Saturday, 22 November 2014 12:07

“የዛሬ ሳምንት ራሴን ያመኛል”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አጐንብሶ መሄድ አላውቅ ብዬ እንደ ሰው
እቀና ብዬ ነው ቤቴ የፈረሰው፤
የሚሏት “ተረትና ምሳሌ” ነገር አለች፡፡ አሁን አሁን እንደምንም ብለው ቀና ያሉ ሰዎች ቤታቸው መፍረሱን ወይም እየፈረሰ መሆኑን እንሰማለን፡፡ ምን አይነት ጊዜ እንደሆነ አንድዬ ይወቀው እንጂ…የአንዱ ስኬት የሌላውን ዓይን የሚያቀላበት ዘመን ውስጥ ነን፡፡ መቼም “ቶክ ኦፍ ዘ ታውን” በሽ ነው፡፡ ታዲያላችሁ…መቼም መአቱ ያው “ፊክሽን” ምናምን ነገር ነው፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ “ፊክሽኑ” ሁሉ አሪፍ በሆነ መንገድ ስለሚቀርብ እውነቱንና “ቁጩውን” መለየት አቅቶናል፡፡ (“ቁጩ” የሚለው ቃል አሁንም “ሰርኩሌሽን” ውስጥ ነው እንዴ!) ደህናውን ጊዜ ያምጣልንማ!
ስሙኝማ…ይቺን ነገር ከዚህ በፊት ሳናወራት አልቀረንም፡፡ እሱዬው እሷዬዋን…”ዛሬ ተገናኝተን እንጫወት…” ይላታል፡፡ እሷዬዋም…”ዛሬ አልችልም…” ትለዋለች፡፡ “እሺ እንግዲያው ነገስ?” ይላታል፡፡ እሷም “ነገም አልችልም” ትላለች፡፡ “እሺ የዛሬ ሳምንትስ?” ሲላት ምን ብትለው ጥሩ ነው… “የዛሬ ሳምንት ራሴን ያመኛል፡፡” አሪፍ አይደል!
እናማ…በተዘዋዋሪ መንገድ…አለ አይደል…”የዛሬ ሳምንት ራሴን ያመኛል…” ስንል የሚሰማን እያጣን ተቸግረናል፡፡
“ስማ፣ ስፈልግህ ነው ያገኘሁህ፡፡”
“ለምን ፈለከኝ?”
“አንድ ጉዳይ አለ፣ ሻይ እየጠጣን እናወራለን፡፡”
“ለምን አሁን አናወራም!”
“ሌላ ጊዜ ተደዋውለን እንገናኝና የምነግርህ ነገር አለ፡፡”
“ጠርጥር፣ ገንፎ ውስጥ አለ ስንጥር” ማለት ይሄኔ ነው፡፡ “ሰሞኑን እንኳን አይመቸኝም፡፡ ጊዜ ሲኖረኝ እኔ ራሴ እደውልልሀለሁ…” ትላላችሁ፡፡ በቃ እንዲህ ማለት እኮ…”የዛሬ ሳምንት ራሴን ያመኛል…” ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች አንድን ነገር ወዲያውኑ የሚነግሯችሁ ካልሆነ…በቃ የሆነ ነገር አለው ማለት ነው፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ በድንገትም ቢሆን ስትገናኙ… “ስማ አንድ የሆነ ቢዝነስ ስላለ እንድንገባበት ፈልጌ ነው፡፡ ብታዋጣ አንድ ሰማንያ መቶ ሺህ ብር ብቻ ነው፡፡” (“ሰማንያና መቶ ሺህ ብር” እንዲህ “ዋዛ፣ ፈዛዛ” ሆና ቀረች!) ከዚህ በኋላ የእሱ ስልክ ሲሆን ወይ “ኔትወርክ አይሠራም…” ወይ “አፓራተሱ ብልሽት አለበት…”፡፡ ልክ ነዋ…ሄዶ የየመን ቱሪስት ያታል! መቼም “ቱሪስት” አያጡም ብዬ ነው፡፡
እናማ…በተዘዋዋሪ መንገድ…አለ አይደል…”የዛሬ ሳምንት ራሴን ያመኛል…” ስንል ልብ ይባልልንማ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ምን ግርም ይልሀል አትሉኝም… “የምንመለመልበት” ሰበቦች ብዛት! ትንፋሽ ስጡና!
ግራ ክንፍ ይሁን፣ ቀኝ ክንፍ ይሁን፣ እንደውም “ክንፍ” እንኳን ይኑረው የማታውቁት “ቦተሊከኛ” ይመጣና… “እውነት፣ እውነት እልሀለሁ ስርየት የምታገኘው የእኛ ቡድን አባል ስትሆን ነው…” አይነት ነገር ይላችኋል፡፡
የኃይማኖቱ ሰው፣ ወይም “የኃይማኖት ሰው ነኝ” የሚለው ደግሞ ይመጣና (ዘንድሮ ማን ከእንትኑ ስር “ጭራ እንዳለው” መለየት አቅቶን ተቸግረናል፣ ቂ…ቂ…ቂ…) ይመጣና… “በእኛ በኩል ካላለፍክ እንኳን መንግሥተ ሰማያት ልትገባ፣ በርቀትም አታየው…” አይነት ነገር ይላችኋል፡፡ (መንገድ ላይ ማለፊያ የምታሳጡን ሰዎች ተውንማ!)
እነሱ የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፍ እስከ መሸጥና እስከ መለወጥ ድረስ የሚያስችል “ውል” አላቸው እንዴ! (አሀ… “ወዮልሽ! ሁልሽም ገሀነም ትወረውሪያታለሽ!” ምናምን ብሎ ነገር ምንድነው!)
“የዓለም ዘጠኝ” ሰው ነኝ” የሚለው ይመጣና… “ማታ፣ ማታ ከተማው እንዴት ነፍስ እንደሚያድስ አልነግርህም፣ ለምን ጆይን አታደርገንም! ጌታው ጊዜ ›ለህ ቸስ በልበት…” ይላችኋል፡፡
ደግሞላችሁ…“ጆብ ዲስክሪፕሺኑ” በደንብ ያልለየው ይመጣና… “ስማ እንዴት አይነት ቺኮች እንደማገናኝህ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡ እመነኝ፣ ዕድሜህ በእጥፍ ነው የሚጨምረው…ይላችኋል፡፡ እናላችሁ …“መልማዮች”ና የመመልመያ ምክንያቶች በዙብንማ፡፡
ታዲያላችሁ…እነኚህ ምክንያቱን በግልጽ የማይነግሯችሁ ግን በ “ቅቤ ምላስ” የዓለም ባንክን ካዝና ፊታችሁ የሚዘረግፉላችሁ “መልማዮች” አሉላችሁ፡፡ “ስማ፣ አንድ የሆነ ሥራ አለ፣ በቃ የዕድሜ ልክህን ፈራንክ የምትዘጋበት ነው፡፡ እኔ ከሰዎቹ ጋር አገናኝሀለሁ…” ምናምን ይላችኋል፡፡
ይሄ ሁሉ ጊዜ ታዲያ …በተዘዋዋሪ መንገድም ቢሆን…አለ አይደል… “የዛሬ ሳምንት ራሴን ያመኛል…” ስንል የሚሰማን አጥተናል፡፡
እኔ የምለው…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…ደረታችሁ ላይ “ጠጉር” ያላችሁ ሰዎች “ለትራስነት” ታከራያላችሁ እንዴ! አሀ…ግራ ገባና! በቀደም አንድ ሚኒባስ ውስጥ ሁለቱ እንትናዬዎች በእነሱ ቤት መንሾካሾካቸው ነው…ሲያወሩ አንደኛዋ ምን ትላለች… “የሚገርመኝ ደረቱ ሁሉ ፀጉር ነው…” ትላለች፡፡ ሌላኛዋ ደግሞ “እሱ ላይ ለጥ አልሻ!” አለቻትና አረፈችው፡፡ በደረት “ጠጉር”ም “ዲስክሪሚኔሽን” ምናምን ሊመጣብን ነው እንዴ! …ሌጣ ደረቶች ሆይ፣ “ያመለጣችሁን” እዩማ፡፡ እኔ የምለው…ቅንድቡ፣ ጢሙ ምኑ፣ ምናምኑ “አርቲፊሻል” ምናምን ሲሠራለት…ምነዋ አርቲፊሻል የደረት ፀጉር አልተሠራ! የደረት “ጠጉር” የምንመኘው ሁሉ ደረታችንን የአማዞን ጫካ አስመስለን “ኤክስሬይ ለማንሳት ስለሚያስቸግር ባርቤሪ ሄደህ ተከርክመህ ና…” ልንባል እንችላለን፡፡
ስሙኝማ…ችግሩ ምን መሰላችሁ…ለደረት የተመኘነው ፀጉር የት ቢበቅል ጥሩ ነው…አዕምሯችን ውስጥ! ቂ…ቂ…ቂ የሚኮሰኩሱ ነገሮች መናገር የምናበዛ ሰዎች ምክንያቱ የቃላት መረጣ ሳይሆን “የአእምሮ ጠጉር” ሊሆን ይችላል!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እነኚህ የዓለም “የሰማይ ስባሪ” የሚሏቸው መሪዎች እንደ “ህጣን” ያደርጋቸዋል እንዴ! አሀ…በቀደም አውስትራሊያ ውስጥ ፑቲን ላይ ያሳዩት የነበረው ነገር ሁሉ…አለ አይደል…የእንትን ሰፈር ልጆች ሊያናድዱት የፈለጉትን ሰው… “ጭራ እናስበቅለው፣” የሚሉት አይነት “አድማ” ይመስላል፡፡ ነገሩ ደስ አይልም፡፡
እናላችሁ…ሁሉም አይነት “መልማዮች” ሆይ… “የዛሬ ሳምንት ራሴን ያመኛል…” ስንል አድምጡንማ! ልጄ… “ሲመች የአማት ተዝካርም ይወጣል፣ ሳይመች የአባትም ይቀራል፣” ስንልስ! (ወይም ከዘመኑ ጋር ለመዘመን ..አርሴም፣ ማንቼም አንሆንም ስንልስ! “እናንተ የማታውቁት፣ እኔ የማውቀው የመንግሥተ ሰማያት መንገድ አለ…” ስንልስ!ደግሞላችሁ…ከጥቂት ጊዜያት በፊት አንድ ወዳጄ ያለኝን ስሙኝማ! አንድ በቅርብ የሚያውቀው ሰው ምን ይለዋል… “ስማ ከሆኑ ፈረንጆች ጋር የሚሠራ ሥራ አለ፡፡ እኔ አንድ የምተማመነው ጓደኛዬ አለ ብያቸዋለሁ…”፡፡ ሥራው ምን እንደሆነ ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየውም “እሱን ወደፊት እነግርሀለሁ፣ ግን ከፍተኛ ምስጢር ነው፣” ይለዋል፡፡ ይሄ ወዳጄ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የጓደኛውን ስልክ ማንሳት ትቷል፡፡ “የዛሬ ሳምንት ራሴን ያመኛል…” እያለው ነው፡፡ እኔ የምለው…የ “ፈረንጅ” ነገር ከተነሳ…ሀሳብ አለን፡፡ ለምንድነው የአውሮፓ ህብረት አባል ያልሆነው? ልክ ነዋ! ምድረ የአውሮፓ ከተማ ሁሉ እዚህቹ ሸገራችን ውስጥ የሬስቶራንትና የቡቲክ ሁሉ መጠሪያ ሆኖ የለም እንዴ! እኔ እንደውም፣ አይደለም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች፣ የአውሮፓ ሀገሮች እንኳን የእኛን ያህል የጐረቤቶቻቸውን ከተሞች ስም የሚጠቀሙ አይመስለኝም፡፡
 አባል ባያደርጉን እንኳን የታዛቢነት ወንበር ይሰጠን፡፡ “የዛሬ ሳምንት ራሴን ያመኛል…” እንደማንላቸው ፈርሙ ካሉንም ግጥም አድርገን እንፈርማለን፡፡
ደህና ሰንብቱልንማ!  


Read 4092 times