Saturday, 22 November 2014 12:22

እነ መብራት፣ ውሃ፣ ኢንተርኔት…የሉም…

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(28 votes)

ኢህአዴግስ?)    በኳስ ድል ስናጣ ወደ ፕሮፓጋንዳ ገባን!

          የፖለቲካ ወጋችንን ሰሞኑን በEBC (በጥንቱ ኢቲቪ ማለቴ ነው!) የስፖርት ፕሮግራም ላይ በሰማሁት አስገራሚ ዜና ለምን አንጀምረውም፡፡ ዘገባው የጀመረው የማሊ እግር ኳስ ቡድን (አሰልጣኝ መሰሉኝ?) “በአዲስ አበባ ላይ ባዩት ለውጥ ተገረሙ” በሚል ነው፡፡ ተገርመው ብቻ ግን ዝም አላሉም፡፡ “የአፍሪካ አገራት ከአዲስ አበባ ብዙ መማር አለባቸው” እንዳሉም  የስፖርት ጋዜጠኛው ዘግቧል (ስንቱ ይሆን ከኛ የሚማረው?!)
ይኸውላችሁ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ስኬት ስኬቱ ላይ (success stories) አተኩር እንደሚል ዘንግቼው አይደለም፡፡ ግን የስፖርት (ያውም የእግር ኳስ) ዜና ላይ “አዲስ አበባን አደነቁ!” ዓይነት ዘገባ ስላልጠበቅሁ ነው! በኋላ ግን ችግሩ ገባኝ፡፡ ኳሱ የሚደነቅ ካልሆነ የትኩረት አቅጣጫን መቀየር የግድ ነው፡፡ አያችሁ … በኳስ ጨዋታው ውጤት አልተገኘም፡፡  እናም የስፖርት ጋዜጠኛው ምን ይዘግብ? ቢያንስ የማሊ እንግዶችን እየዞረ “አዲስ አበባን እንዴት አገኛችኋት?” በማለት “ልማታዊ ዜና” ወይም “ለአገር ገፅ ግንባታ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ዘገባ” ማቅረብ አለበት፡፡ (በኳሱ ድል ቢቀናን እኮ ፕሮፓጋንዳው ይቀር ነበር፡፡)
በነገራችሁ ላይ አዲስ አበባ ስትደነቅ ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ በፈጣን ዕድገቷ (ባለደብል ዲጂቱን ማለቴ ነው!) ስትወደስና በአርአያነት ስትጠቀስ መስማት የማይወድ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን እጠራጠራለሁ፡፡ የEBC ዘገባ ግን ችግሩ ምን መሰላችሁ መረጃና ፕሮፓጋንዳ ይደበላልቃል፡፡ በዚያ ላይ ማሊዎቹ እውነት አድናቆት ብቻ ነው የሰነዘሩት የሚለውም ያጠያይቃል፡፡ እንዴ…መብራት፣ ውሃ፣ ኔትዎርክ በሌለበት “አዲስ አበባ መንግስተ ሰማያት ናት” ቢሉስ ማን ያምናቸዋል፡፡
አሁን እኮ ሁሉም መሰረተ ልማቶች ጠፍተው ኢህአዴግ ብቻውን የቀረ ነው የሚመስለው፡፡ (ፕሮፓጋንዳው ግን ቀጥሏል!) በነገራችሁ ላይ አንዳንዴ ኢህአዴግ ይሁነኝ ብሎ ፕሮፓጋንዳን መተው አለበት፡፡ (ከእነ አካቴው አልወጣኝም!) በቃ በወር… በሁለት ወር አንዴ ከፕሮፓጋንዳ የፀዳ ንፁህ መረጃ ለኛ የስልጣን ህልውናውን በድምፃችን የመወሰን ስልጣን ላለን ህዝቦች ሊሰጠን ይገባል፡፡ በእርግጥ ከፕሮፓጋንዳ ለሰከንድም ቢሆን መላቀቅ ይከብዳል (ከስልጣን የባሰ ሱስ እኮ ነው!!) ሆኖም ማገገሚያም ቢሆን (Rehabilitation Center!) ገብቶ ፕሮፓጋንዳን ከደሙ ውስጥ ጠራርጎ ማስወጣት ይኖርበታል፡፡
ዕውቁ ደራሲ አዳም ረታ በቅርቡ ባወጣውና ተወዳጅነትን ባተረፈበት “መረቅ” የተሰኘ ረዥም ልብወለዱ፤ ፕሮፓጋንዳን “ጥዝጠዛ” ይለዋል፡፡ (ኢህአዴግ ስንት ዓመት ጠዘጠዘን?)
በነገራችሁ ላይ ስለ ፕሮፓጋንዳ ለማውጋት የተነሳሁት በአዳም ረታ ልቦለድ ተነሽጬ በመሆኑ በእናንተ ስም አመሰግነዋለሁ፡፡ እንዴት ነሸጠህ… አትሉኝም? ደራሲው በልብወለዱ ውስጥ ስለ ፕሮፓጋንዳ የፃፈውን አብረን እንቃኝ፡፡
“…ከአብዮት በፊት በአዲስአባ አራዶች ተወዳጅ የሆኑት ሬስቶራንቶች የፈረንጅ ምግብ የሚሸጥባቸው ነበሩ፡፡ የአብዮት ማዕበል አገሪቷን ሲንጥ ከሁሉም አቅጣጫ በሚመጡ ፖለቲከኞች ተንቀውና ፀረ - ኢምፔሪያሊስት በተባለው አቁዋም ተደናግጠው፣ ፍርሃት አስበርግጐአቸው ጠፉ፡፡ በ71 ዓ.ም አካባቢ ቀውሱ መብረድ ሲጀምር፣ ይሄን የውጭ አገር የምግብ ስፍራ በባሕል ምግብ መሙላት የቀረው አማራጭ ነበር፡፡ ይሄን የለውጥ ጐዳና ብዙዎች ተከትለዋል፤ ግን እንደ እኔ ሰፋና ገፋ አላደረጉትም፡፡ (ይሄን የሚለው የአባቱን ሆቴል ወርሶ በማሻሻል የተሳካለት “እዝራ” የተባለ ገፀባህርይ ነው) የተከፈተውን ቦታ በተመሳሳይ ይዘት ሞሉት እንጂ የተለየ ጣዕም ይሁን ቄንጥ አልወለዱም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት የዝልዝል ጥብሴ ነገር በራዕይ ፈሰሰልኝና ወደ እዛ በድፍረት አመራሁ፡፡ ግን ይሄ ፈጠራዬ ተወዳጅ እንዲሆን መደረግ የሚገባቸው ውስብስብ ነገሮች ነበሩ፡፡ ከነዚህ መሰራት ከሚገባቸው ነገሮች አንደኛውና መሰረታዊው ፕሮፓጋንዳ ነበረ፡፡ ዝልዝል ጥብስና ፕሮፓጋንዳ ወይም ቀለል ላድርገውና ጥብስና ማስታወቂያን ለመሆኑ ምን አገናኛቸው?” (ወደ አዳም ዝልዝል ጥብስና ፕሮፓጋንዳ ከአፍታ “ቆይታ” በኋላ እንመለስበታለን፡፡)
እኔ የምለው ግን … የመንግስት መ/ቤት ህዝብ ግንኙነቶች (ይቅርታ “ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር” ለማለት ነው!) ዋና ሥራቸው ምንድነው? መቼም ፕሮፖጋንዳ ወይም ካድሬነት ሊሆን አይችልም፡፡ ኢህአዴግ ከባባድ ስሞች አሽሯቸው ሥራቸውን ነጠቃቸው እንዴ? (ጥያቄ እኮ ነው!) በመ/ቤታቸው ተማራችሁ ትችት ነገር …  ነቀፋ ቢጤ … ለመሰንዘር ከሞከራችሁ ከኢትዮጵያ ፀረ - ሰላም ሃይሎች ጋር ሊመድቧችሁ ምንም አይቀራቸው፡፡ ብዙ ጊዜ “ልማታችንን ለማደናቀፍ…” ምናምም ማለት ይወዳሉ፡፡ (የተተቹትን ከማስተካከል ይኸኛው ይቀላላ!) ኢህአዴግ አውቆም ይሁን ሳያውቅ፣ በየዋህነትም ይሁን በብልጣብልጥነት ካድሬ ወይም አባል አድርጓቸው ከሆነ (አያደርገውም ባይ ነኝ!) ጉዳቱ ተመልሶ ለራሱ ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ? ሁለት ካባ ለብሰው ያምታታሉዋ! የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር እንዳሉት፤ “ህጋዊነትንና ህገወጥነትን እያጣቀሱ ይጓዛሉ”
አሁንም ወደ “መረቅ” ልመልሳችሁ፡፡   
“ …የሰው ልጆች ፍላጐት በየጊዜው ይለዋወጣል፤ ይኼ እውነት ልዩ ምስክር መጥራት  የሚያሻው አይደለም፡፡ የፍላጐት መለዋወጥ ብቻ ሳይሆን ያ ፍላጐቱ የሚተከልባቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ይለዋወጣሉ፡፡ እነዚህን ሳይነጣጥሉ በድምር የመረዳት ኪነቱ ነው “መረዳት” የሚሆነው፡፡ ምግብ እንደ ማንኛውም ሰባዊ ድርጊት ባሕል ነው፡፡ በአዲስነቱ እንደ ማንኛውም ዕውቀትና ባሕል መጀመሪያ መፈልሰፍ፣ ቀጥሎ በብዙዎች መኖሩ መታወቅ፣ ቀጥሎ ልማድ መሆን መቻል አለበት፡፡ ይኼ ደሞ እንደ ሁኔታው በአጭር ጊዜ ወይ በረዥም ጊዜ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ሰብአዊ ባሕርይ ስለሆነ የዕድገት መንገዱን ከሌሎች ሰብአዊ ድርጊቶች በመቅዳት መምራትና መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ቀደም ብዬ ያነሳሁት የፖለቲካዊ ነገር የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡
“…ወጣቶች ፖለቲካ ውስጥ ተንጋግተው የገቡበት ሁኔታ ባብዛኛው በእኔና በሳል በሆኑ ሰዎች ግምት (ወይም በገባቸው ሰዎች ግምት) በአገራችን የሰፈነው ጭቆና አስከፊ ሆኖ መላወሻና መንቀሳቀሻ ጠፍቶአቸው ሳይሆን በረቀቀ ፕሮፓጋንዳ ግፊት መሆኑ ነው፡፡ ፕሮፓጋንዳ አዲስ ፍጡር አይደለም፤ ድሮም ነበረ፡፡ ዛሬ የፈረሰውን የሰለሞናውያን ስርወ መንግስት እዚህ ያደረሰው የአንድ ሰው ፕሮፓጋንዳ እንደ ሆነ ያውቃሉ? ታምሪን የተባለ ነጋዴ ለሳባ ስለ ሰለሞን ጥበብ ነጋ ጠባ ይነግራታል፣ በዚህ ምክንያት ሰለሞንን በአይኗ ሳታየው ወደደችው፡፡ ክብረ ነገስት “ከፍቅሯም ብዛት የተነሳ ታለቅስ ነበር፣ ለመንግስቱም (ለሰለሞን መንግስት) ልትገዛ ፈጽማ ትሻ ነበር” ይላል፡፡ ደካማ ትሁን አትሁን ወይም የዞረባት ቁሌታም፣ እንርሳውና፣ መጀመሪያውኑ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ አርግዛ እንድትመጣ ቀስቃሽ ምክንያት የሆናት የነጋዴው የታምሪን ጥዝጠዛ ነው፡፡ ጥዝጠዛ ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሄን ክብረነገስት ውስጥ ሳነብ እስቅና እገረም ነበር…”
ደራሲው የፕሮፓጋንዳን ታሪካዊ አመጣጥ ለማስረዳት ሁሉ ሞክሯል (የ“ቤቶች” ድራማዋ አዛሉ ትዝ አለችኝ!)
ስለ ፕሮፓጋንዳ መረጃ ስበረብር እጄ ከገቡት አባባሎች ውስጥ አንዱ እንዲህ ይላል፡- “ፕሮፓጋንዳ ሰዎችን አያታልልም፤ ራሳቸውን እንዲያታልሉ ብቻ ነው የሚያግዛቸው” እውነት እኮ ነው፡፡ በጃንሆይ ዘመን ህዝቡ ድንገት ተነስቶ “ፀሐዩ ንጉሳችን!” ማለት አልጀመረም፡፡ የፕሮፓጋንዳ ውጤት ነው፡፡ አሁን በኢህአዴግ ዘመንም ቢሆን ተመሳሳይ ነው፡፡ “ልማታዊ መንግስታችን” የሚለውን እንደ አዝማች በየንግግራቸው የሚዶሉ የበዙት በቅርቡ ነው፡፡ (ከብዙ ዓመት የፕሮፓጋንዳ ልፋት በኋላ የተገኘ ድል በሉት፡፡)
“… ፖለቲካ ከወዳጆቼ ቢለያየኝም ከርቀት ሆኜ ግን እጠይቃለሁ፡፡ “ለምን?” እላለሁ፡፡ “እንዴት ሊሆን ቻለ?” እላለሁ፡፡ እንግሊዘኛ የማይችል በግዕዝ የሚጠነቁል ደብተራ የመጠየቅ መብት የለውም ማን አለ? ለምሳሌ በቀለም ትምህርቷ ጐበዝ የነበረችው፣ “ሳይንቲስት ትሆናለች” ብሎ ተማሪና አስተማሪ ተስፋ የጣለባት ተባረኪ፣ (ከፍቅር ድርጅቴ ይበልጥብኛል ብላ ኢህአፓን የሙጥኝ ያለች ገፀ ባህርይ ናት!) ፖለቲከኛ መሆን ነበረባት? ቢያንስ ቢያንስ የዳሌዋን ስፋት ያየ፣ የቁመቷን መለሎነት ያየ፣ የጡቶቿን ዲብ ያየ፣ የእግሮቿን ጠብደልነት ያየ፣ ጠንካራ ልጆች የምትወልድ ሚስት ትሆን ነበር ብሎ መገመት ይችላል፡፡ ታዲያ ከጐበዝ ተማሪነቷና ሚስት ሆና ልትወልድለት ከሚገባት አላዛር እርቃ ፖለቲካ ውስጥ መሰንቀር ይገባት ነበር? እኔ እንደምገምተው አይመስለኝም፡፡ ግን ጥሩ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ትሆናለች…”
ጆስ ዌዶን የተባለ ፀሐፊ ስለዜና የተናገረው EBCን አስታወሰኝ፡፡ “የዜና ዓላማ በእርግጥ የተከሰተውን መንገር አይደለም፡፡ ልትሰሙ የምትሹትን ወይም ልትሰሙት ትፈልጋላችሁ ተብሎ የሚታሰበው ነው የሚቀርብላችሁ” ይላል፡፡ በእርግጥ የሰለጠነው ዓለም የተስማማበት የዜና ብያኔ ይሄ አይደለም፡፡ ትክክለኛና እውነተኛ መረጃ ለህብረተሰቡ ማቅረብ ነው፡፡ በሶሻሊዝምና በልማታዊ ጋዜጠኝነት ግን ዜና ሳይቀር የፕሮፓጋንዳ ሰለባ ይሆናል፡፡ ዜና በሁለት ይከፈላል ልንል እንችላለን፡፡ የኒዮሊበራሎችና የኮሚኒስቶች!! በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ባለበት ሁሉ ፕሮፓጋንዳ አለ፡፡ በኢቴቪ ብቻ አይደለም፡፡ በፓርላማ ሪፖርት ወይም በመንግስት መ/ቤት ስብሰባ አሊያም ግምገማ ወይም ደግሞ በባለስልጣናት መግለጫ ሳይቀር ፕሮፓጋንዳው በሽበሽ ነው፡፡ (መዝናና ቦታም አይጠፋም!)
“በመጀመሪያ ቃል ነበር” የሚለው ዓረፍተ ነገር በሃይማኖት የስብከት ወይም በዘመኑ አለማዊ አባባል የፕሮፓንዳ መጀመሪያ ነው፡፡ (ከዲቃላው ሚኒሊክ መወለድና ሰለሞናዊ ስርወ መንግስት ከመፈጠሩ በፊት የታምሪን ቃል ነበር እንድንል) የኪነት መዝሙር የሚባለው ሁሉ በድብቅ ሆነ በግልፅ የሚዘምረው ዓለማዊ ቅዳሴ ነው፡፡ እኔ ደጀሰላም ሄጄ የአምላክን ቃል በዜማ ሳጅብ የእሱ የፈጣሪዬ ካድሬ መሆኔ ነው እኮ፡፡ ታዲያ ከነበረው ብዙ እርቀናል?
“ደግሜ ልበለውና ምድር ላይ ያሉ የሐይማኖት ተቁዋሞች ሁሉ ሰመረ አልሰመረ የእግዜር ማስታወቂያና የስለላ ድርጅቶች ናቸው፡፡ የሰዎች መናዘዝና ንስሐ መግባት በቅርብ አገሪቷ ውስጥ ሲደረግ የነበረውን ማጋለጥና ንቃት አይመስልም? ነገሩን ነው የምለው፡፡ ከላይ እስከ ታች ያለው የፖለቲካ ድርጅቶች አሰራር መለኮትና ነገረ መለኮት የተዋቀሩበትን ስልት የያዘ አይመስልም? ይኼን ማመሳሰል ሳደርግ ግን ቅንጣት ያህል ሐጢያተኛነት አይሰማኝም፡፡”
በነገራችሁ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት መሪዎች ቋንቋ ተለውጦብኛል፡፡ (የእግዜር ካድሬ ሳይሆን የመንግስት ካድሬ እየመሰሉ ነው!) ጆሴፍ ጐመልስ የተባለ ፀሐፊ ደግሞ ፕሮፓጋንዳን እንዲህ ይገልፀዋል፤ “በበቂ ድግግሞሽና የህዝብ ስነልቦናዊ ግንዛቤ፤ ስኩዌር (ካሬ) ክብ መሆኑን ማረጋገጥ የማይቻል አይደለም፡፡ ዝም ብለው እኮ ቃላት ናቸው፡፡ ቃላት ደግሞ ሃሳብ እስኪለብሱና እስኪለበጡ ድረስ እንደተፈለገው ሊቀረፁ ይችላሉ፡፡” ኸርበርት ኤም. ሼልተን የተባለ ፀሐፊ እንዲሁ ተንጋደው “የተማሩ ሰዎችን ከማቃናት ጨርሶ የፊደል ደጅ ያልደረሱትን ማስተማር ይቀላል” ብሏል፡፡
ይሄውላችሁ… ኢህአዴጐች በሉ ተቃዋሚዎች… በአጠቃላይ የጦቢያ ፖለቲከኞች ከራሳቸው ውጭ ሌላውን ለመስማት ፈቃደ - ልቦና ያጡት …እልም ያሉ ትዕቢተኞች ወይም ክፉዎች ስለሆኑ አይደለም፡፡ (አንዳንዶች ግን አይጠፉም!!) ድሮ የተማሩትን፣ የሚያውቁትን፣ የኖሩትን… አስወጥተው በአዲስ መተካት ሞት ስለሚሆንባቸው ነው፡፡
አንድ (በፈቃዱ) የኢህአዴግ ተሟጋች የሆነ ወዳጅ አለኝ (ወዳጅነታችንን በከፊል በካድሬነት ለውጦታል) እናላችሁ… አልፎ አልፎ ስንገናኝ እኔ በመብራትና በኔትዎርክ መቆራረጥና መጥፋት ተማርሬ፣ ብሽቀቴን ሳጋራው፤ እሱ ሆዬ… ኢህአዴግ በቲቪ የሚያሰለቸኝን ባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት እንደ አዲስ እየጠቀሰ ይጠዘጥዘኛል፡፡ (የሚሰለቸኝ እኮ ዕድገቱ  አይደለም - ጥዝጠዛው ነው!) አብረን በአገሪቱ መዲና እየኖርን እንዴት ስለ መንገዱና ስለ ባቡር ሃዲዱ ዝርጋታ፣ ስለ ህንፃዎቹ እንደ አሸን መፍላት፣ ስለ ፋብሪካዎቹ መበራከት ወዘተ ሊሰብከኝ ይፈልጋል (ቱሪስት እኮ አልመስልም!) እናላችሁ ወዳጆቼ… በግሉ ተደራጅቶ የፕሮፓጋንዳ ክንፍ ያዋቀረ በጎ ፈቃደኛ ካድሬም አለላችሁ፡፡ (አይጣልባችሁ እኮ ነው!)  

Read 4318 times