Monday, 08 December 2014 14:27

የሞባይል ሂሣብ በኤሌክትሮኒክስ መሙላት በቅርቡ ይጀመራል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

       ኢትዮ ቴሌኮም የተሰረቁና በኮንትሮባንድ የሚገቡ ስልኮች አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ የሚያደርግ ስርአት ሊተገብር እንደሆነ ሰሞኑን አስታውቋል፡፡ ማናቸውም ስልኮች በህጋዊ መንገድ ቀረጥ ተከፍሎባቸው አገልግሎት እንዲሰጡ  በሚል ዓላማ ሥርዓቱ እንደሚተገበር ያስታወቁት የኢትዮ ቴሌኮም የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም አህመድ፤ ከዘመድም ሆነ በሌላ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ስልኮች ቀረጥ ተከፍሎባቸውና በሲስተሙ ተመዝግበው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚያደርግ ስርአት ነው የሚዘረጋው ብለዋል፡፡
የተሰረቁ ስልኮችም ከመጀመሪያው ተመዝጋቢ ባለቤት ውጪ ሌላ ሰው እንዳይጠቀምባቸው የሚያደርግ ስርአት ይሆናል ያሉት ኃላፊው፤ መቼ ተግባራዊ እንደሚደረግ  ገና አልተወሰነም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮ  ቴሌኮም በአገልግሎት ላይ ያለውን የወረቀት ካርድን ያስቀራል የተባለውን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ሂሣብ የመሙላት አሠራር ከሶስት ወር በኋላ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ሰባት ማዕከላት በሙከራ ደረጃ አገልግሎቱ ሲሰጥ አንዳንድ የሚስተካከሉ ነገሮች መገኘታቸውንና ችግሮቹ ተስተካክለው በየካቲት ወር ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮ ቴሌኮም የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
 ኢትዮ - ፓፕ የተሰኘው አገልግሎት ሲጀመር በአገሪቱ ያለው ደንበኛ ሁሉ አጠቃቀሙን እስኪገነዘብ ድረስ አሁን በስራ ላይ ያለው የካርድ አገልግሎት ለአንድ ዓመት ያህል  ጎን ለጎን ይሠራበታል ተብሏል፡፡
በየካቲት ወር አገልግሎቱ ሲጀመር በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑ ወደ መቶ የሚጠጉ አገልግሎት ሰጪ ማዕከላት እንደሚዘጋጁም አቶ አብዱራሂም አስታውቀዋል፡፡
በሂደት ካርዱን የሚያስቀረው አዲሱ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ፤ከ5 ብር ጀምሮ በተፈለገው የገንዘብ መጠን የአየር ሰአት መግዛት የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ሰሞኑን ከካርድ መሙላት ጋር በተገናኘ የተከሰተው ችግር ከኔትወርክ ጋር የሚያያዝ አይደለም ያሉት ኃላፊው፤ የኢንፎርሜሽን ሲስተም አገልግሎት ላይ ባጋጠመ እክል እንደተከሰተና በቅርቡ በላቀ አገልግሎት ስለሚተካ ችግሩ እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡

Read 2135 times