Saturday, 13 December 2014 10:09

60 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክታቸውን ለምርጫ ቦርድ አሳወቁ

Written by  ማህሌት ሰለሞን
Rate this item
(1 Vote)

በምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡ 75 ፓርቲዎች 60ዎቹ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታቸውን ለቦርዱ ያሳወቁ ሲሆን የቦርዱ የመጨረሻ ውሳኔ እየተጠበቀ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደምሰው ባንቲ፤ 60 የሚደርሱ ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታቸውን ለቦርዱ እንዳስገቡ የገለፁ ሲሆን ምርጫ ቦርድ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ያስገቡትን ምልክት ገና ያልፀደቀ በመሆኑ የትኛው ፓርቲ ምን ምልክት እንደያዘ መናገር እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ምልክት ሊያስገቡ ስለሚችሉ ያንን ካስተካከልን በኋላ ይፋ እናደርጋለን ብለዋልም፡፡
የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሀም በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ለምርጫ ቦርድ ሁለት ምልክቶችን ማስገባቱን ጠቁመው፤ የቦርዱን ውሳኔ እየጠበቁ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ፓርቲያቸው ያስገባውን የምልክት አይነት  ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡
መድረክ በበኩሉ፤ በ2002 የተወዳደረበትን የእጅ መዳፍ ምልክት ማስገባቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በ2002 የተወዳደረበትን የአበባ ምልክት ለመወዳደሪያነት እንዳስገባ ገልጿል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋም፤ ፓርቲያቸው ለቦርዱ የጥላ፣ የመርከብ እና የተጨበጠ እጅ፣ በአጠቃላይ ሶስት የመወዳደሪያ ምልክቶችን ማስገባቱን ጠቁመዋል፡፡

Read 1244 times