Monday, 08 December 2014 14:31

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰጠው ምላሽ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“የፀሐይ ብርሃንን ጭምር ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል እንቀይራለን”

ህዳር 13 ቀን 2007 ዓ.ም ለንባብ በበቃው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዕትም ላይ፤የነፋስ ተርባይን የኤሌክትሪክ ሃይልን በተመለከተ ያወጣችሁት ዘገባ ስህተት ነው፡፡ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ በሄደ ቁጥር የነፋስ ኃይልን ብቻ ሳይሆን የፀሐይ ብርሃንንም ወደ ኤሌክትሪክ ኢነርጂ እንቀይራለን፡፡
 በእርግጥ ከውሃና ከንፋስ ኃይል ውዱ የንፋስ ኃይል ነው፡፡ ነገር ግን ከነፋስ ሃይል ማመንጨት የጀመርነው የሃገራችንን ኢኮኖሚ ጭምር ለማልማት የሚያስችል አቅም እየፈጠርን ስለሄድን ነው፡፡ በውሃ ሃብታችን እስከ 50 ሺ ሜጋ ዋት  ማልማት የምንችል ሲሆን በንፋስ ኃይላችን ደግሞ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ማመንጨት እንችላለን፡፡
 ይሄን ሃብት ደረጃ በደረጃ በመጠቀማችን እንኳንስ ዜጐች፣የኛን እድገት የማይፈልጉትም ጭምር አዎንታዊ ምላሽ ላይ ተጋንኖ እንደቀረበው እየሰጡ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አገሪቱ የንፋስ ኃይል በመጠቀሟ በጋዜጣው ላይ እንደ ከሰረች ተደርጎ የቀረበው የተጋነነ ነው፡፡ እንደውም “ውዱን ሃብት ጭምር ለማልማት የቻለች፣ እያደገች ያለች ኢትዮጵያ” ብላችሁ ነው መዘገብ ያለባችሁ፡፡
በኃይል በኩል ገና ሊለማ የሚችል ብዙ ሃብት አለን፡፡ በአሁን ሰዓት 2268 ሜጋ ዋት ብቻ ነው ያለን፡፡ ከዚህ ውስጥ 171 ሜጋ ዋት የምናመርተው ከንፋስ ሲሆን በቀጣይ ሊለማ የሚችል ከውሃ እስከ 50 ሺ ሜጋ ዋት፣ ከነፋስ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት እንዲሁም ከምድር እንፋሎት ከ10 ሺ ሜጋ ዋት በላይ እምቅ ሃብት አለን፡፡
ነገር ግን ቀደም ባሉት ዓመታት በአብዛኛው በውሃ ላይ አተኩረን የቆየነው፣ ውሃ በርካሽ የገንዘብ አቅም መልማት ስለሚችል ነው፡፡ አሁን ግን  የሃገራችን  ኢኮኖሚ በማደጉ በውሃ ላይ ጥገኛ ከምንሆን ከንፋስም ጭምር ኃይል እያመነጨን ለሃገራችን ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል እናቀርባለን፡፡ በአሁኑ ወቅት እየጨመረ የመጣውን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማርካት ከንፋስ ሃይል ማመንጨት የግድ ነው፡፡ ሃገሪቱ ይሄን ሃይል የመፍጠር አቅም ስላጐለበተች ነው ወደዚያ የተገባው፡፡ በመቀጠል  ደግሞ ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት በዝግጅት ላይ ነን፡፡
አቶ ምስክር ነጋሽ፤
የውጭ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ
f

Read 2132 times