Saturday, 13 December 2014 10:40

እናት ባንክ በመጀመሪያው ዓመት ትርፋማ ሆንኩ አለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

በቅርቡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው እናት ባንክ፤ ወደ ሥራ በገባ የመጀመሪያው ዓመት ትርፋማ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የዛሬ ሳምንት ባደረገው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ፣ የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የባንኩን የ16 ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፤ ባንኩ በመጀመሪያው ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡንና ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱን ጠቅሰው፣ በአገሪቱ የባንኮች ታሪክ በመጀመሪያው የሥራ ዓመት ከፍተኛውን ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰበ ባንክ ሊሆን እንደበቃ ገልፀዋል፡፡
ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት፣ እናት ባንክ አክሲዮን ማህበር 354.7 ሚሊዮን የተመዘገበ፣ 261.6 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል እንዳለው በዓመታዊ ሪፖርቱ የተገለፀ ሲሆን ከ10,500 ከሚበልጡት ባለ አክሲዮኖች 63.4 በመቶው፣ ከ7,500 ደንበኞቹ መካከል ደግሞ 59 በመቶ ሴቶች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በመጀመሪያው ዓመት የሥራ አፈፃፀም ከታክስ በፊት 38.5 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አስመዘግቧል ያሉት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ተሾመ፤ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 1,417.3 ሚሊዮን ብር፣ ቅርንጫፎቻቸውም ዘጠኝ መሆናቸውን ጠቁመው በተያዘው የበጀት ዓመት ቅርንጫፎቹን 15 ለማድረስ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ለአጠራጣሪ ብድሮች መጠባበቂያ ከተቀነሰ በኋላ ባንኩ 33.42 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ያገኘ ሲሆን የተለያዩ ወጪዎች ተቀንሰውና ዋስትና ማቅረብ ለማይችሉ ሴቶች ባንኩ ሊሰጥ ላሰበው ብድር አንድ ሚሊየን ብር ከተቀመጠ በኋላ የተገኘውን የተጣራ ትርፍ 20, 031,028 ብር ለባለአክሲዮኖች 10 በመቶ ትርፍ አከፋፍሏል፡፡
እናት ባንክ የመሥራት አቅም እያላቸው ለብድር ዋስትና ማቅረብ ለማይችሉ ሴቶች፣ የገንዘብ ዋስትና ለማግኘት ባደረገው ጥረት፣ ከግለሰቦችና ከድርጅቶች 5.3 ሚሊዮን ብር ቃል ስለተገባለት ተጠቃሚ ሴቶችን በንግድ ሥራ አዋጪነት ጥናትና በሌሎች የባንኩ የብድር መስፈርቶች መሰረት እያወዳደረ ሲሆን በቅርቡ ለተመረጡ ሴቶች ብድሩን እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ባንኩ የሚሰጠውን አገልግሎት ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ ባለው እቅድ፣ መሰረት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ግኝቶችን በመጠቀም፣ የኮር ባንኪንግ አሰራር ለመጀመር ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀና የበጀት ዓመቱ ከመገባደዱ በፊት በስራ ላይ ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የቦርድ ሊቀመንበሯ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ገልፀዋል፡፡



Read 3353 times