Saturday, 22 November 2014 12:04

ወሬ ሲበዛ ጭቃ ከግድግዳ ተፍረክርኮ ይወድቃል፡፡ ሙቀጫም ለጭፈራ ይነሳል፡፡

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ከብዙ ዓመታት በፊት ሰዎች እንደ ዛሬ ሳይሰለጥኑ በፊት፤ በአንዲት ትንሽ ከተማ አንድ እንደ ተዓምር የሚቆጠር ነገር ተፈጸመ፡፡ አንድ ቀንድ ያለው ጉጉት በአቅራቢያው ከሚገኘው ጫካ መጥቶ ከአንድ ሰው ግቢ ከሚገኝ የእህልና የከብት መኖ፣ እንዲሁም ጥራጥሬ መጋዘን  ውስጥ ይገባል፡፡ ሲነጋ እንዳይወጣ፤ ሌሎች ዶሮዎች ያዩኝና ልዩ ዓይነት ወፍ መሆኔን ሲረዱ ይጮሃሉ፡፡ ስለዚህ ዝም ብዬ ልቀመጥ ብሎ ወሰነ፡፡
ጠዋት የግቢው አሽከር ለከብቶች መኖ ሊወስድ ሲመጣ ጉጉቱን ጣራው አግዳሚ ላይ ሆኖ አየውና ደንግጦ “ጭራቅ! ጭራቅ!” እያለ እየጮኸ ወደ ጌትየው ሄዶ ተናገረ፡፡ የቤቱ ጌታም “አይ አንተ!  አንተንኮ እንደ እጄ መዳፍ ነው የማውቅህ፡፡ በሰፊ ሜዳ ቁራና ጥንብ - አንሣ የማባረር ልብ አለህ! አንዲት ጫጩት አንድ ጠባብ ቦታ ሞታ ብታይ ግን ወደዚያ ለመቅረብ ትልቅ ዱላ ፍለጋ ትሄዳለህ፡፡ ይሄን ጭራቅ ያልከውን እኔ ራሴ ሄጄ አየዋለሁ፡፡  ውሸት ቢሆን ወዮልህ!”
ጌትዬው  ወደ መጋዘን ገብቶ ሲያይ በድንጋጤ ተስፈንጥሮ ወጣ፡፡ ሮጦ ወደ ጎረቤቶቹ ሄዶ “ጎበዝ ማለቃችን ነው፡፡ አንድ አደገኛ ፍጡር ግቢዬ ገብቷል! ወጥቶ ወደ ከተማ ከገባ ህዝብ ማለቁ ነው፡፡ እንረዳዳና እዚሁ እርምጃ እንውሰድበት!” አለ፡፡
ወሬው ወዲያው ከመንደር መንደር በረረ፡፡ ከመንገድ መንገድ ሮጠ፡፡ ሰዉ ከፊሉ  ገጀራ፣ ከፊሉ ቆንጨራ፣  ከፊሉ ጦር፣ አካፋም፣ ማጭድም እያየዘ ወደግቢው ይመጣ ጀመር፡፡ ሰራዊት እንጂ አንድ ቀንዳም - ጉጉት ሊገድል የመጣ አይመስልም፡፡ በመጨረሻ ጭራሽ የከተማው ከንቲባ በሌሎች ሹማምንት ታጅበው መጡ፡፡ በተማው ለጥንቃቄ በየገበያው ምሽግ አሰርተዋል፡፡ አንድ የጎበዝ አለቃ ወደጉጉቱ ሄዶ ነበር፡፡ ድምፁን ሲሰማ በርግጎ ተመለሰ፡፡ ሌሎች ሁለት ሰዎች ሞከሩ፡፡
 ጉጉቱ ዓይኑን እያጉረጠረጠ በፍርሃት የሚያወጣው ድምፅ መብረቅ የመታቸው ያህል አስደግንጧቸው ዘለው ወጡ፡፡ በመጨረሻ አንድ መንዲስ የሚያህል ሰው፣ ያገሩ ጦረኛ ነው የሚባል ጀግና፣ ከጉጉቱ ሊተናነቅ ወስኖ መጣ፡፡ ከዛም በፉከራ ቃና “አንድን ጭራቅ “ጉድ! ጉድ!” በማለትና ዐይን ዐይኑን በማየት ልታባርሩት አትችሉም፡፡ ሁልሺም ቡከን ነሽ፡፡ ይሄን ጭራቅ ቀንዱን ይዤ ከጣራው ማውረድ አለብኝ! አለ፡፡ ሁለቱም የመጋዘኑ በር ብርግድ ብሎ ተከፈተ፡፡ አሁን ጉጉቱ ከጣራው  አግዳሚ እንጨት ላይ ተቀምጦ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ ጀግናው መሰላል አምጡልኝ አለ፡፡ መጣለት፡፡ ሰው ከፊሉ “ደፋር!” “አምበሳ!” አለው፡፡ ከፊሉ ይፀልይለት ጀመር፡፡
ጀግናው ወደ ጉጉቱ እየቀረበ ሄደ፡፡ ጉጉቱ ሁኔታውን በመጠራጠር የህዝቡን ጩኸት በመስማትና ምንም መውጫ እንደሌለው በማሰብ፤ ክንፎቹን አርገበገበ፡፡ ኩምቢውን ከፈተ፡፡ መንቆሩን ለጦርነት ያዘጋጀ መሰለ፡፡ ኩ-ፍ-ኩ-ኩ-ህ!” እያለ በፍጥነት መጮህ ጀመረ፡፡ ሰው “በለው!” “ያዘው” “አሳየው!” እያለ ከሥር ይጮህ ጀመር፡፡
“አይ ያገሬ ሰው! እኔ ያለሁበት ቦታ ቆመሽ ቢሆን አዳሜ ትንፍሽ አትይም ነበር!”
ጥቂት እርከን ለመውጣት ሞከረና ጀግናው፤ መርበትበት፣ መራድ ጀመረ፡፡ ቀስ እያለ በደረጃው ወረደ፡፡ ሰውም “አውሬው በትንፋሹ መርዞት ነው እንጂ የእኛ ጀግና እንዲህ ያለ ሰው አልነበረም፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ያለ አውሬ ፊት ቆመን ህይወታችንን ማጥፋት አለብን እንዴ?” እያለ መንሾካሾክ ጀመረ፡፡ “ከተማችንን እንዳያጠፋ ምንድንነው የምናደርገው ማለት ቀጠለ?”  በመጨረሻ ከንቲባው መፍትሄ አመጡ፡፡
“ከመዘጋጃ ቤቱ ወጪ ተደርጎ ለመጋዘኑ ባለቤት የገንዘብ ካሳ እንስጥ፡፡ ለእህሉም. ለጭዱም፣ ለነዶውም መግዣ ይካካስለትና መጋዘኑ ከነአደገኛው አውሬ ይቃጠል! አሁን ለኢኮኖሚ የምናስብበት ጊዜ አይደለም!” ብራቮ ተባለ! ተጨበጨበ!
መጋዘኑ በአራቱም አቅጣጫ እሳት ተለቀቀበት፡፡ ምስኪኑ ወፍ በነበልባል ተለብልቦ አሰቃቂ ሞት ሞተ!
*          *           *
ነገሩ “አይ መሬት ያለ ሰው!” ያልነውን ያስታውሰናል፡፡ ነገርን በቅጡ አለማየት አሳቻ ፍፃሜ ላይ ያደርሰናል፡፡ ስለሆነም ወፍ አይተን ጭራቅ አየን እንላለን፡፡ አገሬው መንገኛ ከሆነ እንግዲህ  ይህንኑ ጭራቅ ጭራና ቀንድ ጨምሮለት ያልሆነ  ስዕል ፈጥሮ መዐት ይፈጥራል፡፡ የሰማህ ላልሰማህ የተባለ ይመስል እንደአዋጅ - ቃል ወሬ ይለፍፋል፡፡ ከዚያ ያገሩ ሹማምንት ያገባናል በሚል በተሳሳተው ነገር ላይ መመሪያ ይጨምሩበታል፡፡ መፍትሄ የማይፈጥር፣ ችግር ብቻ የሚያወራ ህዝብ ያልታደለ ነው፡፡ ኑሮ እንጉርጉሮ እንዳይሆን ማሰብ ያሻል! በወሬ የሚኖር ሰው፣ ነገር ያባብሳል እንጂ አንድ የመፍትሔ ጠጠር አይጥልም፡፡ ጎበዙን በለው! በለው! ለማለት የተፈጠሩ ይመስል፤ “በቅሎ ግዙ ግዙ አንድ አምሌ ላያግዙ!” ይሆናል ግርግሩ፡፡ ራሳችን በፈጠርነው የተሳሳተ ምስል “አስፈሪ! አደገኛ! …” እያልን፤ እሱኑም ፈርተን፤ ሌላውንም አስፈርተን፣ እሳት እንለኩሳለን! ይሄው ነው የአገራችን ፖለቲካ ነገረ - ሥራ!
“ጥፋታችንን አናምን፣ ሀጢያታችንን አንቀበል
ሁሌ ዝግጁና ፈጣን፣ በሌላው ላይ ለመቸከል
ደባ ነው መንገዳችን ሰርክ
ለእምዬ የአብዬን እከክ፣ በጥበብ ቅብ ለመላከክ!”
እንዳለው ገጣሚው፣ ራሳችን የሰራነውን ጥፋት በፈረደበት የበታች ወይም ቀን የጣለው ላይ መላከክ ነው ስራችን፡፡ ጥንት በአንድ አገር ዕምነት. ፍየል የዋህ ናት ትባል ነበር፤ አሉ፡፡
በሥርየት ቀን ቄስ ፍየሏ ጭንቅላት ለይ እጁን አድርጎ፣ የህዝቡን ሀጢያት ይናዘዛል፡፡ ጥፋት ሁሉ ወደ የዋህ ፍየል ይሄዳል፡፡ ይተላለፋል፡፡ ከዚያ ፍየሏ ወደ በረሀ ትነዳለች፡፡ እዛው ትቀራለች፡፡ የሰዉን ኃጢያት ሁሉ ይዛለት ጠፋች ማለት ነው፡፡ እንግዲህ Scapegoat የሚለው የፈረንጆች ቃል ከዚህ ነው የመጣው” ሊባል ይችላል፡፡ በሌላ ላይ ማሳበብ፣ በሌሎች ላይ መጫን ነው የአበሻ ኑሮ ዘዴ፡፡ ማዖ የባህል አብዮቱ ከሽፎ ክፉኛ ሲወድቅበት ምንም ይቅርታ አልጠየቀም፡፡ ይልቁንም በከፍተኛው የፓርቲ አመራር አባል ላይ ላከከ፡፡ የግል ፀሐፊውንም እንኳ ከወንጀሉ ነፃ አላደረጋትም፡፡ የእኛን ጨምሮ በየትም አገር በዘመቻም፣ በፕሬስም፣ በማፍረስም፣ በመገንባትም አንዳንድ የዋህ ፍየል አይጠፋም፡፡ ያውም እንደ ሰበብ ተደርጎ ሲቆጠር የማያጉረመርም ፍየል! ሌላ ምሣሌ:- ጥንት ጃንሆይ ለፀሐፊ ትዕዛዙ በቃል መመሪያ ይሰጡ ነበር አሉ፡፡ ያ መመሪያ ወደ ሥራ ተመንዝሮ ውጤቱ ሰናይ ከሆነ ምስጋናው ለጃንሆይ ይሆናል፡፡ ያልተሳካ ከሆነ ግን እርግማኑ ከፀሐፊ ትዕዛዝ ራስ አይወርድም፡፡ ዓለም የሥርዓተ- መላከክ (escapegoatism) ዓለም ነው፡፡
በተግባርና በወሬ መካከል ያለው ገደል - አከል ርቀት ሳይገደብ ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ወሬ - ናፈቅ ትውልድ አገር ይሸረሽራል! “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚለው የአበው አነጋገር ቧልት አይደለም፡፡ “ወሬ ሲበዛ ጥበብ ዋዛ” እንደማለት ነው፡፡ ወሬ ሲበዛ ያልተሰራው ተሰራ፣ ያላሸነፈው አሸነፈ፣ ያልቀናው ቀና ማለትን ይወልዳል፡፡ ከጊዜ ብዛት ሰው ያምናል፡፡ ከዚያ ውሸት ሁሉ ዕውነት ይመስላል፡፡ “ወሬ ሲበዛ ጭቃ ከግድግዳ ተፍረክርኮ ይወድቃል፡፡ ሙቀጫም  ለጭፈራ ይነሳል” የሚለው የወላይታ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው!

Read 5172 times