Print this page
Saturday, 13 December 2014 10:54

ሰላማዊ ሰልፍ የሚስተጓጐለው የመሬት ሊዝ ዋጋ በመናሩ ይሆን እንዴ?

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(20 votes)

አቶ መለስ “መንግስት የመላዕክት ስብስብ አይደለም” ብለው ነበር

    አሜሪካዊው ዶ/ር ዊሊያም ዩሪ፤ በግጭት አፈታት፣ በእርቅና በገላጋይነት እንዲሁም በድርድር ጥበብ የተካነ ባለሙያ ነው፡፡ ፀሐፊና ደስኳሪም (speaker) ጭምር፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት ግጭት በተከሰቱባቸው አብዛኞቹ የዓለማችን አገራት መፍትሄ በማፈላለግ ተግባር ላይ ተሳትፏል፡፡ (የአገራችን ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ በሉት!) ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገራት እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ተጉዟል፡፡  በግጭት ላይ የሚያጠነጥን “The Third Side” የተሰኘ ዝነኛ መፅሃፍም አሳትሟል፡፡ (ማን ይሆን ሦስተኛው ወገን?)
ዩሪ፤ ለትላልቅ ኩባንያዎች፣ ለመንግስት ኃላፊዎች፣ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወዘተ… (በብዙ 100ሺዎች ለሚገመቱ ታዳሚዎች) በግጭት አፈታትና በድርድር ጥበብ ዙሪያ ደስኩሯል - ከህይወት ተመክሮው እየጨለፈ፡፡ (የዩሪ ዓይነት በእጅጉ ያስፈልገናል!) እኔም ይሄን የሰላም ሰው ያወቅሁት ሰሞኑን ነው፡፡ የድርድር ጥበብ (The art of negotiation) በሚል ርዕስ መረጃ ሳስስ Tedtalk በተባለ ዝነኛ ሰዎች በሚደሰኩሩበት የቲቪ ፕሮግራም ላይ አግኝቼ አዳመጥኩት - አንዴ ሳይሆን ደጋግሜ፡፡ ለምን መሰላችሁ? እንደኔ አይነት “የአበሻ ደም” ያለው ሰው የድርድር… የውይይት… የመግባባት…. የመከባበር…. የመደማመጥ…ነገር  ቶሎ ወደ ውስጡ ዘልቆ አይገባም፡፡ (አበሻ ነዋ!)
አያችሁ… እኛ አበሾች ደማችን ቶሎ ስለሚፈላ ከመቅፅበት በስሜት ቱግ እንላለን፡፡ (ለወገናችንም ለባዕድም ያው ነን!) በእልህ እንንተከተካለን፤ ከማሰብ ይልቅ በስሜት መነዳት ይቀናናል፡፡ “መቻቻል” ጥርሳችንን የነቀልንበት ነው ብንልም እውነቱ ግን ጨርሶ ከመቻቻል ጋር አለመተዋወቃችን ነው፡፡ እኔን ካላመናችሁኝ… የአገራችንን ፓርቲዎች (ፖለቲከኞች) እዩአቸው፡፡ (ሃቀኛ አበሾች እነሱ ናቸዋ!)
ድርድርና ውይይት የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የነበሩ ቢሆንም እንዳሁኑ ዘመን በከፍተኛ መጠን ተተግብረው (ለሰው ልጅ ጥቅም ውለው) አያውቁም ይለናል - ዶ/ር ዩሪ፡፡ (እንደ አንዳንድ የመጠቁ ቴክኖሎጂዎች እኛ ጋ አልደረሰም እንጂ!) የግጭት አፈታት ሊቁ ዶ/ር ዊሊያም ዩሪን ያለምክንያት አላመጣሁትም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገዢው ፓርቲና የተቃዋሚዎች ውዝግብ እየተባባሰ በመምጣቱ ነው (የጦቢያ “ቀዝቃዛው ጦርነት” በሉት!)
እኔ የምላችሁ … ለምንድነው በአሁኑ ወቅት የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ የውዝግብ መነሻ የሆነው? አሁንማ እኛንም ታከተን እኮ፡፡ ተቃዋሚዎች የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ያቀርባሉ፤ የሚመለከተው አካል ፈቃድ ይከለክላል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይሄ የሚመለከተው አካል የተቋቋመው ሰላማዊ ሰልፍ ለመከልከል አይደለም (ይሄማ ህገ መንግስቱን መፃረር ነው!) እንኳን እሱ ሌላውም የመንግስት ተቋም ህገመንግስቱን ለማስፈፀም እንጂ ለመጣስ አልተቋቋመም፡፡ ግን አንዳንዴ በተቃራኒው የሚንቀሳቀሱ አይጠፉም፡፡ ለዚህ እኮ ነው የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (መሬት ይቅለላቸውና!) “መንግስት የመላእክት ስብስብ አይደለም” ያሉት፡፡ እናም አስበውም ሆነ ሳያስቡ ህገ መንግስቱን የሚጥስ ተግባር የሚፈፅሙ አይጠፉም፡፡ ይሄ’ኮ ፈፅሞ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም፡፡ በቅርቡ አይደለም እንዴ…አንድ ትልቅ የመንግስት መ/ቤት ሃላፊዎች (ከላይ እስከ ታች) በሙስና ተዘፍቀው የተገኙት? በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ከንቲባዎችን ጨምሮ በርካታ ሃላፊዎች በመሬት ዝርፊያ ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውንና ክስ ተመስርቶባቸው እንደተፈረደባቸውም እንዳትዘነጉ፡፡ (ህገመንግስቱን እያስከበሩ እኮ አይደለም!) ከምሬ ነው የምላችሁ… የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር “መንግስት የመላእክት ስብስብ አይደለም” የምትለዋን አባባል ባይተነፍሱ እኮ ሙሰኞች እንደ አሸን ሲፈሉ ኢህአዴግ ማጣፊያው ያጥረው ነበር፡፡ (ዕድሜ ለሳቸው!) ወደ ተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ ልመልሳችሁ - የተቃውሞ ሰልፍ (ህዝባዊ ስብሰባ) ጥያቄና ክልከላ እንዲሁም ያንን ተከትሎ የሚፈጠር ውዝግብ… እሰጥ አገባ… ፍጥጫ…. የፖሊስ ከበባ… ዱላ… እስር… ክስ… የዲሞክራሲያዊነት ምልክቶች አይደሉም፡፡ …(ከዚህ በላይ Conflict አለ እንዴ?) ይሄ ሁሉ እኮ በሰላም አገር ነው፡፡ (ቢያንስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልታወጀማ!)
እኔ መንግስትን ብሆን ግን ምን መሰላችሁ የማደርገው? የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃጅ ወይም ዕውቅና ሰጪ የተባለውን ክፍል አፍርሼ እንደገና አዋቅረው ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? የፓርቲንም ሆነ የመንግስትን እንዲሁም የአገር ገፅታን እያበላሸ ነዋ!! ሃላፊነቱን ያለ ብዙ ግርግርና ወከባ በዘዴና በብልሃት የሚወጣ አካል ነው የሚያስፈልገው፡፡
 ተቃዋሚዎች የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ባነሱ ቁጥር ግጭትና ፍጭት ከተፈጠረማ ብቃት የለውም ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ፈርሶ እንደገና መደራጀት አለበት (እኔ መንግስት ብሆን ነው ያልኩት - “If I were a boy…አለች ቢዮንሴ! በነገራችን ላይ “የፖለቲካ ኪራይ ሰብሳቢዎች”ም ሳይኖሩ አይቀሩም ባይ ነኝ፡፡  
እኔ የምለው ግን… ሰላማዊ ሰልፍ የሚደረግባቸውና የማይደረግባቸው ስፍራዎች የሚባል ነገር አለ እንዴ? (ከሆስፒታሎችና ከሃይማኖት ተቋማት ውጭ ማለቴ ነው!) ባለፉት ሳምንታት የ“አዳር ተቃውሞ” ጥያቄው ያልተሳካለት በዘጠኝ ፓርቲዎች ጥምረት የተመሰረተው “የፓርቲዎች ትብብር” (ምርጫ ቦርድ “ዕውቅና አልሰጠሁትም” ብሏል!) የ24 ሰዓት ሰልፉን ለማድረግ የፈለገው በመስቀል አደባባይ ነበር፡፡ (ቢሳካ ኖሮ እኮ ለአገር ገፅ ግንባታ ይጠቅም ነበር፡፡) እንዴት ብትሉ…ለ24 ሰዓት የዘለቀ በምስራቅ አፍሪካ ረዥሙ የተቃውሞ ሰልፍ ተብሎ “ጊነስ ቡክ ኦፍ ዎርልድ ሪከርድ” ላይ ይመዘገብ ነበር!
የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት ግን መስቀል አደባባይን በሦስት ምክንያቶች አልፈቀደም፡፡ የውጭ ድርጅቶች ያሉበትና የመንግስት ተቋማት የሚበዙበት እንዲሁም የግንባታ ሥራ የሚከናወንበት በመሆኑ ዕውቅና አልሰጠሁም ብሏል - ፅ/ቤቱ ባለፈው ሳምንት፡፡ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል በበኩላቸው፤ የመንግስት ተቋማት የሚበዙበት ለተባለው በሰጡት ምላሽ፤ “እኛም ተቃውሟችንን የምናሰማው ለመንግስት ስለሆነ ተገቢ ቦታ ነው” ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡ (ወይም የተሳለቁ መስሎኛል!) አንዳንድ ታዛቢዎች ደግሞ እንደ ዛሬ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተከለከለ አደባባይ፤ በበነጋታው ገዢው ፓርቲ እንዳሻው ሲሰለፍበት ይውላል ሲሉ ይተቻሉ (እውነት ነው ሃሜት?)
ታዛቢዎቹ ግን አንድ ያልገባቸው ወይም ያልሰሙት ነገር አለ፡፡ በቅርቡ እኮ ሥልጣን የያዘ ገዢ ፓርቲና ተቃዋሚ እኩል መብትና ጥቅም (privilege) ሊኖራቸው አይችልም ተብሏል፡፡  እኔ የምለው ግን… ገዢው ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ወይም ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግ ሲፈልግ ፈቃድ ይጠይቃል እንዴ? (ማንን?) አንዳንድ “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” (የኢቲቪዎቹ አይደሉም!) ጠይቅልን ስላሉ እንጂ እኔማ መልሱን አውቀዋለሁ፡፡ ሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲና ተቃዋሚዎች እኩል መብትና ጥቅም (privilege) ሊኖራቸው እንደማይችል የተናገሩት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ነበሩ - በፓርላማ!! (ይሄ ነገር በአዋጅ ፀድቋል እንዴ?)
እናላችሁ… ከሰላማዊ ሰልፉ ይልቅ ሰልፉ የሚደረግበት ስፍራ (መስቀል አደባባይ፣ ጃንሜዳ፣ ሽሮሜዳ፣ ስታዲየም፣ ቸርችል ጐዳና ወዘተ…) በእጅጉ ያወዛገበ ሲሆን ባለፈው ቅዳሜም የተቃዋሚዎች አመራርና አባላት ያለ ፈቃድ ሰልፍ ሊወጡ ሞክረዋል ተብለው በፖሊስ ተይዘው ታስረዋል፡፡ ፍ/ቤት በቀረቡበት ወቅትም ፖሊስ ከፍተኛ ድብደባና እንግልት ፈፅሞብናል ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ (ዱላን ምን አመጣው?) ፍ/ቤቱም መደብደብ እንደሌለባቸወና በአግባቡ ሊያዙ እንደሚገባ ትእዛዝ ሰጥቷል ተብሏል፡፡ (ፖሊስን “ለምን ደበደብክ” ብሎ መጠየቅ ነውር ነው እንዴ?)
ምናልባት ይሄ የሰላማዊ ሰልፍ ማድረጊያ ቦታ እንዲህ ያወዛገበው ከሰሞኑ የመሬት ሊዝ ዋጋ መናር ጋር በተገናኘ ይሆን እንዴ? (መርካቶ በርበሬ ተራ አንድ ካሬ ሜ. ቦታ 305ሺ ብር አውጥቷል በጨረታ!) እናም ምን አልኩ መሰላችሁ? “ወደፊት ከእነ አካቴው የሰላማዊ ሰልፍ ማድረጊያ ቦታ ስለሚጠፋ ከአሁኑ በብድርም ቢሆን ሰፋፊ መሬት ገዝቶ ማስቀመጥ ሳይበጅ አይቀርም” (ግን በሆዴ ነው!) ከምሬ እኮ ነው… ያለዚያ ሰላማዊ ሰልፍ የሚባል ነገር ታሪክ ሆኖ ሊቀር ይችላል (“እንኳንም ዘንቦብሽ…” አሉ!)
እርግጠኛ ነኝ ኢህአዴግ ወይም መንግስት የሰላማዊ ሰልፍ ውዝግቡን ተከትሎ በተከሰተው ነገር ይደሰታሉ ብዬ አላስብም፡፡ ውዝግቡ ሳይነሳ፤ ከተነሳም ደግሞ ሳይጯጯህ ቢፈታ የሚመርጥ ይመስለኛል፡፡ እስቲ ይታያችሁ… ከአንድ አመት ወዲህ እየተሰማ ያለው እኮ አስፈሪና ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ (እንኳን ለሌላው ለራሱም ለኢህአዴግ!) ብዙዎቹ የአገሪቱ መፅሄቶች ተዘግተው ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች ተሰደዋል፡፡ (የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም ቢባልም!) አምስት ገደማ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በሽብር ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡ 10 የሚጠጉ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን እንዲሁ በሽብር ተጠርጥረው በእስር ላይ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ከዘጠኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተውጣጡ አመራሮችና አባላት ታስረው ተፈቱ፡፡ የፈለገ ምርጫ ቢደርስ…የፈለገ ኢህአዴግ ቢጠላቸው… ይሄ ሁሉ ሰው በእስር ላይ እንዲሆን መንግስት ይፈልጋል ብዬ ማሰብ ያዳግተኛል፡፡ (“ታዲያ ማን አስገደደው” እንዳትሉኝ?) ይሄ ሁሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ታስሮ ምርጫ ቢያካሂድ እኮ ለገፅታ ግንባታው ጥሩ አይሆንም! (ጠላቶች “አምባገነን ጥሎ አምባገነን ሆነ” ብለው ሊያጋንኑት ይችላሉ!)
ሁሌም የሚገርመኝ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ የጐረቤት አገራትን ግጭትና ፍጭት ለመፍታት ቀድሞ እየተገኘ፣ የጓዳውን ችግር ለመፍታት አቅም ማጣቱ ነው (“የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች” ማለት ይሄኔ ነው!) እኔ ግን ይሄን የሚፈፅሙት “የፖለቲካ ኪራይ ሰብሳቢዎች” ናቸው ባይ ነኝ፡፡ (ኢህአዴግን ለማሳጣት የሚፈልጉ!)
ቀደም ብዬ ያስተዋወቅኋችሁ አሜሪካዊ ምሁር በግጭት ወቅት “The Third Side” አስፈላጊ ነው ይላል፡፡  በእኛ አገር ግጭቱ ያለው በአውራ ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል ነው፡፡ ፀቡ… ብጥብጡ… ጥሉ… እስሩ… ዛቻው… እርግማኑ… መወጋገዙ… በሁለቱ ወገኖች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ይሄን የሚያበርድ… የሚያቀዘቅዝ… የሚያስታርቅ… ሽምግልና የሚቀመጥ… ግራ ቀኙን የሚያዳምጥ… “ሦስተኛ ወገን” የግድ መኖር አለበት - እንደ ዩሪ አባባል፡፡ The Third  Side ይባላሉ፡፡ የ97 ምርጫ የፖለቲካ ቀውስን ተከትሎ የታሰሩ የቅንጅት ከፍተኛ አመራሮችንና መንግስትን የሸመገለው በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ የሚመራው የአገር ሽማግሌ ቡድን “ሦስተኛ ወገን” ነው፡፡ ሁለቱን ወገኖች አደራድሮ… አስማምቶ… በይቅርታም በሉት በምህረት ከእስር እንዲፈቱ አድርጓል - ይሄ ነው የሦስተኛ ወገን ትክክለኛ ሚና፡፡
አያችሁ… ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በስሜት እልህ ተገባብተው… የቃላት ጦርነት ውስጥ ሲገቡ፣ ቶሎ ካልተገታና በፍጥነት ወደ ውይይትና… ድርድር ካልተገባ መጨረሻው አያምርም፡፡ ሁለቱ ወገኖች እንዳይጋጩ የምንፈልገው በዋናነት ስለምንወዳቸውና ስለሚጠቅሙን ላይሆን ይችላል፡፡ የሁለቱን ጠብ/ግጭት የማንፈልገው ለልጆቻችን… ለቤተሰባችን… ለማህበረሰባችን… ለአገራችን… ሰላምና ደህንነት ስንል ነው፡፡ (ኋላቀርነትም እኮ ነው!) ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅም ከአሜሪካ ድረስ በአውሮፕላን እየተመላለሱ አንዴ ቤተመንግስት፣ ሌላ ጊዜ ወህኒ እየወረዱ የሸመገሉት… ለአገርና ለህዝብ ሲሉ ነው፡፡ (ለመጪው ትውልድ የምናስረክባትን አገር አንዘንጋ!)
እስከዛሬ የተቃዋሚ አመራሮች ታስረው ቢሆን ኖሮ… ለአገር ምን ያህል  ኪሳራ እንደሚሆን አስቡት፡፡ እናም… የስሜትና የእልህ ትኩሳቱ  ከፍ ሲል… ደማቸው እየተንተከተከ ሲያስቸግር… እንደ ደቡብ አፍሪካውያን ጥንታዊ ማህበረሰቦች፣ መርዝ የተቀባውን የአደን ቀስት ጫካ ውስጥ ደብቆ ሁለቱን ወገኖች ለውይይት የሚጋብዙ ሽማግሌዎች… ተቋማት… የሃይማኖት አባቶች… ያስፈልጉናል፡፡ ቢመስለንም ባይመስለንም እውነቱ ይሄ ነው፡፡ አገር እኮ በሃይልና በህግ ብቻ አትመራም፡፡ ለዚህ እኮ ነው መንግስት የቤኒሻንጉል ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ሰላማዊ ጥረት የሚያደርገው፡፡ ዶ/ር ዩሪ እንዳለው፤ ዘመኑ የጉልበት ሳይሆን የድርድር ነው!!!  

Read 3985 times