Saturday, 29 November 2014 11:36

በኢትዮጵያ የግል ባንክና ኢንሹራንስ ከተመሰረቱ 20 ዓመት ሞላቸው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ለ7 በጎአድራጎት ድርጅቶችና ለአንድ ግለሰብ 2.3 ሚ. ብር ድጋፍ አደረጉ
በኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ በጣም ዝቅተኛ ነው

        በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቀደምት የሆኑት የግል ባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያ የተመሰረቱበትን 20ኛ ዓመት እያከበሩ ነው፡፡
ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ የሚከተለው ፖሊሲ ነፃ ኢኮኖሚ እንደሚሆን የተገነዘቡ ጥቂት ባለራዕይ ምሁራን የመሰረቷቸው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባን አክሲዮን ማኅበራት 20ኛ የምስረታ በዓላቸውን እያከበሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራውና የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀጋዬ ከምሲ 20ኛ የምስረታ በዓሉን አስመልክተው በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በማንኛውም ነገር ጀማሪ መሆን ከባድ ፈተናና ችግሮች እንዳሉት ጠቅሰው፣ ባለፉት 20 ዓመታት ያጋጠማቸውን የተለያዩ መሰናክሎችና ችግሮች በዘዴ፣ በትጋትና በቆራጥነት አልፈው አሁንም በግል ኢኮኖሚው ውስጥ ቀዳሚ መሆናቸው በጣም ከፍተኛ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ፀጋዬ የኩባንያቸውን ስኬት ሲገልፁ፡፡ በ12 ሰራተኞች ጀምረው ዛሬ 380 መድረሳቸውን ከአንድ ቅርንጫፍ ተነስተው አሁን 34 ቅርንጫፎች፣ 3 አገናኝ ቢሮዎችና ከ300 በላይ የሽያጭ ወኪሎች እንዳሉት በቅርቡ ያስመጧቸውን 2 ዘመናዊና ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ክሬኖች ጨምሮ 4 የተጎዱ መኪኖች ማንሻ ክሬኖች እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የ19 ሚሊዮን ብር መግዛታቸውንና የኩባንያው የተከፈተ ካፒታል 120 ሚሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ባንካቸው ጠንካራ የህዝብ መሰረት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንኑ የህዝብ አመኔታ መሰረት ይበልጥ ለማጠናከር የተለያዩ ዘዴዎችን ቀይሰው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የአንድ ባንክ ጥንካሬ የሚለካው በሁለት ነገሮች ጠንካራ ሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ነው፤ ያሉት አቶ ፀሐይ ዘንድሮ ማሻሽ ከተባለ የእንግሊዝ የኤቲ ኤም ኩባንያ ጋር የ3.5 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት አድርገው፣ ባደጉት አገሮች በቀዳሚነታቸው የሚታወቁ ባንኮች በሚጠቀሙበት ዩኒቨርሳል ባንክ ፊዩዥን በተባለ እጅግ ዘመናዊ ኮር ባንኪንግ ሲስተም አብዛኞቹን ቅርንጫፎቻቸውን ማገናኘታቸውንና አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ባንኩ ከ20 ዓመት በፊት በ486 ባለራስ መስራቾች፣ በ24.2 የተከፈለ ካፒታል መቋቋሙን ጠቅሰው ዛሬ የተከፈለ ካፒታል 1.4 ቢሊዮን ብር የባለ አክሲዮኖች ቁጥር ከ3, 300 በላይ መድረሱን፣ ተቀማጭ ካፒታል 17 ቢሊዮን ብር በላይ ከ10 ቢሊዮን በላይ ለተለያዩ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ብድር መስጠቱን ጠቅላላ ሀብቱ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ማስገኘቱን (ዘንድሮ ብቻ ከ830 ሚሊዮን በላይ) ማትረፉን፣ በአንድ ቅርንጫፍ ጀምሮ 157 ቅርንጫፍ መድረሱን፣ በጥቂት ሰራተኞ ጀምሮ አሁን ከ5 ሺህ በላይ እንዳሉትና የ3.4 ቢሊዮን ቦንድ በመግዛት ከግል ባንኮች ቀዳሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በ20 ዓመት ውስጥ ምን ያህል አዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎት አመጣችሁ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ፀጋዬ በፊት ከነበረው ምንም የተለየ አዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዳላቀረቡ ጠቅሰው፣ አዲስ አገልግሎት ለማቅረብ ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ብዙ ካፒታል፣ በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል ፓኬጆቹን የሚያስተዳድር ሕግ፣ … ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የኢንሹራንስ ኢኮኖሚው አዲስ አገልግሎቶችን ለመሸከም አቅም አላዳበረም፡፡ እነዚህ ነገሮች ባልተሟሉበት አዲስ አገልግሎት መጀመር በጣም ከባድ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ቁጥር በጣም ትንሽ ነው፡፡ ይህን ቁጥር ለማሳደግ ምን ሰራችሁ? የተባሉት አቶ ፀጋዬ ጥያቄው በጣም ትክክለኛ መሆኑን አምነው፣ የሕይወት ኢንሹራንስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሰጠው አጠቃላይ ኢንሹራንሶች ከ5-7 በመቶ መሆኑንና ይህ አሃዝ ከማንኛውም አገር ጋር ሲነፃፀር በጣም አነስተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ከበርካታ ዓመታት በፊት ጀምሮ ተንሰራፍቶ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው በኩባንያ የህይወት ኢንሹራንስ 40 በመቶ፣ በደቡብ አፍሪካ ከ50 በላይ በርካታ ያደጉ አገሮች ከ70 በመቶ በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዋናው ችግር የኢንሹራንሶች ኩባንያዎች ለሕይወት ኢንሹራንስ ትኩረት ያለመስጠት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ በየዓመቱ ሰራተኞቻችን በዚህ ዘርፍ ይሰለጥናሉ፡፡ ነገር ግን ለመሸጥ ወደ ህዝቡ ሲሄዱ የሚያበረታታ ነገር አያዩም፡፡
የሽያጭ ሰራተኞች ገቢ ደግሞ በሸጡት መጠን ስለሆነ ተስፋ ቆርጠው ይተዋሉ፤ እኛም አናበረታታም ብለዋል፡፡ እያደገ ለወደፊት ግን የተለየ ሁኔታ እያየን ነው ያሉት አቶ ፀጋዬ የሰው ገቢ የተማረ ሰው ቁጥር እየጨመረ ሲሄድና “እግዜር ያውቃል” የሚል ሰው ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድ የአገራችንን የሕይወት ኢንሹራንስ ሁኔታ ይቀይራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን በማለት አስረድተዋል፡፡
 እህትማማቾቹ ኩባንያዎች፣ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመውጣት ረገድ የሚያኮራ ስም እንዳላቸው ጠቅሰው በ10ኛው ዓመት በዓላቸው እንዳደረጉት ሁሉ በ20ኛው በዓላቸውም ለ7 በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ለአንድ ታዋቂና አቅመ ደካማ ግለሰብ የ2.3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ መሰረት 600 ሺህ ብር በማግኘት አንበሳውን ድርሻ ያነሳው፣ መቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ሲሆን፣ 500 ሺህ ብር በመቀበል ቀጣይ የሆነው ሃምሊን የፌስቱላ ሆስፒታል ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል እያንዳንዳቸው 300 ሺህ ድጋፍ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ድርጅትና አነስሞስ ነስብ ፋውንዴሽንም ናቸው፡፡
150 ሺህ ብር ድጋፍ የተደረገላቸው ደግሞ አበበች ጎበና የህፃናት ክብካቤና ልማት ማኅበር፣ ጆይ እና ነህምያ የኦቲዝም (የአዕምሮ ዘገምተኞች) ማዕከል ሲሆኑ ከታዋቂ ግለሰቦች ደግሞ ለታዋቂው አትሌት ለሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ 150 ሺህ ብር ተለግሰዋል፡፡   

Read 2712 times