Saturday, 15 November 2014 11:13

በናይጀሪያ ባለፉት 18 ወራት ከ255 በላይ ተማሪዎች በአሸባሪዎች ተገድለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቦኮ ሃራም በአንድ ቀን ብቻ 209 ትምህርት ቤቶችን አቃጥሏል
ፕሬዚዳንቱ ዳግም ከተመረጥኩ ቦኮ ሃራምንና ሙስናን አጠፋለሁ ብለዋል

          ባለፈው ሰኞና ረቡዕ  ዮቤ በተባለ የናይጀሪያ ግዛት በምትገኘው ፖቲስኩም ከተማና  ኮንታጎራ በተባለች ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤትና ኮሌጅ ላይ በአጥፍቶ ጠፊዎች በተፈጸሙ የቦንብ ፍንዳታዎች  የሞቱትን ከ52 በላይ ተማሪዎች ጨምሮ፣ በአገሪቱ ባለፉት 18 ወራት ከ255 በላይ ተማሪዎች በአሸባሪዎች እንደተገደሉ ተዘገበ፡፡የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፤ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ዜጎችን ለህልፈት በመዳረግ ላይ የሚገኘውን ቦኮ ሃራም የተባለ ቡድንና ሙስናን ከአገሪቱ ለማጥፋት በሚል ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡
የምዕራባውያን ትምህርት መቆም አለበት የሚል አቋም ይዞ የሚንቀሳቀሰው ቦኮ ሃራም የተባለ የአሸባሪዎች ቡድን፣ በተለይ ካለፈው አመት ግንቦት ወር ጀምሮ በአገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሽብር ጥቃት መፈጸሙን አጠናክሮ መቀጠሉን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሰኞና ረቡዕ የተከሰቱት ጥቃቶችም በዚሁ አሸባሪ ቡድን እንደተፈጸሙ ይገመታል ብሏል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ ወር በቺቦክ ከተማ ወደሚገኘው ትምህርት ቤታቸው በማምራት ላይ የነበሩ 276 ናይጀሪያውያን ልጃገረዶችን የጠለፈው አሸባሪ ቡድኑ፤ በተማሪዎች ላይ ግድያ መፈጸም ከጀመረ መቆየቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ቦኮ ሃራም ከሳምንታት በፊት ካንኮ በተባለች ከተማ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በከፈተው ተኩስ፣ 13 ያህል ተማሪዎችን መግደሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ሌሎች 15 ተማሪዎችን እንደገደለም  አክሎ ገልጧል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር በዮቢ ግዛት በሚገኝ የመንግስት ኮሌጅ ላይ ባደረሰው ጥቃት 59 ተማሪዎች መሞታቸውን፤ በመስከረም ወር ላይ በግብርና ማሰልጠኛ ተቋም 44 ተማሪዎችንና መምህራንን መግደሉን፤ በሃምሌ ወር በማሙዱ ከተማ አዳሪ ትምህርት ቤት ባደረሰው ጥቃት 29 ተማሪዎችና መምህራን መሞታቸውን አስታውሷል፡፡ ቦኮ ሃራም ባለፈው ወር፣ 209 ትምህርት ቤቶችን ማቃጠሉንና በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የንብረት ውድመት መፈጸሙን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ለቦኮ ሃራም ጥቃት ተገቢውን ምላሽ አልሰጡም በሚል በዜጎቻቸው እየተተቹ ያሉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን በበኩላቸው፤ ቦኮ ሃራምንና ሙስናን ከአገሪቱ የማጥፋት አላማቸውን ከግብ ለማድረስ ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ አገሪቱንና ዜጎቿን ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል ያሉት ጆናታን፣ ከተመረጡ ቡድኑ ያገታቸውን ልጃገረዶች እንደሚያስለቅቁና የሽብር ሰንሰለቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚበጣጥሱ ቃል ገብተዋል፡፡

Read 1474 times