Saturday, 29 November 2014 11:35

ዳሽን ባንክ የአሜሪካ ኤክስፕረስ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ የካርድ ክፍያን አስቀድሞ የጀመረውን ዳሽን ባንክ፣ ዛሬ ደግሞ ከአሜሪካው ኤክስፕረስ ጋር ባደረገው ስምምነት የኤክስፕረስ ካርድ የያዘ ሰው በኢትዮጵያ አገልግሎት ማግኘት ጀመረ፡፡ የምንሰጠው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ጥሬ ገንዘብ  ሳይዝ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሰው ዓለም አቀፍ ካርድ ከያዘ የእኛን ኤቲ ኤም በመጠቀም በውጭ ካለው ሂሳቡ ገንዘብ ማውጣት ይችላል ያሉት የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ወ/ሥላሴ በኢትዮጵያ ጥሬ ገንዘብ የማይጠቀም ህብረተሰብ ለመፍጠር የተነሳንበት ዕቅድ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ስለሆነ በአጭር ጊዜ እውን እንደምናደርግ ተገንዝበናል ብለዋል፡፡ የአሜሪካን ኤክስፕረስ ሜርቻንት ካርድ የያዘ ሰው ወይም ቱሪስት በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሳምንቱን ሙሉ 24 ሰዓት በሱፐር ማርኬቶች፣ ካፌና ሬስቶራንቶች ሆቴሎች… የፈለገውን ዕቃና አገልግሎት መግዛትም ከመቻሉም በላይ ከዳሽን ኤቲ ኤም ገንዘብ ማውጣት (መመንዘር) ይችላል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ያ ሰው ጥሬ ገንዘብ ይዞ ባለመምጣቱ የፈለገውን ነገር ከመግዛት የሚያግደው ነገር የለም፤ ጥሬ ገንዘብ ይዞ ሲዘዋወር ከሚደርስበት የደህንነት ስጋት ነፃ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በካርድ መገበያየት ጥቅሙ ለገዥ ብቻ ሳይሆን ለሻጭ ጭምር እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ገዢው ገንዘብ ያልቅብኛል የሚል ስጋት ስለሌለበት፣ ያለገደብ የሚፈለገውን ዕቃ ወይም አገልግሎት ይገዛል ነጋዴውም ብዙ ዕቃ ወይም አገልግሎት ይሸጣል በማለት ገለፀዋል፡፡
የአሜሪካ ኤክስፕረስ በክፍያ ኩባንያነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በደህንነት፣ በአገልግሎትና በግለሰብ እውቅና እጅግ የተጠና ኃይለኛ ብራንድ ነው ያሉት ም/ፕሬዚዳንትና ጄነራል ማናጀር፣ በቱርክ የካርድ አገልግሎት ሽርክና በመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ የአሜሪካ ኤክስፕረስ ተወካይ ሚ/ር አንድሪው ስትዋሪት አሜሪካን ኤክስፕረስ ከተቋቋመ 160 ዓመታት ማስቆጠሩንና በመላው ዓለም 100 ቢሊዮን ኤክስፕረስ ካርድ ተጠቃሚ እንዳላቸው በኢትዮጵያም ከዳሽን ባንክ ጋር ተባብረው በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡  

Read 1979 times