Saturday, 22 November 2014 11:56

ከጐንደር እስከ ጉዋሣ የጉዞ ማስታወሻዬ

Written by  ነቢይ መኮንን-
Rate this item
(1 Vote)

“ቡና የለም እንጂ ቡናማ ቢኖር

ወይ አገር ወይ አገር፣ ወይ አገር ጎንደር”
      *        *      *
አገሯ ጉዋሳ መገራ
ምነው አልሰማ አለች ብጣራ ብጣራ
      *        *      *
እውነት ለመናገር አንዳንድ አገራችንን ክፍሎች የምናውቃቸው በግጥም ብቻ ነው፡፡ ሄደን ስናይ ከግጥሙና ከአገሩ የቱ እንደሚሰፋ እንለያለን፡፡ መጀመሪያ ጎንደር፡፡ ጐንደር ደርሼ የተመለስኩት በአውሮፕላን ነው፡፡ ያረፍኩት ላንድ ማርክ የሚባል ግፉፍ ሆቴል ነው፡፡ ባለቤቱ ይህን ዓይነት ትልቅ ሆቴል ምን ሲል ሰራው አሰኝቶኛል ግርማ ሞገሱ! ፋሲል መናፈሻ ምሣ በላን፡፡ ከላንድ ማርክ ከፎቁ ላይ ሆኜ ጐንደርን ዙሪያ - ገባውን የማየት (Panoramic view) ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ የጋበዘኝ “ግጥም በመሶንቆ” የሚባል ፕሮግራም አዘጋጅ አካል ነወ፡፡ [ጉዋሳ የሄድኩት ደግሞ ከ “ኤን.ቲ.ኦ” ጋር ነው (ዝርዝሩን ወደ ኋላ አምጥቼ ዓላማና ሁነቱን እተርክላችኋለሁ ግጥም በመሰንቆ ታዋቂ ሰዎችን በመጋበዝ)] በየወሩ ይሄንኑ ይሠራል፡፡ ጌትነት እንየው፣ በረከት በላይነህ፣ ኤፍሬም ሥዩም… ከኔ በፊት መምጣታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ የፓኤቲክ - ጃዝ አመራር አባላትም ሙሉአቸውን ሄደው ነበር አሉ፡፡ አገር ላገር ግትም መናበብ ትልቅ ጸጋ ነው! ጥናቱን ይስጠን!! ይህ ፕሮግራም ቀድሞ ሲጀመር በመሰንቆ ብቻ ጨዋታ ይኖርና ግጥም ይፈስስበታል፤ አሉኝ፡፡ አሁን አሁን ክራርም፤ ዘመናዊ ሙዚቃም ተጨምሮበታል፡፡ እኔ የሄድኩበትን ፕሮግራም ልዩና በዓይነቱ አዲስ የሚያደርገው፣ ከዚህ ቀደም ፕሮግራሙ የሚካሄደው አዳራሽ ውስጥ ሲሆን አሁን በእኔ ጊዜ ግን ደጅ በላንድ ማርክ የተንጣለለ መስክ ላይ መካሄዱ ነው፡፡ አየሩ ይጥማል፡፡ ሰዉ አምፊ - ቲያትራዊ (ግማሽ- ክበብ) በሆነ ድባብ ግጥም ብሏል፡፡ ግጥም ብሎ ግጥም ይጠብቃል! ግጥም በናፍቆት የጐንደር ባህል ውስጥ መሪ ቦታ አለው፡፡ ለንጉሥ የሚገጠመውን ያህል ለአዘቦቱ ሰው፣ ለዜጋው፣ ለአሽከሩም ይገጠማል፡፡
አንድ ትዝ ያለኝን ነገረ ላጫውታችሁ፡፡
መልኬ ብርሃኔ የተባለ ጐንደሬ ወዳጄ አንዴ ማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት እሥር ቤት አብረን ሳለን፤ ስለ ጐንደር ምስኪን ገበሬ የተገጠመውን ነግሮኛል፡፡
ያ ምስኪን ገበሬ ስሙ ‘ና’ ስቲለው ነው፡፡ ና ስቲለው ማለት ፈጣሪ ና እስኪለው፤ አምላክ እስቲጠራው፣ ድረስ ይለፋል ለማለት ነው፡፡ ታዲያ የሱን ኑሮና ህይወት ለመግለጽ እንዲህ ብለው ገጥመዋል፡፡
“ሰኞ ማለስለስ ነው
ማክሰኞም ጐልጓሎ
ዕሮብ ዘር ዝሪ ነው፤
ሀሙስ አረም ማረም
ዐርብም አጨዳ ነው፤
ቅዳሜም ውቂያ ነው
እሁድ ጐተራ ነው፤
ና - እስቲለው ኮት ገዝቷል፣ መቼ ሊለብሰው ነው!”
ከእሁድ እስከ እሁድ ለኮት መልበሻ እንኳ ጊዜ አጥቶ ሲለፋ ይኖራል ነው ነገሩ፡፡ ጐንደር ያለጥርጥር የግጥም አገር ነው፡፡ የጀግና አገር ነውና ይዘፈንለታል፡፡ ይገጠምለታል፡፡
“መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም፤ ወንድ አንድ ሰው ሞተ” የተባለው እዚያ ነው፡፡
ያለነገር ---“ ገዴ ዙራ ዙራ፣ በዕንቁላሏ ላይ
ጊዜ እሚጠብቅ ሰው፣ ጅል ሊባል ነው ወይ! … አልተባለለትም፡፡
ያለነገርም፤
“ሞኞች ናቸው፣ ዳኞች ሞኞች ናቸው - ዋስ ጥራ ይላሉ
ከነዋሱስ ቢሄድ፣ ማንን ይይዛሉ!”
ተብሎ አልተገጠመለትም፡፡
እንግዲህ እዚህ ጐንደር አገር ነው የህይወት ገጠመኜን ለወጣቱ ላካፍልና ግጥም ላነብ የተጋበዝኩት፡፡
እንደልምድ ማጋራት ያወራኋቸው እሥር ቤት ሆኜ ስለተረጐምኩት “ነገም ሌላ ቀን ነው” የተባለ መጽሐፍ ነው፡፡ የማርጋሬት ሚሼል ጐን ዊዝ ዘ ዊንድ (Gone with the Wind) ነው፡፡ እና አንዳንድ የእሥር ቤት ገጠመኞቼንም አወጋኋቸው፡፡ አንዳንድ መከራ መጽሐፍ እስከመፃፍ ያስችላል፡፡ ግን ዋናው ትዕግሥቱና ጥንካሬው ወሳኝ መሆኑ ነው፡፡ ጊዜውን ከተጠቀሙበትና ፅናቱ ካለ ሥራ የማያሠራ ሁኔታ የለም!! የሚለው የሁልጊዜ አፅንዖቴ ነው፡፡ እሱንም  ተናግሬአለሁ፡፡አብረውኝ የጐንደር ወጣቶች ግጥም አንብበዋል፡፡ ጉልበት ያላቸው ግጥሞች በድራማዊ አነባበብ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ወዝና ደርዝ ያላቸው ግጥሞች ፈጥረዋል፡፡ ወጣት ግጥሞች በወጣት ፍል - ብስለት ቀርበው ነበር ለማለት ይቻላል! ቀስ  እያሉ የሚበስሉ ግጥሞችም አሉባቸው፡፡ ከድራማዊ አቀራረብ ወደ አርምሞአዊ ጥሞናዊ አነባበብ ይሸጋገራሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ የሌሎችን የአነባበብ ስልት መቅዳት እንደሚተውም ተስፋ አለኝ፡፡ እኔ ከራሴ “ከጥቁር ነጭ ግራጫ ግጥሞች፣ ከስውር ስፌት ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት፣ እንዲሁም በቅርቡ ከሚታተመው ስውር ስፌት ቁጥር ሶስት መራርጬ ነው ያነበብኩላቸው፡፡
ጐንደር ሄዶ ባህል ቤት ሳይደርሱ መምጣት መቼም ነውር ነው አሉ፡፡ እዚያም ሄጃለሁ፡፡ የሴት አታሞኛ (አታሞ መቺ) ማየት ማርኮኛል፡፡ የጐንደር ጨዋታ ቤት በጀግንነት የተሞላ ነው፡፡ ግጥሞቹ የጀግንነት እንፋሎት የአሞቃቸው ናቸው፡፡ ከአገሬው ግጥሞች በድጋሚ የሰማሁት ቢሆንም የምወደውን አግኝቻለሁ፡- “ደገኛ በሬውን ይለዋል አውግቼው
አትምጣ ብለሺኝ መጣሁ እረስቼው፡፡”
ከአዘጋጆቹ አንዷ የገጠመችው ግጥም ለየት ማለቱም፣ ቅርፅ- ወጣ ይዘቱም ማርኮኛል፡-
“አይቼ ሰምቼ ሁሌም ዝም የምለው
አይቶ እሚናገረው፣ ዐይኔ ስላለ ነው፡፡
ቀን ጨለማ ሳይል፣ ብርሃን ሳይሰጋ
ተራራ ሸለቆ፣ ቆላ ሳይል ደጋ
ልበ - ቢሱ ልቤ፣ ሄዷል ቀን ፍለጋ!”
ባለኝ አጭር ጊዜ በወፍ በረር እይታ ከአርባ ዓመት በኋላ አይቻት ከህንፃ ብዛትና ከባጃጅ ብር-ሽር-ሽው ሌላ ብዙ ለውጥ ያላየሁባትን ጎንደርን ብዙ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቤያለሁ፡፡ አንዳንድ የምለው ግን አለኝ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 3745 times