Saturday, 22 November 2014 12:43

በአለማችን 36 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በዘመናዊ ባርነት ውስጥ ይገኛሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

* የግዳጅ ጋብቻ፣ ከሚገባው በላይ ማሰራት፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህጻናትን ጦር ሜዳ ማሰለፍ---
* በህንድ 14.3 ሚሊዮን ሰዎች የዘመናዊ ባርነት ሰለባዎች ናቸው
በአሁኑ ወቅት በአለማችን የተለያዩ አገራት 36 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ዘመናዊ የባርነት ህይወት እየገፉ እንደሚገኙ ዎክ ፍሪ ፋውንዴሽን የተባለ ተቀማጭነቱን በአውስትራሊያ ያደረገ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ተቋሙ ለሁለተኛ ጊዜ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው አመታዊ የባርነት መጠን አመልካች ሪፖርት እንደሚለው፣ በአለማችን የዘመናዊ ባርነት ሰለቦች ቁጥር ከአምናው በ23 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ጥናቱ ከተደረገባቸው 167 አገራት ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘው ህንድ ስትሆን፣ በአገሪቱ 14.3 ሚሊዮን ዜጎች የባርነት ኑሮን በመግፋት ላይ ይገኛሉ፡፡
ቻይና በ3.24 ሚሊዮን፣ ፓኪስታን በ2 ሚሊዮን፣ ኡዝቤኪስታን በ1.2፣ ሩስያ በ1 ሚሊዮን፤ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ከአጠቃላይ ህዝባቸው ብዙ በባርነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ያሉባቸው አገራትን በተመለከተ ሪፖርቱ እንዳለው፣ ሞሪታንያ በ4 በመቶ፣ ኡዝቤኪስታን በ3.9 በመቶ፣ ሃይቲ በ2.3 በመቶ፣ ኳታር በ1.3 በመቶ እና ህንድ በ1.1 በመቶ ከአንድ እስከ አምስት ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ዘመናዊ ባርነት በሁሉም አገራት ውስጥ እንዳለ የተቋሙ መስራችና ሊቀመንበር አንድሪው ፎሬስት መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ዘመናዊ ባርነትን ለማጥፋት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ረገድ፣ አውስትራሊያ፣ ኦስትሪያ፣ ጆርጂያ፣ አየርላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ፣ እንግሊዝና አሜሪካ ቀዳሚነቱን እንደሚይዙ ገልጧል፡፡ እንደ ሪፖርቱ አገላለጽ፤ የሚገባቸውን ክፍያ ሳያገኙ ከሚገባቸው በላይ የስራ ጫና ያለባቸውና የተለያዩ ጥቃቶች የሚደርሱባቸው ህጻናት፣ ሴቶችና በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ ሰዎች፣ ከዘመናዊ ባርነት ሰለባዎች  ይመደባሉ፡፡ ሰዎች ነጻነታቸውን ተጠቅመው የፈለጉትን እንዳይሰሩ በመጨቆን፣ የገቢ ማስገኛ አድርጎ መጠቀም፣ የባርነት አንዱ ትርጓሜ ነው ያለው ሪፖርቱ፤ የግዳጅ ጋብቻ፣ ከሚገባው በላይ ማሰራት፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህጻናትን ወደ ጦር ሜዳ ማሰለፍና የመሳሰሉት የባርነት ተግባራት በስፋት እየተፈጸሙ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡


Read 1796 times