Saturday, 22 November 2014 11:29

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኢቦላ ሰበብ እየተገለሉ ነው

Written by 
Rate this item
(9 votes)

የዋሽንግተን የጤና ዳይሬክተር ጆክሴል ጋርሺያ
የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የጤና ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ጆክሴል ጋርሺያ በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን በኢቦላ ምክንያት እየተገለሉ እንደሆኑ ዘ ዋሽንግተን ታይምስ ዘገበ፡፡
ስለ ኢቦላ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በተለይ በታክሲ ሾፌርነት በመስራት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎችን እያገለሉ እንደሚገኙ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ አሽከርካሪዎቹ አፍሪካውያን እንደሆኑ ሲያረጋግጡ ቫይረሱን ያስተላልፉብናል በሚል ስጋት ከመኪና እንደሚወርዱ ተናግረዋል፡፡
የመገኛኛ ብዙሃን ሰራተኛ የሆነ አንድ ግለሰብ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወደ አሜሪካ ሲገቡ ለምን የኢቦላ ምርመራ አይደረግላቸውም የሚል ጥያቄ እንዳቀረበላቸው ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ከሁለቱ አገራት ዜጎች ጋር የእጅ ሰላምታ የማይለዋወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሳል ፒስ ፌዴሬሽን የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ዳይሬክተሩ፤ የሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎችም በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴቸው በኢቦላ ሰበብ መገለል እንደሚደርስባቸው አስታውቀዋል፡፡
በዋሽንግተን ከሚኖሩ የሌሎች አገራት ዜጎች፣ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡

Read 2502 times