Saturday, 22 November 2014 11:23

የአውሮፓ ህብረት መንግስትንና ተቃዋሚዎችን ስለምርጫው ማነጋገር ጀመረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

            በ97 ዓ.ም እና የዛሬ አምስት አመት በተደረጉ ምርጫዎች ከመንግስት ጋር ክፉኛ የተወዛገበው የአውሮፓ ህብረት ታዛቢ ቡድን፤ ለዘንድሮው ምርጫ በታዛቢነት እንደማይጋበዝ የተገለፀ ሲሆን፤ ሰሞኑን የአውሮፓ አገራት ዲፕሎማቶች ምርጫውንና የፓርቲዎች እንቅስቃሴን በተመለከተ በየክልሉ እየተዘዋወሩ ማነጋገር ጀመሩ፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ እርዳታ በመስጠት የሚታወቀው የአውሮፓ ህብረት በምርጫ ታዛቢነት ባይጋበዝም፤ ከበርካታ ድሀ አገራት ጋር ባለው የትብብር ስምምነት መሰረት በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ፓርቲዎችን ማወያየትና መረጃዎችን መሰብሰብ ይችላል ተብሏል፡፡
በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር የመንግስት ሃላፊዎችና የፓርቲ ተወካዮችን፣ ምሁራንና የሲቪል ማህበራት መሪዎችን ማነጋገር የጀመሩት የአውሮፕ ዲፕሎማቶች፤ በአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን እንዲሁም የታዋቂ ፓርቲ መሪዎችን በተናጠል አነጋግረዋል፡፡ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ለምርጫ እንዴት እየተዘጋጁ እንደሆነ፤ በየክልሉ ተቃዋሚዎች ቢሮ ለመክፈትና ለመንቀሳቀስ የሚያጋጥማቸው ችግር፣ የህግ አከባበርና የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ጉዳዮች በዲፕሎማቶቹ ጉብኝት ላይ እየተነሱ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የህብረቱ ዲፕሎማቶች፣ ወደ ኦሮሚያ ክልል ከተሞች ከሚያደርጉት የጥናት ጉብኝት ጋር በተያያዘ ከክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድርና በርካታ የኦህዴድ አመራሮች፤ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ የኦፌኮ ተወካዮችን እንዲሁም የአንድነት አባላትን አነጋግረዋል፡፡
ከዚሁ ጐን ለጐን የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ከአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሸንታል ኸብረሻት ጋር እንዲተዋወቁ ተጋብዘው፣ የግንቦቱን  ምርጫ በተመለከተ አጭር ውይይት ማካሄዳቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፤ ከአምባሳደሯ ጋር የትውውቅ ፕሮግራም ከተከናወነ በኋላ ምርጫው ህግንና ስርአትን ተከትሎ መካሄድ እንዳለበት መነጋገራቸውን ጠቅሰው፤ የአውሮፓ ህብረት በምርጫው ዙሪያ ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከተቃዋሚዎች ጋር ተከታታይ ውይይት አደርጋለሁ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ ከአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጋር እንደተወያዩ ገልፀው፤ ነፃና ሚዛናዊ  ምርጫ የማካሄድና የመሳተፍ እድሉ ምን ያህል ነው? በሚለው ጉዳይ አጭር ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡ መድረክ በምርጫው ይሳተፍ እንደሆን ጥያቄ እንደቀረበላቸው ፕ/ር በየነ አስታውሰው፤ መድረክ ለምርጫው ሂደት ሲል ወደ ምርጫውና ሂደቱ ሊገባ ይችላል የሚል ምላሽ ሰጥተናል ብለዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎችም ከህብረቱ ጋር በ2007 ዓ.ም ምርጫ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በ1997 ዓ.ም እና በ2002 ዓ.ም ምርጫዎች ላይ በታዛቢነት ተጋብዞ ባወጣቸው ሪፖርቶች ከመንግስት ጋር መወዛገቡ የሚታወስ ሲሆን፤ በተለይ በ1997 ምርጫ የታዛቢ ቡድኑ መሪ የነበሩት አና ጎሜዝ ስለምርጫው ይፋ ባደረጉት ሪፖርት የአውሮፓ ህብረትና መንግስት ሆድና ጀርባ ሆነው ነበር፡፡

Read 2084 times