Saturday, 13 December 2014 10:41

የእንግሊዝ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎት ካታሎግ ኤግዚቢሽን ተካሄደ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

      በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ሱፐር ካቴክስና የእንግሊዝ ንግድና ኢንዱስትሪ በመተባበር ለሶስት ቀናት በኢሊሌ ሆቴል ያዘጋጁት የእንግሊዝ ላኪ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎት የካታሎግ ኤግዞቢሽን በጣም ጥሩ እንደነበር አዘጋጁና የቢዝነስ ሰዎች ገለፁ፡፡
የሱፐር ካቴክስ አባልና የኤግዚቢሽኑ አዘጋጅ ሚ/ር ጀምስ ኦ’ሲሊቫን፣ ኤግዚቢሽኑ በጣም የተሳካ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ “ከ350 እስከ 400 የቢዝነስ ሰዎች በኤግዚቢሽኑ ተሳትፈዋል፡፡ በቀን ከ100 ሰው በላይ ከጎበኘው እኛ ሥራ በዝቶብን (ቢዚ) ነበርን ማለት ነው፡፡ ይኼ ለእኛ ከጠበቅነው በላይ ነው” ብለዋል፡፡
የካታሎግ ኤግዚብሽኑን ሲጎበኝ ያገኘሁት ወጣት ነቢያት ዴሺ የተባለ የተለያዩ ቁሳቁሶች አስመጪ ኩባንያ ጄነራል ማናጀር ነው፡፡ ኤግዚብሽኑ ጥሩ መሆኑን የተናገረው ነቢያት፣ አሁን ከካታሎጉ ያገኘው ትንሽ ቢሆንም ምሪትና አገልግሎቶቹ በጣም ብዙ ስለሆኑ በሰጡት ሲዲ በኢ-ሜይል አድራሻቸው ሊያገናቸው አስቧል፡፡
አንተነህ የሚሰራው በኬሚካልና ላቦራቶሪ ዕቃዎች ላይ ነው፡፡ ወደ ኤግዚቢሽኑ የሄደው ጠቃሚ ነገር ባገኝ ብሎ ሲሆን ያያቸው ነገሮች ጥሩ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ የእንግሊዝ ዕቃ ጥራት ያለው ስለሆነ ዋጋው ውድ እንደሚሆን ገምቷል፡፡ ውድ ቢሆኑም ጥንካሬና ረዥም ዕድሜ ስላላቸው አልጠላቸውም፡፡ የእኛ አገር ገበያ ያልለመዳቸው ቢሆኑም፣ ዝም ብሎ ከመተው ሊሞክራቸው አስቧል፡፡ ወደ ፊት ግንኙነቱ ሲፈጠር የበለጠ ጥሩ እንደሚሆን ተስፋ ሰንቋል፡፡
አብዲ ደጀኔ የሕክምና ባለሙያ ነው፡፡ ለመ/ቤቱም ሆነ ከዚያ ውጭ ጠቃሚ ምርትና አገልግሎት ባገኝ ብሎ ነው ወደ ኤግዚቡሽኑ የሄደው፡፡ አብዲ በሌሎች አገሮች ኤግዚቢሽን ተሳትፎ ያውቃል፡፡ ይህ ኤግዚብሽን በአገራችን የተለመደ ባይሆንም ብዙ ጠቃሚነገሮች እንዳገኘበትና ግንኙነቱ ሲፈጠር የበለጠ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ብሏል፡፡
የእንግሊዝ ኤክስፖርተሮች ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶችና አገልግሎቶች የቀረቡት በአካል ሳይሆን፤ ከ180 በላይ ኩባንያዎች የሚያመርቷቸው ከ100ሺህ በላይ ውጤቶችና የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ምን እንደሆኑ ዝርዝር መግለጫ በያዘ ካታሎግ ነው፡፡
ኤግዚቢሽኑን የከፈቱት የኢንዱስትሪ ሚ/ሩ ክቡር አህመድ አብተውና በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ሚ/ር ግረጅ ዩሪ ሲሆኑ፤ በእንግሊዝ ኤክስፖርተሮችና በኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ መካከል ግንኙነት፣ ትስስርና ሽርክና በመፍጠር መስራት የኤግዚቢሽኑ ዓላማ እንደሆነ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
የእንግሊዝ ባለሀብቶች፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ውጤታማ እንደሆነ ተገንዝበው እንደ ዲያጐ ያሉና ሌሎችም ትላልቅ ኩባንያዎች ምርት መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ አሁን በሚፈጠረው የንግድ ትስስር፣ ሌሎች በርካታ ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለመሳብ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል - አምባሳደሩ፡፡የእንግሊዝ ኩባንያዎች በእርሻ፣ በሆርቲካልቸር (አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ) በንግድ፣ በሕክምና፣ በጤና ክብካቤ፣ በኢንጂነሪንግ፣ በኦቶሞቲቭ፣ በኮንስትራክሽን፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በቤት ቁሳቁስ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በሆቴል ዕቃዎች አቅርቦት፣ በችርቻሮ ንግድ፣ በአላቂና የቅንጦት ዕቃዎች፣ ኃይል በማመንጨት፣ በውሃና ፍሳሽ፣ በከባድ መሳሪያዎች፣ በኢንቫይሮመንት፣ በማዕድን፣ በምግብና መጠጥ፣ በግንባታ መሳሪያዎችና ዕቃዎች፣ በእንስሳት ሕክምና፣ በትራንስፖርት፣ በመገናኛ፣ በጤናና ውበት፣… በአጠቃላይ ከ31 በሚበልጡ ዘርፎች ከኢትዮጵያውያን ጋር ተባብሮ ለመስራት ወኪልና አከፋፋይ እንደሚፈልጉ ታውቋል፡፡
ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጁት ሱፐር ካቲክስና የእንግሊዝ ንግድ ኢንዱስትሪ ሲሆኑ፣ ሱፐር ካቲክስ በመላው ዓለም 122 የካታሎግ ኤግዚቢሽን አዘጋጅቶ 45ሺህ አዳዲስ የቢዝነስ ትብብሮች መፈጠሩን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጅት የሱፐር ካቲክስ አባል ሚ/ር ጀምስ ኦ.ሱልቫን ገልፀዋል፡፡


Read 1156 times