየቦታው ሁሉም ባለዕሴት መሆኑን ሲነቁጥ ነው!  


Read 5395 times