Saturday, 20 December 2014 11:58

ቮልቮ በእጅና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የጭነት መኪኖችን አስመጣ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

“የቮልቮ እምነት ምርታማነት ነው”

በኢትዮጵያ የቮልቮ ኩባንያ በመገባደድ ላይ ባለው የፈረንጆች ዓመት ያመረታቸውን በእጅና በኤሌክትሪክ የሚሰሩና፣ ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ከባድ የጭነት መኪኖችን አስተዋወቀ፡፡
ከትናንት በስቲያ በሚሌኒየም አዳራሽ ግቢ በተካሄደው ማስተዋወቅ፣ FM 400 እና FH 400 የተባሉ ሁለት ዓይነት መኪኖች የቀረቡ ሲሆን፣ የአዲሶቹ ቮልቮ መኪኖች ጋቢና ከበፊተኞቹ ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለና ለአሽከርካሪዎች ምቹ፣ መብራትና መስታወታቸውም ከበፊተኞቹ የተሻለ እንደሆነ የቮልቮ የሽያጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት በኃይሉ፤ ገልፀዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ መኪኖቹ ግማሽ አውቶማቲክ (ኢንተሌጄንት ወይም ሃይሺፍት) እንደሆኑ ጠቅሰው ማርሹ የእጅ ቢሆንም መቆጣጠሪያው የኤሌክትሪክ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አሽከርካሪው አንዴ ማርሹን አውቶማቲክ ላይ ካደረገ፣ መሳሪያው ራሱ የአካባቢውን ሁኔታ (ዳገትና ቁልቁለት) መሆኑን ተረድቶ ማርሹን ይጨምራል ወይም ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ በአጠቃቀም ስህተት የሚከሰት የማርሽ ጥርስ መሰበር ስለማይኖር፣ መኪኖቹ ሳይበላሹ ረዥም ጊዜ ይሰራሉ ብለዋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ከከባድ መኪኖች ጋር ተያይዞ ተፈላጊ ያልሆነ የማርሽ ዓይነት በመጠቀምና ተሽከርካሪውን በማስጨነቅ ብዙ ነዳጅ እንደሚባክን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፤ የአዲሶቹ መኪኖች ማርሽ አውቶማቲክ በመሆኑና የኃይል መቆራረጥ ስለማይኖር ከ3 እስከ 5 በመቶ የነዳጅ ፍጆታ እንደሚቆጥቡ አስረድተዋል፡፡
መኮኖቹ ዳይናሚክ ስፕሪንግ የተባለ ቴክኖሎጂ ስላላቸው ሹፌሩ መሪውን በቀላሉ ማዞር እንደሚችልና በወጣ ገባ መንገድ ላይ ወደ ላይ መንጠርና መንገጫገጭ እንደማይሰማቸው ገልፀዋል፡፡
ቮልቮ በ2014 ምርቶቹ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያደረገው በመኪኖች ጋቢና ላይ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ነፃነት፤ የFM ጋቢና ከበፊተኞቹ መኪኖች ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለና መካከለኛ ሲሆን የFH ጋቢና ደግሞ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ሾፌሩን ማቆም ስለሚያስችልና የጋቢናው ስፋት አየር በሚገባ እንዲዘዋወር ስለሚያደርግ ለሾፌሩ ምቾት ይፈጥርለታል ብለዋል፡፡
“የቮልቮ እምነት ምርታማነት ነው፡፡ ምርታማነት የሚመጣ ደግሞ የሾፌሮች ምቾትና ደህንት ሲጠበቅ ነው፡፡ ሦስቱ የቮልቮ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የአሽከርካሪው ደህንነት፣ ጥራትና ከባቢ አየርን ያለመበከል ናቸው” ያሉት አቶ ነፃነት፤ ቮልቮ በጥራት ላይ እንደማይደራደር ሲገልጹ፤ ባለፉት 20 ዓመታት ኢትዮጵያ የገቡ የቮልቮ መኪኖች የሞተር እድሳትና ጥገና እየተደረገላቸው አሁንም እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
   

Read 2243 times