Monday, 08 December 2014 14:43

14ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሁሉም ረገድ ተሳክቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ኃይሌ ወደ ቡና ኢንቨስትመንት ገብቷል
ከ2 ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በሁሉም ረገድ ስኬታማ እንደነበር ተገለፀ፡፡ ለ2ኛ ተከታታይ ዓመት መነሻ እና መድረሻውን በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ያደረገው የጎዳና ላይ ሩጫው በስፖርት ኤክስፖ፤ በዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ስብሰባ፤ በታላላቅ የኢትዮጵያ አትሌቶችና ዓለም አቀፍ የስፖርት ሰዎች የክብር እንግድነት በመታጀብ ድምቀት የተላበሰ ነበር፡፡ ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበርካታ ሚዲያዎችን ትኩረት ሳበ ሲሆን ብሊቸርስፖርት፤ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ድረገፅ፤ በእንግሊዞቹ ቢቢሲ እና ዘጋርድያን ዘገባዎች፤ በሲኤንኤን እና በሌሎች ዓለም አቀፍ የሚዲያ ድረገፆች በተለያዩ አቅጣጫዎች የዘገባ ሽፋን አግኝቷል፡፡ ሁሉም ዓለም አቀፍ ሚዲያዊች የጎዳና ላይ ሩጫው ማራኪ ድባብ ያለው እና ድምቀት የተላበሰ ዝግጅት ብለው ስኬቱን አወድሰዋል፡፡ በ14ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ የ13 አገራት አምባሳደራትእና ሌሎች የውጭ አገር እስከ 400 ስፖርተኞች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በዋናው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ወደ 500 የሚሆኑ አትሌቶች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ 40 ሺህ ተሳታፊዎች  ሮጠውበታል፡፡
በሌላ በኩል ከጎዳና ላይ ሩጫው ተያይዞ በተደረገ የገቢ ማሰባሰብ ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱ ታውቋል፡፡ ይህ ገቢም ለአራት ግበረሰናይ ድርጅቶች የሚከፋፈል እንደሆነ ታውቋል፡፡ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል የአየርላንድ ቅርንጫፍ ቡድን 150ሺ ዩሮ በመሰብሰብ ስኬታማ ሲሆን በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ከ50 በላይ ስፖርተኞችን አሳትፎ ነበር፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በውድድሩ ላይ የተለያዩ ቡድኖችን በማሳተፍ ከ600ሺ ዩሮ በላይ የሰበሰበው ኦርቢስ አየርላንድ የዓይን ህክምናን የሚደግፍ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡ የክብር እንግዳ የነበረችው የኬንያዋ ማራቶኒስት ኤድና ኪፕላጋት በሰጠችው አስተያየት በውድድሩ ሁሉም ተሳታፊ ደስተኞች መሆናቸው አስቀንቶኛል ብላለች፡፡‹‹ አንዳንዱ በርምጃ፤ ሌላው በሶምሶማ ሁሉም የቻለውን ሲሮጥ ማየት አስደስቷታል፡፡ ተመሳሳይ ዝግጅት በኬንያ እንዲኖርም ተመኝታለች፡፡
በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው 500 አትሌቶች የተሳተፉበትን ዋና ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ያሸነፉት አትሌቶች የቀድሞ አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ ሁለቱም ሻምፒዮኖች በዓለም አቀፍ የጎዳና እና የትራክ ውድድሮች ልምድ ያካበቱ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ በሴቶች ውዴ አያሌው ለሶስተኛ ጊዜ አሸንፋ በውድድሩ 14 ዓመት ታሪክ ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግባለች፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሻምፒዮናነት ሃትሪክ ማለት ነው፡፡ ውዴ አያሌው በ8ኛው እና በ9ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር አሸናፊ ነበረች፡፡ በወንዶች ደግሞ አዝመራው በቀለ ለሁለተኛ ጊዜ ከ5 ዓመት በኋላ ማሸነፍ ችሏል፡፡ አዝመራው የመጀመርያ ድሉን በ9ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር  አስመዝግቧል፡፡ የ14ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሸናፊዎች  ሰዓት ግን ከመወዳደርያው ጎዳና አስቸጋሪነት የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡
በውድድሩ የ14 አመታት ታሪክ ያዘገመ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ውዴ አያሌው በ34 ደቂቃዎች ከ4 ሰከንዶች በመሮጥ ስታሸንፍ አዝመራው በቀለ  በ30 ደቂቃዎች ከ12 ሰከንዶች 10 ኪሎሜትሩን ጨርሶታል፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር  መሳተፍ በጣም ያስደስተኛል ያለው አዝመራው በቀለ፤  የፌደራል ማረሜያ ክለብ አትሌት ነው፡፡ ከታላቁ ሩጫ በኋላ  ወደትራክ ውድድሮች በመመለስ  በቤጂንጉ 15ኛው  የዓለም  አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ውጤታማ ለመሆን ፍላጎት አለኝ ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብን የወከለችው ውዴ አያሌው በበኩሏ፤  በታላቁ ሩጫ ውድድር ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ ማሸነፏ  እንዳስደሰታት ገልፃ በዓለም አቀፍ ደረጃ  የመጣሁበት ውድድር ስለሆነ ውጤቱን እጅግ አከብራለሁ ብላለች፡፡
በሌላ በኩል  የዓለማችን የረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ ሯጭ ብሎ ከሰየመው ኃይሌ ገብረስላሴ ጋር ቃለምልልስ ያደረገው ቢቢሲ የኢትዮጵያ እጅግ ታዋቂ ሰው መሆኑን በመጥቀስ አሁን ስኬታማ የቢዝነስ ሰው ሆኗል በሚል ሰፊ ዘገባ ሰርቷል፡፡ ሩጫ በማሸነፍ እና ባለማሸነፍ ውጤቱ ይለካል፤ በኢንቨስትመንት ስራ ግን አቅደህ ውጤቱን መጠባበቅ ግድ ይላል ብሎ መናገሩን ያወሳው የቢቢሲ ሪፖርታዥ አፍሪካን መረዳት የሚቻለው ገንዘብ በመለገስ አይደለም ጠቃሚ ሃሳቦችን በማስፋፋት ነው ማለቱንም አስፍሮታል፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ ኢንቨስትመንቱን ከሩጫ ስፖርት ባገኘው ገቢ ባለብዙ አገልግሎት ያላቸውን ህንፃዎች በመገንባት እንደጀመረ ያስተወሳው ዘገባ፤ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በስኬታማነት ሲሰራ ቆይቶ አሁን ደግሞ መሬት ገዝቶ ወደ ቡና ማልማት ግብርና ውስጥ መግባቱን ተንትኗል፡፡ 1500 ሄክታር መሬት በሊዝ የገዛው ኃይሌ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት በ500 ሄክታሩ ላይ ቡና በማብቀል ኦርጋኒክ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ገበያውን ለማጥለቅለቅ ማሰቡን አመልክቷል፡፡  ከቡና ማልማቱ ባሻገር በተፈጥሮ ሃብት እጅግ በበለፀገችው ኢትዮጵያ ካሉት የኢንቨስትመንት እድሎች አንዱ በሆነው የማእድን ቁፋሮ ላይም ትኩረት ማድረጉን ገልጿል፡፡
===============

የዴይሊ ሜል ጥያቄዎች ለኃይሌ ገብረስላሴ
በስፖርት ጀግናህ ማነው
ምሩፅ ይፍጠር፡፡ በሞስኮ ኦሎምፒክ በረጅም ርቀት ባገኛቸው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ወደ ሩጫ ለመግባት ተምሳሌት ሆነውኛል፡፡
ስፖርተኛ ባትሆን ኖሮ
የፈጠራ ስራዎች አንደዝንባሌ እደሰትባቸው ነበር፡፡ ሰዓሊነት፤ አነፂነትም እወዳለሁ፡ ሯጭ ባልሆን አርቲስት ነበርኩ፡፡
ከታላቅ ስፖርተኞች ብትሆን የምትፈልገው
እግር ኳስ መመልከት እወዳለሁ፡፡ በእድሜዬ የማውቀው ምርጥ ተጨዋች ደግሞ ማራዶና ነው፡፡
በሩጫ የማትረሳቸው ምርጥ እና መጥፎ ገጠመኞች
በሲድኒ ኦሎምፒክ ከፖል ቴርጋት ያደረገነው ፉክክር ምርጡ ነው፡፡ በ2007 የለንደን ማራቶን  ውድድር አቋርጦ ለመውጣት መገደዴ መጥፎ ትዝታ ነው፡፡
የማይረሳህ ምርጥ ምክር
‹‹ተስፋ እንዳትቆርጥ›› በማለት አባቴ የመከረኝን ነው፡፡ ይህ ምክር በየውድድሩ እንደ ትልቅ የሞራል ስንቅ ተጠቅሜበታለሁ፡፡
ከውድድር በፊት የሚወደው ምግብ እና ምን ማብሰል ይችላል
ከውድድር በፊት ስፓጌቲና ማናቸውም የፓስታ ምግብ ምርጫዬ ነው፡፡
ላዛኛ እና ፓስታ አጣፍጬ እሰራለሁ፡፡  
ተወዳጅ የእረፍት ቦታው
አናብስት እና ዝሆኖች የሚገኙበትን የደቡብ አፍሪካው ክሩገር ፓርክ
ፊልም ቢተውን ደስ የሚለው
እንደ ሚር ቢን

Read 2216 times