Saturday, 13 December 2014 11:08

የአፍታ ቆይታ ከአሜሪካ አምባሳደር ጋር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“አሜሪካ ፆታዊ ጥቃቶችን አጥብቃ ትቃወማለች”
አገራቸው በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን አጥብቃ እንደምትቃወምና የሴቶችን አቅም በመገንባትና በማሳደግ ረገድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በህብረት እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ኤም ሃስላክ ገለፁ፡፡ ከህዳር 16 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ በዘለቀው የነጭ ሪባን ቀን፤ በኤምባሲው በተዘጋጁ የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ከተሳተፉት የአሜሪካ አምባሳደር ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ የአፍታ ቆይታ አድርጋለች፡፡

አምባሳደር በመሆን ተሹመው ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣትዎ በፊት ስለ ኢትዮጵያ ያውቁ ነበር?
በ1980ዎቹ በኢትዮጵያ በተከሰተው ረሃብና የድህነት ችግር ላይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር እሰራ ነበር፡፡ በ2010 አለም አቀፍ የድህነት መዋጋትና የምግብ ዋስትና (አሁን Future Initative እየተባለ የሚጠራውን) ድርጅት ወክዬ ወደ ኢትዮጵያ መጥቻለሁ፡፡
አሁን ሲመጡ ምን ለውጥ አዩ?
ብዙ ለውጦች አሉ፡፡ አገሪቱ እያደገች በመሄድ ላይ መሆኗንም ለማየት ችያለሁ፡፡
ፆታዊ ጥቃትን አስመልክቶ ሰሞኑን በተዘጋጁ የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከተደራራቢ የሥራ ኃላፊነትዎ አንፃር ይህን እንዴት ተወጡት?
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን አገሬ አጥብቃ ትቃወማለች፡፡ ለዚህም ነው በፀረ ፆታዊ ጥቃትና ሴቶችን በማብቃት ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራው፡፡ ይህ የነጭ ሪባን ቀን ደግሞ ለፆታዊ ጥቃቶች ያለንን ተቃውሞ የምናሰማበት ስለሆነ ነው በኤምባሲው በተዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ ሁሉ ተሳታፊ የሆንኩት፡፡ በግሌ ደግሞ ከመሃከለኛው ህዝብ ጋር መሆን ደስታን ይሰጠኛል፡፡ ለሰዎች ድጋፍና ተስፋን ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራት እወዳለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ቦታዎች ላይ መገኘትም የሚሰጠኝ ደስታ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡
በቅርቡ በቡድን በተደረገባት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ህይወቷ ያለፈው ታዳጊ ወጣት ሃና ላላንጐ ጉዳይ በአገሪቱ አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ጉዳዩ በማህበረሰቡ ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ቢሆንም አንዳንድ ወገኖች መንግሥት ስለ ጉዳዩ ብዙም ያለው ነገር የለም በማለት ይተቻሉ፡፡ በእናንተ አገር እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲያጋጥም የመንግስት ሚና ምንድነው?
የሃና ጉዳይ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ወይንም የሚከሰት ብቻ አይደለም፡፡ በመላው ዓለም የሚከሰትና የተከሰተም ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ለማስቀረት ዋንኛው መፍትሄ ህብረተሰቡን ማስተማር ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ ለጉዳዩ ያገባኛል ማለት መቻል አለበት፡፡ ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ባል ሚስቱን ሲደበድብ ወይም ጐረምሳው ወጣቷን ሲመታ አይቶ በዝምታ ማለፍ አግባብ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው እንዲህ አይነት ፆታዊ ጥቃቶች ሲፈፀሙ ሲያይ ለማስቆም ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ሴቶች በራሳቸው ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለማስቆም የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው ለማድረግም ጥረት እናደርጋለን፡፡ በፆታዊ ጥቃቶች ላይ መንግስታችሁ ጥብቅ አቋም እንዳለው አውቃለሁ፡፡ የአስራ ስድስት ቀናቱን የነጭ ሪባን ቀን በማስተባበር እየሰራ የነበረው የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡ እናም መንግሥታችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ ነው፡፡
የሁለት ሴት ልጆች እናት ነዎት፡፡ አንደኛዋ ልጅዎ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ተሰማርታለች፡፡ የት ነው የምትሰራው? ለጋዜጠኝነት ሙያ ያለዎት ስሜትስ ምን ይመስላል?
ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ፡፡ አንዷ ከጥቂት ቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ለሁለት ሳምንታት ቆይታ ሄዳለች፡፡ ለጋዜጠኝነት ፍቅር አላት፡፡ ከኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ ስኩል ኦፍ ጆርናሊዝም ዲግሪዋን ወስዳለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ለቢቢሲ ትራቭል እንዲሁም፣ ለኒውዮርክ ታይምስና ለሌሎች መፅሄቶች ትሰራለች፡፡ ለሙያው ጥሩ ስሜት አለኝ፡፡   

Read 2936 times