Saturday, 22 November 2014 12:26

ዳሽን ባንክ የአሜሪካ ኤክስፕረስ ካርድ፣ የሞባይልና ኤጀንሲ አገልግሎት ሊጀምር ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለመቄዶንያ 500ሺ ብር አበረከተ

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የክፍያ ካርድ ያስተዋወቀው ዳሽን ባንክ፤ አሁን ደግሞ የአሜሪካ ኤክስፕረስ ካርድ፣ የሞባይልና ኤጀንሲ (ውክልና) አገልግሎት በቅርብ እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡
የአሜሪካ ኤክስፕረስ ካርድ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ሀብታሞች የሚጠቀሙበት “ፕሪስቲጂየስ ካርድ” ነው ያሉት  የዳሽን  ባንክ የፕሮሞሽን ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ እስጢፋኖስ በፍቃዱ፤ ከውጭ የሚመጡ ሀብታሞች ካርዱን ስለሚጠቀሙ ለውጭ ምንዛሬ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በቪዛ ካርድ እንዳደረግነው ሁሉ፣ የአሜሪካን ኤክስፕረስ ብራንድ ያላቸውን ካርዶች አምርተን ከጥር ጀምሮ ለህዝቡ እናድላለን ያሉት ኃላፊው፣ ካርዱ በአሜሪካ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እዚህም ያስገኛል ብለዋል፡፡
አንድ ሰው በአሜሪካ በኤክስፕረስ ካርዱ ፒዛ ገዝቶ በመብላቱ ብቻ 40  ዶላር ሊመለስለት ይችላል፡፡ እዚህም የካርዱን አገልግሎት በሚሰጡ ማዕከላት ለምሳሌ እንደ ካልዲስ ወይም ሌላ ካፌ ፒዛ በልቶ፣ ወተት ወይም ማኪያቶ ጠጥቶ ካርዱን ሲሰጣቸው 40 ብር ሊመልሱለት ወይም የመቶ ብር ዕቃ ገዝቶ 80 ብር ሊመለስለት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ዳሽን ባንክ ከትንሽ እስከ ትልቅ የፕላቲንየም፣ የብርና የወርቅ ብራንድ ያላቸው አሜሪካን ኤክስፕረስ ካርዶች ያዘጋጀ ሲሆን እንደ ግለሰቡ ፍላጐት የ100ሺ፣ የ300 ሺና የ500 ሺና ብር ካርድ ሊዘጋጅለት እንደሚችል ታውቋል፡፡
ዳሽን ባንክ፣ በአገራችን ያልነበረ አዲስ የሞባይልና ኤጀንሲ (የውክልና) አገልግሎት በሚቀጥለው ታህሳስ ወር ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ ሞባይልና  ኤጀንሲ ማለት፣ ዳሽን ባንክ ቅርንጫፍ በሌለው አካባቢ አገልግሎት የሚሰጥ በማህበረሰቡ የተወደደና የተመረጠ ወኪል ማለት እንደሆነ አቶ እስጢፋኖስ ገልፀዋል፡፡
ዳሽን ባንክ ቅርንጫፍ በሌለው ትንሽ ከተማ ማህበረሰቡ የሚወደውና የሚያምነው ነዳጅ ማደያ፣ ሱፐርማርኬት፣ ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር ውክልና ይፈራረማል፡፡ ውሉ የተሰጠው ድርጅት የተወሰነ ገንዘብ (200ሺ፣ 300 ሺ፣… ብር) እንዲያሲዝ ይደረጋል፡፡ ከዚያም፣ አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ ጂማ፣ ሐዋሳ፣ ድሬደዋ፣ …. ያለ የዳሽን ባንክ ደንበኛ፣ ሞባይልና ኤጀንሲ ወዳለበት ቀበሌ ገበሬ ማኅበር፣ መንደር ወይም ትንሽ ከተማ፣ … ለሚኖር ዘመድ ወይም የንግድ ባልደረባ፣ … እንዲሰጠው ገንዘብ ዳሽን ባንክ ያስገባል፡፡
ባንኩም፣ ለላኪው፣ ተቀባይ ገንዘቡን የሚቀበልበትን ሚስጢራዊ ቁጥር ወይም ኮድ ይሰጠዋል፡፡ ከዚያም ለሞባይልና ኤጀንሲው (ወኪሉ) ደውሎ፣ እንዲህ ዓይነት ኮድ ለሚያቀርብልህ ሰው ወይም ድርጅት፣ ይህን ያህል ብር ክፈለው የሚል መልእክት ያስተላልፍና ወኪሉ ካስቀመጠው ገንዘብ ላይ የከፈለው ገንዘብ እንዲቀነስ ይደረጋል፡፡ በመጨረሻም፣ ወኪሉ ለሰጠው አገልሎግት ባንኩ ኮሚሽን ይከፍለዋል በማለት አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የዳሽን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን “ብቸኛ የዓመቱ ምርጥ በጐ አድራጐት ድርጅት” በማለት የ500ሺ ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ አስታወቁ፡፡
መቄዶንያ በአሁኑ ወቅት 715 አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማንን በተለይም የአልጋ ቁራኛ የሆኑ፣ ለመመገብም ሆነ ለመፀዳዳት የሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ከወደቁበት ጐዳና በማንሳት፣ የምግብ፣ የልብስ፣ የሕክምና፣ የተሟላ ቤተሰባዊ ፍቅርና እንክብካቤ እያደረገ መሆኑን አቶ ቢንያም ጠቅሰው፤ ዳሽን ባንክ ለሦስት ዓመታት በተከታታይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ባንኩ ባደረገላቸው ድጋፍም የብዙ ወገኖችን ሕይወት ማትረፋቸውን ገልፀው፤ ሌሎች ባንኮችና ድርጅቶች አርአያውን ተከትለው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በድርጅታችን የአንድ ሰው የቀን ወጪ 20 ብር ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የ715 ወገኖች የቀን ወጪ 14,300 ብር፣ የወር ወጪ 429ሺህ ብር፣ የዓመት ደግሞ 5 ሚ. 219 ሺ 500 ብር ይሆናል ብለዋል፡፡ ዳሽን ባንክ ዘንድሮ ለማዕከሉ ባደረገው ድጋፍ፤ ተጨማሪ 70 ሰዎችን ከጐዳና ማንሳታቸውን ጠቅሰው፤ በተረጂ ወገኖች ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቅርቡም “ዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ” ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል 500ሺ ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

Read 2894 times