Saturday, 20 December 2014 12:01

ኤልጂ በሰንዳፋ አካባቢ ለሚገኘው ሙዳ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ድጋፍ አደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኤልጂ ኩባንያ በኦሮሚያ ክልል ሰንዳፋ አካባቢ ለሚገኘው ሙዳ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሳርያዎች ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ኤልጂ ከወርልድ ቱጌዘር፣ መንግስታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ የልማትና የግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በሰንዳፋ አካባቢ ዱግዴራ በተሰኘ መንደር የማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክት በመተግበር ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡ ፕሮጀክቱ “ኤልጂ ሆፕ ቪሌጅ” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን የመንደሩ ነዋሪዎች እራሳቸውን ለዘለቄታው እንዲችሉ በእርሻና በእንስሳት እርባታ ስልጠናና ድጋፍ የሚያገኙበት ነው ተብሏል፡፡
ኤልጂ ግብርና ላይ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማስፋፋት በአካባቢው ለሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በሰንዳፋ ወረዳ ለሚገኙ አራት ት/ቤቶች ከማስፋፊያ ግንባታዎች ጀምሮ እስከ ትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድረስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ኤልጂ በስሩ በሚገኘው ኢኖቴክ ኩባንያ አማካኝነት ላለፉት ወራት ለሙዳ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን አሁን ደግሞ ት/ቤቱን በማደስ እንዲሁም ለተማሪዎች ቦርሳ፣ የመማሪያ መፃህፍት፣ የመማሪያ ዴስኮች፣ ወንበሮችና ጥቁር ሰሌዳዎችን ባለፈው ሕዳር ወር መጨረሻ በት/ቤቱ በተሰናዳው ዝግጅት አበርክቷል፡፡
ት/ቤቱ ከከተማ ባለው ርቀት የተነሳ በአዲስ መልክ ለመገንባትና በተፈለገው መልኩ ለትምህርት አመቺ ለማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም የመማሪያ ክፍሎቹን ባሉበት በማደስ፣ የቀድሞዎቹን አሮጌና ለመማር ማስተማር አመቺ ያልነበሩትን ክፍሎች የተሻለ ብርሃን እንዲያገኙ፣ እንዲሁም የክፍሎቹ ወለሎችና ግድግዳዎች እንዲፀዱ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተማሪዎች መፀዳጃ በመማሪያ ክፍሎቹ አቅራቢያ እንዲሆን በማድረግ ከዚህ ቀደም ተማሪዎች መፀዳጃ ለማግኘት እስከ 10 ደቂቃ ይወስድባቸው የነበረውን የእግር ጉዞ አስቀርቷል ተብሏል፡፡

Read 992 times