Saturday, 22 November 2014 11:32

አፍራሽ ዘገባዎችን ያሰራጫሉ የተባሉ የግል ህትመቶች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

“የመንግስት ሚዲያዎች የአቅም ውስንነትና የህግና ሥነ-ምግባር ጥሰት ይታይባቸዋል” አፍራሽ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ ህትመቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና እንዲታረሙ ጥረት ቢደረግም ለውጥ ሊመጣ አልቻለም ያለው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፤ አሳታሚዎቹን ለህግ ለማቅረብ መረጃዎች ተጠናቅረው ለሚመለከታቸው አካላት እንደተላለፈ ገለፀ፡፡ ህትመቶቹ ከገንቢነት ይልቅ የአፍራሽነት ሚናን ይዘው የሚሰሩ ናቸው ብሏል ባለስልጣኑ፡፡
ብሮድካስት ባለስልጣን ባለፈው ሳምንት ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት  እንደገለፀው፤ የግል ህትመት ሚዲያዎች ከአደረጃጀታቸው ጀምረው አብዛኛዎቹ በኃላፊነት መንፈስ እየሰሩ የንግድ ዓላማቸውን ለማሳካት ሳይሆን የፖለቲካ ዓላማና ፍላጎትን ያለሙ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ህትመቶች በአገሪቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴ ውስጥ ከገንቢነት ይልቅ የአፍራሽነት ሚናን የመጫወት አስተሳሰብ ይዘው እየሰሩም ይገኛሉ ተብሏል፡፡
 በባለስልጣኑ አመታዊ ሪፖርት ላይ ሚዛናዊ ዘገባዎችን በማቅረብ፣ ህብረተሰቡ በአገሪቱ ስለሚከናወኑት እንቅስቃሴዎች ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ ተብለው የተጠቀሱ ሚዲያዎች ሲኖሩ፣ አፍራሽ ዘገባዎችን የሚያሰራጩና የሚስተዋሉባቸውን ክፍተቶች ለማረም ፈቃደኝነት የሌላቸው የተባሉም በዝርዝር ተገልፀዋል፡፡ አፍራሽ ዘገባ የሚያሰራጩ ህትመቶች እንዲታረሙ ጥረት ቢደረግም የሚፈለገው ለውጥ እንዳልመጣ በሪፖርቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡ ገንቢ ሚና የሚጫወቱት የህትመት ሚዲዎች በስርጭት ላይ ከመቆየት አኳያ የአከፋፋዮች ጫና እንዳለባቸው የጠቆመው ሪፖርቱ፤ አፍራሽ ዘገባ የሚያሰራጩት አብዛኞቹ በገበያ ውስጥ መቆየታቸው፣ የማይታወቅ የፋይናንስ ምንጭ እንዳላቸው የሚያመላክት በመሆኑ፣ የተጠናከረ የክትትልና የጥናት ሥራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡
ባለስልጣኑ የመንግስት ብሮድካስት ሚዲያውን አስመልክቶ በሪፖርቱ ላይ እንደገለፀው፤ የመንግስት ብሮድካስት ሚዲያው ምንም እንኳን በብሮድካስት አዋጁ የተጣለበትን ኃላፊነትና በልማቱ በኩል የራሱን ሚና ለመወጣት ጥረት የሚያደርግ ቢሆንም በአቀራረቡና አጀንዳ ቀርፆ አስተሳሰብን በመገንባት ረገድ የአቅም ውስንነት እንዳለበትና አልፎ አልፎም የህግና የስነ ምግባር ጥሰቶች እንደሚስተዋልበት ተጠቁሟል፡፡
ሪፖርቱ የግል ብሮድካስት ሚዲያውን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ፤ በአመዛኙ የአየር ጊዜያቸውን ወሳኝ ባልሆኑ ጉዳዮች የሚያውሉና በልማቱ ውስጥ ማበርከት የሚገባቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት የአመለካከት ችግር ያለባቸው እንደሆኑ ጠቅሶ፤ የሙያ ክህሎት እጥረት እንደሚታይባቸውም ጠቁሟል፡፡ ባለስልጣኑ በተያዘው በጀት ዓመት አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል፡፡   

Read 3077 times