Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Friday, 06 January 2012 10:25

መንግስት፤ ፍቺ የሌለው “እንቆቅልሽ” እየሆነብን ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ፤ “እንቆቅልሽ የሆነች አገር” ስለመሆኗ የሚተነትኑ ምሁራንና ፀሃፊዎች ቢኖሩም፤ ለብዙ ሰዎች ግን የመንግስት እንቆቅልሽነት ገዝፎ እየታያቸው ነው። ከእንቆቅልሽም፣ “ፍች የሌለው እንቆቅልሽ”። እውነትም፤ በየእለቱ በመንግስት ባለስልጣናትና አካላት የሚፈፀሙ ተግባሮች ሲታዩ፤ “ቅጥ የለሽ” ሆነዋል። ድንገት የሚታወጁ ህጎችና መመሪያዎች ለበርካታ ወራትና አመታት ጥናት እንደተካሄደባቸው ቢገለፁም፤ ከሳምንታት በኋላ በዘፈቀደ ይሻራሉ። ብዙ ዜጎች፤ የመንግስት ፍላጎትና ሃሳብ ምን እንደሆነ ለመገንዘብም ሆነ ለመተንበይ የሚቸገሩትም በዚህ ምክንያት ነው። “የነገን ማን ያውቃል?”... መንግስት ዛሬ የወሰነውን ነገ ሲያፈርስ የሚመለከቱ ዜጎች፤ መንግስት ምን እንደሚሰራና ምን ለማድረግ እንዳቀደ ለማወቅ መሞከር ከንቱ ነው እስከማለት ደርሰዋል። በአጭሩ፤ መንግስት እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል።

ብዙውን ጊዜ ስለኢትዮጵያ እንቆቅልሽነት የሚቀርበው ትንታኔ፤ ጥንታዊ ታሪኮችን የሚያጣቅስና አድናቆትን የተላበሰ ነው። መቼም፤ “በተቃራኒ ገፅታዎች የተወጠረና ተሸፋፈነ ሚስጥር” ነው፤ “እንቆቅልሽ” የሚባለው። እና ታዲያ፤ ኢትዮጵያ ምኗ ነው እንቆቅልሽ? በርካታ የኢትዮጵያ ገፅታዎች፤ እጅግ ተመሳሳይና በግልፅ የሚታዩ ናቸው። ምእተ አመታትን ያስቆጠሩ ድህነትና ረሃብ፤ ኋላቀርነትና አቅመቢስነት፤ የነፃነት እጦትና ግጭት ... የኢትዮጵያ ገፅታዎች መሆናቸው ሚስጥር አይደለም። የዚህን ጊዜ፤ “ግንኮ ... በረዥም ታሪክ ህልውናዋን ጠብቃ የቆየት አገር ነች። የጨዋነትና የአትንኩኝ ባይነት ባህል አልራቃትም፤ ጥንታዊ የስልጣኔ ጉዞና አስደናቂ ስራዎችን ያቀፈች አገር ነች” የሚሉ ተቃራኒ ገፅታዎች ይጠቀሳሉ። በእርግጥም አገሪቱ በተቃራኒ ገፅታዎች የተወጠረች ሽፍንፍን ሚስጥር (እንቆቅልሽ) ትመስላለች። ነገር ግን፤ በረዥም ታሪክ ውስጥ፤ በየጊዜው በሚሰፍኑ የተለያዩ አስተሳሰቦችና ቀስ በቀስ ስር በሚሰዱ ባህሎች መካከል፤ ተቃራኒ ገፅታዎች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው። እናም፤ በሳይንሳዊ እይታ ለሚያጠና ሰው፤ የኢትዮጵያ እንቆቅልሽ፤ ፍቺ አያጣለትም።የመንግስት እንቆቅልሽነት ግን፤ በረዥም ታሪክ ውስጥ የሚከሰት አይደለም። እዚያው በዚያው፤ ዛሬና ነገ፤ ያለ እረፍት ተቃራኒ ነገሮችን እያፈለቀ፣ ተቃራኒ ህጎችንና መመሪያዎችን እያወጣና እየሻረ፣ ተቃራኒ ተግባራትን እየሰራና እያፈረሰ፤ በየእለቱ እንቆቅልሽ ይፈጥብናል።  መቼም መንግስት፤ ነጋ ጠባ ስለህገመንግስት መናገር እንደማይደክመው ታውቃላችሁ። እንዲያውም፤ ስለህገመንግስት በጣም እየደጋገመ ከመናገሩ የተነሳ፤ እንደ ሃይማኖት መፅሃፍ እንድናመልከው የሚፈልግ ይመስላል። ህገመንግስቱ ግን፤ እንደማንኛውም የሰው ስራ፤ እንደማንኛውም ህግ ነው። እንደማንኛውም ህግ መከበር አለበት። እንደማንኛውም ህግ እየተፈተሸና እየተመረመረ፤ ትክክልና ስህተት አንቀፅ እየተለየ መመዘን ይኖርበታል። ህገመንግስትን አክብሮ፤ ህገመንግስቱን ወይም የተለያዩ አንቀፆችን መቃወም ተፈጥሯዊ የሰው መብት ነው - መንግስት የሚሰጠን ወይም የሚነሳን መብት ሳይሆን፤ ተፈጥሯዊ መብት! አለበለዚያኮ፤ ህገመንግስቱ... ከነተፈጥሮው ህገመንግስት መሆኑ ይቀርና፤ በሰው አእምሮ የማይመረመር፤ የማይደረስበት፤ የማይሻሻል የሃይማኖት ቀኖና ይሆናል። በሌላ አነጋገር፤ ሁለት ወዶ አይሆንም። ህገመንግስትንና ቀኖናን አንድ ማድረግ አይቻልም። መንግስት የሚፈልገው የትኛውን ነው? አንዱ እንቆቅልሽ ይሄ ነው።መንግስት በአንድ በኩል፤ “ህገመንግስቱ ቀኖና ሳይሆን፤ በሁሉም ዜጋ ሊከበር የሚገባው፤ ሊመረመርና ሊሻሻል የሚችል፤ ለዚህም የማሻሻያ ስርአት ያበጀ ህገመንግስት ነው” በማለት አድናቆቱን ይገልፃል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ህገመንግስቱን ከማክበር አልፎ መውደድና መደገፍ እንደግዴታ ለመጫን ይሞከራል - እንደ ቀኖና። ህገመንግስቱን አክብሮ ማድነቅና መደገፍ ብቻ እንጂ፤ መተቸትና መቃወም ህገመንግስትን እንደመጣስ እንዲቆጠር ግፊት ሲደረግ ይታያል - ፀረ ህገመንግስት የሚል ፍረጃ። “ህገመንግስቱ፤ የመደገፍና የመቃወም ነፃነትን ያስከብራል” የሚል መንግስት፤ “ህገመንግስቱን መቃወም ህገወጥነት ነው” የሚል ከሆነ፤ ያኔ ፍቺ ያጣ እንቆቅልሽ ሆኖ ቁጭ ይላል። እስቲ ደግሞ፤ ከሃሳብ እንቆቅልሽ ወደ ተግባር እንቆቅልሽ የሚያሸጋግር ነገር እናንሳ።  የሰዎችን ስም በሃሰት የማያጠፋ እስከሆነ ድረስ፤ እያንዳንዱ ዜጋ ማንኛውንም ሃሳብ የመግለፅና የመቀበል፤ ማንኛውንም መረጃ የመሰብሰብና የማሰራጨት ነፃነት አለው የሚሉ አንቀፆችን ይዟል - ህገመንግስቱ። ነገር ግን፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት ያነበብነውን አስታውሱ። ታላቁ ሩጫ በሚካሄድበት እለት፤ “ማንበብ ሙሉ ያደርጋል” የሚል ፅሁፍ በአደባባይ ይዞ ይሮጥ የነበረ ጋዜጠኛ ለ10 ቀናት ታስሯል። በራሱ አንደበት እንደሰማነው (ማለትም ከራሱ ብእር እንዳነበብነው)፤ ሌሎች በርካታ ሰዎችም፤ ሁከትና ረብሻ ለመፍጠር ሞክራችኋል የሚል ታስረዋል። “ማንበብ ሙሉ ያደርጋል” የሚል ፅሁፍ ይዞ መዞር፤ በአንዳች ተአምር “ሁከት የመፍጠር ሙከራ” የሚሆነው እንዴት ነው? ፅሁፉን በማየት ሁከት የሚፈጥሩ ወይም ለረብሻ የሚነሳሱ ሰዎች ቢኖሩ እንኳ፤ ተጠያቂዎቹ እነሱ ራሳቸው ናቸው። በአንድ በኩል፤ መንግስትን መደገፍ ወይም መቃወም፤ የማንኛውም ዜጋ መብት እንደሆነ እየተነገረን፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ “ምናልባትኮ ለተቃውሞ የታሰበ ሊሆን ይችላል” በሚል ጥርጣሬ ሰው ይታሰራል። “የተቃወመ፤ ለመቃወም ያሰበ ወይም ያሳሰበ ...” የሚል ጨለማ የአፈና ስሜት እንድናስታውስ የሚያደርግ አሳዛኝ ክስተት ነው። እዚህም ላይ፤ ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን አጣምሮ መጓዝ አይቻልም። የመደገፍና የመቃወም ነፃነትን ማክበር አንዱ አማራጭ ነው። አልያም “የሚቃወሙ፤ ለመቃወም የሚያስቡና የሚያሳስቡ” ሰዎችን ማሰር። ሁለቱን አንድ ላይ የምናይ ከሆነስ? “ጉድኮ ነው” ብለን የምንገረምበት፤ “ፍቺ የለሽ እንቆቅልሽ” ሊሆን ነው? ይህም ብቻ አይደለም።የቀበሌ የ”ልማት ዘመቻ” ላይ አልተሳተፉም ተብለው ከ20 በላይ ሰዎች እንደታሰሩ ባለፈው ሳምንት ሲዘገብ አንብበናል። ብዙ ዜጎች የሚመጣላቸው ጥያቄ፤ “ልማት የሚባለው ነገር፤ እውነተኛ ልማት ነው ወይ?” የሚል ነው። “እውነተኛ ልማት ከሆነ፤ ሰዎች እንዲሰሩ በሃይል ማስገደድ ይቻላል” በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ የተመሰረተ ጥያቄ ነው። በሃይል ማስገደድኮ፤ መብትን ከመጣስ አይለይም። እንዲያውም፤ ነፃነትንና መብትን መጣስ ማለት ሌላ ትርጉም የለውም - “አስገዳጅ ሃይል መጠቀም” እንደማለት ነው። ዋናው ጉዳይ፤ ልማት የተባለው ነገር እውነት መሆኑና አለመሆኑ ላይ አይደለም። ሰውን በሃይል አስገዳጅነት እንዲሰራ ማድረግ፤ ነፃነትን የሚጥስ ተግባር ነው። ህገመንግስት ላይም በአንቀፅ 18 ላይም ተገልጿል - ሰዎች ከግዳጅ ስራ ነፃ የመሆን መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ ተጠቅሷል። እውነትም፤ የግዳጅ ስራ፤ ነፃነትን ያሳጣል። ለዚህም ነው፤ እንደ ቅጣት የሚቆጠረው። ነገር ግን፤ እዚያው የህገመንግስት አንቀፅ ውስጥ፤ ይህንን ነፃነት የሚፃረር አረፍተነገር ተፅፏል። በአካባቢው ህዝብ ፈቃድ የሚከናወን የልማት ተግባር ላይ እንዲሰሩ የሚገደዱ ሰዎች፤ መብታቸው እንደተጣሰ አይቆጠርም ይላል - አንቀፁ። እንግዲህ አስቡት። በአንድ በኩል፤ ሰዎች እንዲሰሩ ማስገደድ ... በአንድ በኩል ነፃነትን የሚጥስ ተግባር ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ነፃነትን የማይጥስ ተግባር ነው። እነዚህን ተቃራኒ ነገሮች አንድ ላይ ማስኬድ አይቻልም። ለማስኬድ ሲሞከር ምን ይሆናል? እንቆቅልሽ? መቼም ዛሬ መንግስት ላይ አተኮርን እንጂ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በእንቆቅልሽ የተከበቡ ናቸው። የተቃዋሚዎችን እንቆቅልሽ ከማየታችን በፊት ግን፤ ለዛሬ የመንግስትን እንቆቅልሽ ጠቀስቀስ አድርገን እንዝጋ።  “እነ አርቲስት ደበበ እሸቱ፤ አገሪቱን አሸብረው በደም ጎርፍ ሊያጥለቀልቋት አሲረዋል” ተብሎ አኬልዳማ በተሰኘው የኢቲቪ ስርጭት ስትመለከቱ፤ የተፈጠረባችሁን ስሜት አስታውሱ። “አኬልዳማ” ማለት፤ የደም መሬት ማለት መሆኑን እያሰቡ፤ “ኧረ ጉድ፤ ኧረ ጉድ” እያሉ በስሜት የገነፈሉ ሰዎች መኖራቸው አይቀርም። ህዝቡን ሊጨርሱ አሲረዋል የተባሉት “አደገኛ አሸባሪዎች”፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ በነፃ ከእስር ሲለቀቁና በየጎዳናው አብረውን ሲራመዱ ስናይስ? እንቆቅልሽ።ለህዳሴ ግድብ ግንባታ፤ በየመስሪያ ቤቱ ስበሰባዎች እየተካሄዱ፤ የገንዘብና የደሞዝ መዋጮ በጭብጨባ ሲወሰን አይታችኋል። የግድቡ ግንባታ እንዲጀመር የአብዛኛው ዜጋ ስሜት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር፤ አዳራሾቻችን በብዙሃኑ ውሳኔ ወይም በጋራ የድጋፍ ጭብጨባ መድመቃቸው አይገርምም። ነገር ግን፤ ደሞዝ የብዙሃን ወይም የጋራ አይደለም። የግል ነው። ኑሮም አዳራሽ ውስጥ ብቻ አይደለም። ከአዳራሹ ውጭ የሚቀጥለው ዋናው ኑሮ፤ ... አዎ ይሄም የግል ነው። ታዲያ፤ የገንዘብ መዋጮው በስብሰባ ተወስኗል ተብሎ፤ ከዜጎች ደሞዝ በግዴታ መቁረጥ ተገቢ ይሆናል? በጭራሽ አይሆንም። በወቅቱ ጥያቄው ሲነሳም፤ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፤ “የግዴታ መዋጮ፤ ፈፅሞ አይኖርም” ብለዋል። እንዲያውም፤ እያንዳንዱ ሰው፤ የማዋጣት ፍቃደኝነቱንና ምን ያህል ማዋጣት እንደሚፈልግ በየግሉ በፊርማ ካላረጋገጠ፤ ከደሞዙ ሳንቲም እንደማይቆረጥበት፤ ባለስልጣናት ቃል ገብተው ነበር። በበርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የምናየው ግን፤ የዚህ ተቃራኒ ሆኗል። በስብሰባ ተወስኗል ተብሎ የሰራተኞች ደሞዝ በጅምላ እየተቆረጠ ነው። ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰራተኞች ሲመጡም፤ “በስብሰባ ሲወሰን፤ አጨብጭበሃል። እጅ አውጥተህ በውሳኔው እንደማትስማማ መግለፅ ነበረብህ” የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። እንቆቅልሾቹ ብዙ ናቸው።

 

 

Read 4149 times Last modified on Friday, 06 January 2012 10:58