Saturday, 20 December 2014 12:01

“ጉዞ አድዋ 119” የእግር ጉዞ ጥር 10 ይጀመራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

ከ1 ሺ ኪ.ሜ በላይ መጓዝ የሚችል እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል

ባለፈው ዓመት የተጀመረው “ጉዞ አድዋ” የእግር ጉዞ ዘንድሮም የተጓዦችን ቁጥር በመጨመር እንደሚቀጥል የገለፁት አዘጋጆቹ ባለፈው ዓመት የአድዋ 118ኛውን  የድል በዓል ለማክበር ከአዲስ አበባ አድዋ ድረስ የተጓዙት የሶሎራዩ መስራቾች፤ ዘንድሮም 119ኛውን የአድዋ ድል በዓል በድምቀት ለማክበር ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍነውን ርቀት ለመጓዝ ጥር 10 ከአዲስ አበባ በመነሳት የካቲት 23 ቀን 2007 ዓ.ም አድዋ ለመድረስ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ይህን ጉዞ ካከናወኑ በኋላ ለአድዋ ጦርነት መንስኤ የሆነውን የውጫሌ ስምምነት 125ኛ ዓመት ማክበራቸውን ያስታወሱት አዘጋጆቹ፤ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ 25 ጋዜጠኞች፣ የክልሉና የፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የጥበብ ባለሙያዎችና የታሪክ ምሁራን ወደ ስፍራው በመጓዝ መታደማቸውን አውስተዋል፡፡
በዘንድሮው “ጉዞ አድዋ 119” ላይ ለታሪክ ፍቅር ያላቸው ከ10 እስከ 15 ያህል ሰዎች እንዲሳተፉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን እድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ የሆነ፣ ከመኖሪያ ከተማቸው ርቀው መቆየት የሚችሉ፣ የ44 ቀናት አድካሚ ጉዞ ለማድረግ አቅምና ጤና ያላቸው እንዲሁም ለአድዋ ድል ፍቅር ያላቸውና ታሪኩን በመልካም ጎኑ ለማስተዋወቅ ፈቃደኛ የሆኑ እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም በስልክ ቁር 0912 73 64 06 በመደወል እንዲመዘገቡ አሊያም በፌስ ቡክ ገፅ መልእክት እንዲተዉ፣ ካልሆነም በድርጅቱ የኢሜል አድራሻ (solorayo This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) መልእክት መላክ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
“ሶሎራዮ ኤቨንትስ ኤንድ ኮሙኒኬሽን” በተለያየ የስራ መስክ እውቅና ያላቸውና የሃገራቸውን ታሪክ በሚወዱ ወጣቶች የተመሰረተና ታሪካዊና ተገጥሯዊ መስህቦችን በማጉላት ብሎም፣ በማስተዋወቅ አለም አቀፍ ዝና እንዲያገኙ ጥረት ለማድረግ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑም ተገልጿል፡፡ 

Read 2676 times