Saturday, 22 November 2014 12:54

‹‹በጋራ እየሮጥን በጋራ እንደሰት››

Written by 
Rate this item
(0 votes)

          14ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነገ 40ሺ ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ ይካሄዳል፡፡ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫውን ከማካሄዱ በፊት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሰሞኑን ውድድሩን ያጀቡ የተለያዩ ዝግጅቶች ነበሩት፡፡ የመጀመርያው ባለፈው ረቡዕ በኤግዚብሽን ማእከል የተከፈተው የስፖርት ኤክስፖ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ስብሰባም ተስተናግዷል፡፡ የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ስብሰባ ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በቀነኒሳ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ መስተንግዶውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከታዋቂው የአትሌቲክስ ስፖርት ፎቶግራፈር ዢሮ ሚሹዙኪ፤ ከቀነኒሳ በቀለ እና ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር በመተባበር አከናውነዋል፡፡ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት  ከ10 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ 29 የስፖርት ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ከመካከላቸው ከኦስትሪያ ፤ከዩክሬን፤ ከሮማንያ ፤ከፈረንሳይ፤ ከደቡብ ኮርያ፤ ከጃፓን፤ ከእንግሊዝ ከጣሊያን ከኬንያ እና ሌሎች የዓለም ክፍሎች የመጡ ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡

ባለፈው ረቡእ በቀነኒሳ በቀለ ሆቴል በተዘጋጀላቸው የእራት ግብዣ ላይ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች እና ሊቀመንበር ኃይሌ ገብረስላሴ ባሰማው ንግግር አትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያን ለዓለም ለማስተዋወቅ ሁነኛ አማራጭ እንደሆነ ትተዘባላችሁ ሲል ተናግሯል፡፡ በዚሁ የእራት ግብዣ ላይ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ለእንግዶቹ የአገር ልብስ ስጦታ ያቀረበ ሲሆን የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ተወካዮች በበኩላቸው ኢትዮጵያ በስፖርቱ የ65 ዓመታት ታሪክ ማሳለፏን ጠቅሰው የታላላቅ አትሌቶች መገኛ በሆነች አገር ለምታዘጋጅቱ ትልቅ ውድድራችሁ እናመሰግናለን በማለት ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡
14ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬ በጃንሜዳ አካባቢ እስከ 4ሺ ህፃናትን በማሳተፍ በሚካሄደው ከ500 ሜትር እስከ 2000 ሜትር ውድድር ነው፡፡ ነገ ጠዋት በጃንሜዳ አካባቢ ውድድሩን የሚያስጀምሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አባዱላ ገመዳ ሲሆኑ የእለቱ የክብር እንግዶች እንግሊዛዊው የትራያትሎን አትሌት አሊስተር ብራውንና ኬንያዊቷ ማራቶኒስት ኤድና ኪፕላጋት አብረዋቸው ይኖራሉ፡፡ በዋናው የአትሌቶች ውድድር 40 ክለቦችን የወከሉ ከ600 በላይ አትሌቶች የሚፎካከሩ ሲሆን ፤ ለአንደኛ 40ሺ ለሁለተኛ 25 ሺ እንዲሁም ለሶስተኛ 12ሺ 500 ብር በሁለቱምፆታዎች በሽልማት ይበረከታል፡፡  ከ15 አገራት የመጡ 300 ስፖርተኞች ከ40ሺው ስፖርተኛ መካከል ሲገኙበት የ13 አገራት አምባሳደራት በኢትዮጵያን ኤርላይንስ አዋርድ ለማሸነፍ ይሽቀዳደማሉ፡፡ትናንት በሂልተን ሆቴል በተሰጠው መግለጫ ላይ  በ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው በጋራ እየሮጥን በጋራ እንደሰት በማለት መልዕክት ያስተላለፈው ኃይሌ ገብረስላሴ፤ የውድድሩ እድገት ገና ይቀጥላል ብሏል፡፡ የክብር እንግዶች ከሆኑት አንዷ ኬንያዊቷ ኤድና ኪፕላጋት ኃይሌን ከ16 ዓመቷ ጀምራ እንደምታውቀው ገልፃ በምታደንቀው አትሌት የተዘጋጀ ውድድርን ለማስጀመር መጋበዟ ታላቅ ክብር ነው ብላለች፡፡ ኤድና ኪፕላጋት ከ12 በላይ ማራቶኖችን ያሸነፈች አትሌት ስትሆን  በሀለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በማራቶን አከታትላ በማሸነፍ ሁለት የወር ሜዳልያዎች የተጎናፀፈች እና ዘንድሮ የለንደን ማራቶንን ለማሸነፍ የበቃች ናት፡፡ በሌላ በኩል ሌላው የክብር እንግዳ በለንደን ኦሎምፒክ በትራይትሎን ስፖርት የወርቅ ሜዳልያ ያገኘው አሊስተር ብራውንሊ በውድድሩ ለመሳተፍ መጓጓቱን ይናገራል፡፡ ትራያተሎን 500 ሜትር በዋና፤ 40 ኪሎሜትር በብስክሌት ግልቢያ እንዲሁም 10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫን በማካተት የሚካሄድ ስፖርት ነው፡፡ ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በአጋርነት ሲደግፉ ከቆዩት አንዱ የሆነው የእንግሊዙ ኖቫ ኢንተርናሽናል ዲያሬክተር ዴቪድ ሊንግተን ውድድሩ ባለው ማራኪ ድባብ ከዓለማችን ምርጡ ነው ካሉ በኋላ የውድድር ተቋማቸው በመላው እንግሊዝ ካካሄዳቸው ውድድሮች አሸናፊዎቹን ይዞ በመምጣት ዘንድሮ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ ኖቫ ኢንተርናሽናል አስከ 1 ሚሊዮን ተሳታፊዎች ያገኙ ውድድሮችን በማዘጋጀት በመላው ብሪታኒያ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ በሌላ በኩልየኢትዮጵያ ቱሪዝም ኦርጋናይዜሽን ዲያሬክተር አቶ ሰለሞን ታደሰ የሩጫ ውድድሩ የቱሪዝም እንቅስቃሴን የሚያቀላጥፍ ብለው ሲያደንቁ፤ የውድድሩ ስፖንሰር የሆነው የኢትዮጵዩ ንግድ ባንክ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም መኩርያ የኢትዮጵያ ትልቁ ባንክ የአፍሪካን ታላቅ ውድድር ስፖንሰር በማድረጉ ደስተኛ ነው ብለዋል፡፡

Read 2287 times