Print this page
Monday, 08 December 2014 14:26

ይድረስ ለአዲስ አድማስ፣ ይድረስ ለመብራት ኃይል ኢንጂነር አይናለም አረጋዊ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“ኤሌክትሪክ በየሰዓቱ ይጠፋል” በሚል ርዕስ ቅዳሜ ህዳር 13 ቀን 2007 ዓ.ም በታተመው ጋዜጣችሁ የወጣውን ፅሁፍ ከአነበብኩት በኋላ ይህንን ሃሳብ ለመሰንዘር ወደድኩኝ፡፡
ፅሁፉ ሙሉ በሙሉ ጉዳዩን የፈተሸ ባይሆንም፣ መደምደምያውም ትክክል ነው ብዬ ባላምንም እንደዚህ ዓይነት አብይ ጥያቄ ይዞ በመነሳቱ ግን አድንቄዋለሁ - በሁለት ምክንያት፡፡ በድፍረትና በተቆርቋሪነት የቀረበ በመሆኑ፣ እንዲሁም በተቻለ መጠን በመረጃ በመደገፉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ነገሮች በብዙ የስራ ዘርፎች የማይታዩ ባህሪዮች ናቸውና፡፡
ወደ አስተያየቴ ስገባ፣ በመጀመሪያ በፅሁፉ በተነሱት አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ የራሴን ላክልና በመደምደሚያው ያልተስማማሁበትን ምክንያት አቀርባለሁ፡፡ ከዚያም የራሴን ለየት ያሉ መደምደሚያዎች ደግሞ አስከትላለሁ፡፡ በመሰረቱ በፅሁፉ የቀረቡ ንፅፅሮች ትክክል ናቸው፡፡ ያም ብቻ አይደለም፡፡ ንፋስ በየሰከንዱ የሚለዋወጥ ስለሆነ፣ የንፋስ ጄኔሬተሮች የሚያመነጩት ኃይል በጣም ተቀያያሪ ነው፡፡ ይህም በኦፕሬሽን ላይ ጭምር በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ ከዚህም ሌላ የንፋስ ጀነሬተሮች በሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ መግነጢሳዊ ስበታቸው ከመረቡ የተለየ ስለሆነ ለሲስተሙ ጥንካሬና (stability) በአደጋ ጊዜ ሲስተሙን ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ አያግዙም፡፡ ያም ሆኖ ግን የንፋስ ኃይል ማልማት ተቀባይነት ያገኘበት ጠንካራና አሳማኝ ምክንያቶች አሉት፡፡
በመጀመርያ የንፋስ ኃይል ለማልማት በጣም ፈጣን መሆኑ ነው፡፡ በተለይም ከውሃ ኃይል ጋር ሲነፃፀር የሚወስደው ጊዜ በጣም አጭር ነው ሊባል ይችላል፡፡ አንድን የንፋስ ኃይል ጣቢያ ለማልማት እንደ ሁኔታው ከ16-19 ወራት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩልም አንድን መካከለኛ ወይም ከፍተኛ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለማልማት ቢያንስ ቢያንስ 6 እና 8 ዓመት ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ የከፍተኛ ኃይል የማምረቻ ጊዜያቸው ተመጋጋቢ መሆኑ ነው፡፡ የአንዱ ምርት ዝቅ በሚልበት ወቅት የሌላኛው ምርት ከፍ ይላል፡፡ የውሃ ሃብታችን ግንቦት ወር አካባቢ ዝቅተኛ ሲሆን የንፋስ መጠኑ ደግሞ በዚህ ወር አካባቢ ይበረታል፡፡ ስለዚህም ጥሩ የሆነ የኃይል አቅርቦት ቅይጥ ይኖረናል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም እስከ አሁን የለሙት የንፋስ ኃይል ጣቢያዎች ከከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ማእከላት በጥሩ ቅርበት መሆናቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚዘረጋው የኃይል ማስተላለፍያ መስመር ወጪ በንፅፅር አነስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የንፋስ ኃይል ላይ የወጣው ኢንቨስትመንት እንደ ፅሁፉ አቀራረብ ብክነት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ከዚህ ውጭ ደግሞ አገራችን በከባቢያዊ ወይም በአረንጓዴ ልማት የበኩሉዋን አስተዋፅኦ ለማድረግ የገባችው ፖለቲካዊ ቃል መረሳት የለበትም፡፡
እንደዚያም ሆኖ ፅሁፉን በበጎ በመረዳት የሚከተሉት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው - በሚመለከታቸው አካላት፡፡ አንደኛ፣ ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው የኃይል ልማት ኢንቨስትመንት “ፖርትፎልዮ” ምን መምሰል አለበት? ይህም ማለት የንፋስ ድርሻ (ከቴክኒካዊም ሆነ ከኢኮኖሚያዊ መመዘኛዎች አንፃር) ስንት በመቶ መሆን አለበት ብሎ መወሰን ነው፡፡
ሁለተኛ፣ አሁን ያለው ጠቅላላ የሲስተሙ ኦፕሬሽን ላይ የንፋስ ኃይል ጣቢያዎች ባህሪይ ምን ይመስላል? በጠቅላላ የሲስተሙ መደላድል (stability) ላይስ ያለው ሁኔታ እንዴት ነው? የሚሉት ናቸው፡፡ ከዚህ ዋናው አርእስት ውጭ ስለ መብራት መቆራረጥ ለማንሳት ያህል ደግሞ ችግሩ በኃይል መቆራረጥ ላይ ብቻ የተወሰነ አድርጎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል፡፡
 መቆራረጡ በመብራት ኃይል አጠቃላይ ሲስተም እቃዎች ላይ የማርጀት ሂደት (depreciation) ከሚገባው በላይ እንዲፋጠን እንደሚያደርግ መታወቅ አለበት፤ ተገቢው ገቢ እንዳይሰበሰብ ከማድረጉም በተጨማሪ፡፡ በብዙ ባለሙያዎችና ባለሀብቶች እንዲሁም ድርጅቶች ተደጋግሞ እንደተገለፀውም፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በተወሰነ መጠን የማቀዝቀዝ ውጤቱ ሳይረሳ፣ እነዚህ ከፍተኛ ችግሮች በዘርፉና በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳይ ለመቅረፍ የኃይል ዘርፋችን የችግር አያያዝ (Crisis/Problem Management) የተዳከመበትና የተዘበራረቀበት ምክንያት ምንድን ነው? ወይም በቀላል አማርኛ ችግሮቹን በተረጋጋ እጅ ለመፍታት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

Read 1803 times
Administrator

Latest from Administrator