Print this page
Saturday, 13 December 2014 10:18

የኅትመትና የማሸግ ኢንዱስትሪው ዕድገት በጣም ዝቅተኛ ነው ተባለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

በኢትዮጵያ የህትመትና ማሸግ ኢንዱስትሪው በተለይም የህትመት ዘርፉ ረዥም ዕድሜ ቢኖረውም ዕድገቱ ኋላ ቀር በመሆኑ የተማሪዎች መማሪያ መጻሕፍት እንኳ ማተም እንዳልቻለ ተገለጸ፡፡
በሀገር ውስጥ በህትመትና ፓኬጂን የተሰማሩ ድርጅቶች ከውጪዎቹ ልምድ እንዲቀስሙ ፕራና ፕሮሞሽንና የሱዳኑ ኤክስፖ ቲም ከኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማህበር ጋር በመተባበር በሂልተን ሆቴል ባዘጋጁትና ለ3 ቀን በሚቆየው 5ኛው አፍሪ ፕሪንት ኤንድ ፓኬጂንግ ኤግዚቢሽን፣ የሁለቱ ዘርፎች እድገት በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ የህትመት ኢንዱስትሪው ከተመሰረተ መቶ ዓመት ያህል ቢሆነውም በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚያስችል ዕድገት አልፈጠረም ተብሏል፡፡
በዚህ ዘርፍ ላይ ብዙ የፕሮሞሽን ሥራ አልተሰራም ያለው የፕራና ፕሮሞሽን የኤግዚቢሽን ማናጀር፣ በኢትዮጵያ ት/ቤቶች የሚያገለግሉ የመማሪያ መጻሕፍት ወደ ኤስያ አገራት እየተላኩ  በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ውጭ ምንዛሬ እንከስራለን፡፡ ይህን ኤግዚብሽን ያዘጋጀነው በአንድ እርከን ከፍ ለማድረግ ነው በማለት ገልጿል፡፡
የሁለቱም ዘርፎች ዕድገት በጣም ዝቅተኛ መሆን የታወቀ ነው ያሉት የዕለቱ የክብር እንግዳና ኤግዚብሽኑን የከፈቱት የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ማቴሪያል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሜኤል ሃላላ፣ መንግስት፣ የግሉ ባለሀብትና ባለድርሻ አካላት ይህን ዘርፍ ለማሳደግ መትጋት አለባቸው ብለዋል፡፡
አገራችን በየዓመቱ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመግባት በምታደርገው ጥረት፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂና የጥሬ ዕቃ ፍላጎት እየጨመረ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ፍላጎታችንን ለማሟላት ዝቅተና ዋጋ ወደሚያቀርቡት የኤስያ አገራት ማተኮር ትተን አስፈላጊውን ሰው ኃይል፣ ቴክኖሎጂና ጥሬ ዕቃ እዚሁ ማሟላት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የተራቀቁ የህትመት መሳሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የካፒታል እጥረት፣ መሳሪዎቹን የሚያንቀሳቅስም ኢንዱስትሪውን የሚመራ ሰው ኃይል እጥረት፣ መንግስት ለዘርፉ ያለው ትኩረት ማነስ፣ … ከሚጠቀሱ ችግሮች ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ በህትመትና ማሸግ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች የካፒታል የሥልጠና፣ የቴክኖሎጂ … ድጋፍ ካልተደረገላቸው ወደፊት ኢንዱስትሪው፣ እጅግ የተራቀቁ ዘመናዊ መሳሪዎችን መግዛትና መሳሪያዎቹን ማንቀሳቀስ የሚችል የሰው ኃይል ማሰልጠን በሚችሉ ጥቂት ከበርቴዎች እጅ ይወድቃል የሚል ስጋት አለ፡፡
በኤግዚብሽኑ፤ 20 የአገር ውስጥና 20 የጀርመን፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ቤልጂየም፣ ጃፓን፣ ሕንድ፣ ሳዑዲ አረቢያና የግብፅ ድርጅቶች መሳተፋቸውና አህጉራዊ የህትመት ማህበር ለማቋቋም ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

Read 1524 times