Saturday, 20 December 2014 12:03

ለማዳበሪያና ምርጥ ዘር ግዢ የሚውል አዲስ የኩፖን አሰራር ተጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

አርሶ አደሮች ለግብርና ሥራ የሚጠቀሙበትን እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያሉ ግብአቶች ማግኘት የሚችሉበት አዲስ የኩፖን ሽያጭ አሰራር ሰሞኑን ይፋ ተደረገ፡፡ በአገሪቱ ያሉ የገንዘብ ተቋማት የኩፖን ሽያጭ ሥርዓቱን እንዲተገብሩ ኃላፊነት ተሰጥቶአቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ተግባራዊ ባደረገው አዲስ የኩፖን ሽያጭ ስርዓት፤ እስከ አሁን 230 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ግብአት ተከፋፍሏል፡፡
አዲሱን የኩፖን ሽያጭ አሰራር አስመልክቶ ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አርሶ አደሩ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አጠቃቀሙ አመርቂ እንዳልሆነ ተጠቁሟል፡፡ በአገሪቱ ካለው አርሶ አደር ማዳበሪያ የሚጠቀመው ከ30-40% የሚሆነው ብቻ ሲሆን በሰብል ከተሸፈነው የሀገሪቱ መሬት በተሻሻሉ ምርጥ ዘር አይነቶች የተሸፈነው 10 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም የብድር አቅርቦት ውስንነት ዋነኛው ምክንያት ሲሆን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ የገንዘብ ተቋማት አቋማቸው ጠንካራ ያለመሆንና የመድን ዋስትና ያለመኖር እንደችግር ተጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ተሾመ ዋለ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ቀደም ሲል የክልል መንግሥታት፣ አርሶ አደሩ ለማዳበሪያና ምርጥ ዘር ግዢ የወሰደውን ብድር በአግባቡና በጊዜው ባለመመለሱ ምክንያት ከበጀታቸው ያልተሰበሰቡ የብድር እዳዎችን ለመክፈል ይገደዱ ነበር፡፡ አዲሱ የኩፖን ሽያጭ ስርዓት ግን ተበዳሪው የተበደረውን ገንዘብ በአግባቡ ለመክፈል የሚችልበትን አሰራር የዘረጋ በመሆኑ የክልል መንግስታት ላልተሰበሰበ የብድር እዳ ተጠያቂነታቸውን ያስቀራል ብለዋል፡፡
አዲሱ የግብርና ግብአት ኩፖን ሽያጭ፤ አርሶ አደሩ ለተወሰኑ የግብርና ግብአቶች ለገንዘብ ተቋማት ክፍያ በመፈፀም ከተቋማቱ በሚሰጠው የካሽ ኩፖን ወደ ህብረት ሥራ ማህበራት በመሄድ፣ በግብርና ግብአቶች ለመለወጥ የሚችሉበትን አሰራር የዘረጋ ነው፡፡ የአገሪቱ የገንዘብ ተቋማት የአርሶ አደሩን ለብድር ብቁነት ማረጋገጥ፣ የግብአት ብድር ኩፖንን የመስጠትና ክፍያዎችን የመሰብሰብ፣ ለሰበሰቡት ገንዘብ የግብአት ካሽ ኩፖን የመስጠት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ የተሰጣቸውን ብድር እስከ 12 ወራት በሚደርስ ጊዜ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዲሱ የኩፖን ሽያጭ ሥርዓት ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል የሙከራ ሥራ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን 156 ሺ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉም ተገልጿል፡፡

Read 1346 times