Saturday, 15 November 2014 11:24

ዋልያዎቹ ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ሙከራ ያደርጋሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የተስፋ ጭላንጭል አለው፡፡ ዛሬ ከሜዳው ውጭ በአልጀርስ ከአልጄርያ ጋር  እንዲሁም የፊታችን ረቡእ በአዲስ አበባ ከማላዊ አቻዎቹ ጋር በሚያደርጋቸው የ5ኛ እና 6ኛ ዙር  የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ከባድ ፈተና ይገጥመዋል፡፡ ዋልያዎቹ ለሁለቱ ጨዋታዎች የሁለት ሳምንት ዝግጅት ነበራቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት በቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አሰልጣኝ በነበሩት ሚቾ ከሚመራው የኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርገው 3ለ0 መሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡   
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዓመት በፊት በነበረው ስኬታማ ጉዞ ዘንድሮ መቀጠል አለመቻሉ የሚያሳስብ ሆኗል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በቅድመ ማጣርያ ፉክክር ብቻ በ2013 እኤአ ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ መሳተፍ የቻለ ነበር፡፡ በዚህ ውጤቱ በውድድሩ የምድብ ማጣርያ በቀጥታ መሳተፍ ቢችልም ፉክክሩ  ከብዶታል፡፡  በተለይም በፌደሬሽኑ ዙርያ ያሉ አስተዳደራዊ ድክመቶች፤ የበጀት መራቆት፤ በትጥቅ እና ሌሎች ቁሳቁሶች አለመሟላት፤ በጡረታ በጉዳት እና በቅጣት የስብስቡ መመናመን፤ በማበረታቻዎች ማነስ  ዋና አሰልጣኙ ማርያኖ ባሬቶ በገጠሟቸው የስራ ውጣውረዶች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
30ኛው የአፍሪካ ዋንጫን ልታዘጋጅ የነበረችው ሞሮኮ በኢቦላ ስጋት ውድድሩ በአንድ ዓመት እንዲሸጋሸግላት ብትጠይቅም ካፍ አስተናጋጅነቷ ለመንጠቅ ከውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ ሞሮኮን በመተካት አፍሪካ ዋንጫውን የሚያዘጋጅ አገር በሚቀጥለው ሳምንት ይታወቃል፡፡ አዘጋጁ ወዳልታወቀው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፉ ቡድኖችን የሚለዩት የማጣርያ ግጥሚያዎች ሰሞኑን በመላው አህጉሪቱ ይቀጥላሉ፡፡  አልጄርያ እና ኬፕቨርዴ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ሁለት አገራት ናቸው፡፡ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 2 ከአልጄርያ፤ ከማሊ እና ከማላዊ ጋር ሲደለደል የማለፍ ተስፋ እንደነበረው ይገለፅ ነበር፡፡ ዋልያዎቹ ቢያንስ በምድባቸው በሁለተኛ ደረጃ በመጨረስ ወይንም ከሁሉም ምድቦች ምርጥ ሦስኛነት ያልፋል የሚል ግምትም ተሰጥቷል፡፡  ባደረጋቸው አራት የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ቢያንስ 6 ነጥብ ሊያገኝ ቢገባውም ስላልሆነለት ግን የማለፍ ዕድሉ ጠቦበታል፡፡  በሶስቱ ጨዋታዎች  ሲሸነፍ አንዱን ከሜዳው ውጭ በማላዊ 3ለ2 እንዲሁም ሁለቱን በሜዳው በአልጄርያ እና በማሊ በተመሳሳይ 2ለ0 ውጤት በመረታቱ ነበር፡፡ በማጣርያው አራተኛ ዙር ጨዋታ ግን ከሜዳ ውጭ ማሊን 3ለ2 ሲያሸንፍ ፤ እድሉን ሙሉ ለሙሉ ከመመናመን አድኖታል፡፡ በ3 ነጥብ እና በ3 የግብ እዳ 3ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በሚቀሩት  ሁለት የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ዋልያዎቹ ከ4 ነጥብ በላይ ማግኘታቸው ተስፋቸውን ያጠናክረዋል፡፡ በተለይ ሁለቱ  ግጥሚያዎች ለማሊና ለኢትዮጵያ ወሳኝነት አላቸው፡፡ አልጄርያ ማለፏን ብታረጋግጥም በሁለቱም ቀሪ ጨዋታዎች ቡድናቸው በሙሉ አቋም በመሰለፍ ለማሸነፍ መዘጋጀቱን አሰልጣኙ ከሰሞኑ ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካ የእግር ኳስ ደረጃ በአንደኛነት የተቀመጠችው አልጄርያ በዓለም ያለችበት 15ኛ ደረጃ በአህጉሩ ቡድን የተመዘገበ ከፍተኛ ስኬት ነው፡፡ ዘንድሮ የአልጄርያው ክለብ ኢኤስ ሴቲፍ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን  ማግኘቱን ጨምሮ ብሄራዊ ቡድኑ ከመንፈቅ በፊት በተሳተፈበት 20ኛው የዓለም ዋንጫ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ለጥሎ ማለፍ በመድረስ አስደናቂ ስኬት ማስመዝገቡ ከባድ ቡድን ያደርገዋል፡፡ ቀይ ቀበሮዎችን የሚያሰለጥኑት ፈረንሳዊው ክርስቲያን ጉርኩፍ አገሪቱን ለአፍሪካ ዋንጫ ድል ለማብቃት ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡   23 ተጨዋቾች ከሁለት ሳምንት በፊት ጠርተዋል፡፡ ተጨዋቾቹ ከአውሮፓ አገራት ስፔን፤ እንግሊዝ፤ ጣሊያን፤ ፈረንሳይ፤ ፖርቱጋል እና ቱርክ ሊጎች ከሚወዳደሩ ክለቦች የተውጣጡ ናቸው፡፡  ሲድ ሙሳ በተባለው እና በአልጀርስ ከተማ በሚገኘው ብሄራዊ የልምምድ ማእከል  ለ10 ቀናት ዝግጅት ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል በምድብ 2 ሌላ የ4ኛ ዙር ጨዋታ ማሊ እና ማላዊ ይገናኛሉ፡፡ ይህ ግጥሚያ በተለይ ለምእራብ አፍሪካዋ ማሊ ወሳኝ ይሆናል፡፡ ማላዊ ብታሸንፍ ደግሞ ውጤቱ የኢትዮጵያን ዕድል ይደግፋል፡፡ የኢትዮጵያ የመጨረሻ ተጋጣሚ የሆነችው ማላዊ ከወር በፊት  በበጀት እጥረት  ለመውጣት አመንትታ በምድቡ ያደረጋቻቸው የጨዋታ ውጤቶች እንደሚያሰርዝ መዘገቡም ለኢትዮጵያ የማለፍ እድል ፈጥሮ ነበር፡፡ ሰሞኑን ግን ኤርቴል የተባለ ኩባንያ ለማላዊ ፌደሬሽን የበጀት ድጋፍ በመስጠቱ ስጋቱን አብርዶታል፡፡ ማላዊ ከውድድሩ ብትወጣ ኖሮ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የገንዘብ ቅጣት እና የ2 አመት እግድ ሊጥልባት ይችል ነበር፡

Read 2693 times