Saturday, 15 November 2014 11:14

በሰመራ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ተመረቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

          የዛሬ ሳምንት በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ ሰመራ ውስጥ “አግዳ” የተባለ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴልና ሪዞርት ተመርቋል፡፡ ሆቴሉ አሁንም ግንባታው ያልተጠናቀቀ ቢሆንም እስካሁን 260 ሚሊዮን ብር እንደወጣበት ተገልጿል፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅ 200 አልጋዎች ይኖሩታል የተባለው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል፤ በአሁኑ ሰዓት በስራ ላይ ያሉ 60 የመኝታ ክፍሎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሶስት ባሮችና ሁለት ሬስቶራንቶች፣ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ለአምስት ኮከብ ሆቴል የሚመጥን የመዋኛ ገንዳ፣ ሲኒማ ቤት፣  ነፋሻማ የሆነ የተንጣለለ ግቢና ሌሎች አገልግሎቶችም ተሟልቶለታል፡፡ ለ150 ጊዜያዊና ለ60 ቋሚ ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረው አግዳ ሆቴልና ሪዞርት፤ በአሁኑ ሰዓት የአገር ውስጥና ውጭ ጎብኚዎችን በብቃት በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
ከመዲናዋ በ560 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ እንዴት 260 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ለማድረግ ደፈሩ የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ አሊ፤ “በዚህ ቦታ ላይ ኢንቨስት ላደርግ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ስመካከር እንደፈተና የቀረበልኝ አሁን የተነሳው ጥያቄ ነው፤ ብዙ ወዳጅ ዘመድ በስጋትና በጭንቀት ከርመው አሁን ለምረቃው ሲያዩት እፎይ ብለዋል” ይላሉ፡፡
“በዚህ ቦታ ላይ ይህንን ሆቴል ለመገንባት ስነሳ ትርፍና ኪሳራ አስልቼ፣ ከቢዝነስ አኳያ አይቼው ሳይሆን ለክልሉና ለህዝቡ ያለኝን ፍቅር ለመግለፅ ነው፡፡ ለክልሉና ለህዝቡ ያለን ፍቅር ከእኔ እድሜ የጀመረ ሳይሆን ከአያቶቼ እየተወራረሰ የመጣ ነው” ያሉት ትግራይ ተወልደው ያደጉት የ44 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ አሊ ግደይ፤ እንዲያው በደረቁ ህዝቡንም ክልሉንም እወዳለሁ ከማለት አንድ ቁምነገር ያለው ስራ ሰርቶ በተግባር ፍቅርን መግለፅ ተገቢ በመሆኑ ይህንን ሆቴል መገንባታቸውን፣ በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ከሆቴል ግንባታው በፊት በዚሁ አካባቢ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ትልቅ ተሳትፎ እንደነበራቸውም ገልፀዋል፡፡
“እርግጥ ነው እኛ በዚህ ከተማ ግንባታ ስንጀምር አየር መንገድ አልነበረም፤ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክትም ገና ውጥን ነበር፣ ደረቅ ወደብም አልነበረም” ያሉት ባለሃብቱ፤ በአሁኑ ሰዓት ከላይ የተጠቀሱት በሙሉ ስራ በመጀመራቸው የቱሪስት ፍሰቱ መጨመሩንና ለበጎ ስራ ብለው የጀመሩት ስራ አሁን ከቢዝነስ አኳያ ቢታሰብም የሚያስከፋ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ የክልሉ መንግስት ተባባሪነት ለዚህ እንዳደረሳቸው የተናገሩት ባለሀብቱ፤ ከ8 ዓመት በፊት መሬቱን ከሊዝ ነፃ በሆነ መንገድ እንዳገኙም አስታውሰዋል፡፡
የአፋር ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢስማኤል አሊሴሮ በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ በሆቴሉ እዚህ መድረስ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ “እኛ የማንወደው መሬት ወስዶ አጥሮ የሚያስቀምጥ እንጂ በአግባቡ ለሚሰራ ሰው የፈለገውን ያህል መሬት ወስዶ እንዲሰራ እንፈልጋለን” ካሉ በኋላ፣ የእኚህን ባለሀብት ብርታትና ጥንካሬ እንደ ምሳሌ በመቁጠር፣ ፍላጎት ያለው ኢንቨስተር በየትኛውም ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርግ ግብዣ አቅርበዋል፡፡
በሆቴሉ ምረቃ እለት ያገኘናቸው ነጋሽ ካህሳይ አባይ የተባሉ የእድሜ ባለፀጋ፤ ሆቴሉን ለመመረቅ ከአዲስ አበባ መሄዳቸውንና የአቶ አሊ ግደይ ዘመድ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ “አሊ በፊውዳል ስርአት ጊዜ የባላባት ልጅ ነበር፤ አባቱ አቶ ግደይ ፈጣንና የስራ ሰው ነበሩ፤ የአባቱን ፈለግ ተከትሎ ለዚህ በመድረሱ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል፡፡ “አፋር የእናቴ አገር ስለሆነ በደንብ አውቀዋለሁ፤ እዚህ ቦታ ግንባታ ሲጀምር ይሳካ ይሆን የሚል ስጋት ነበረኝ፤ እድሜ ሰጥቶኝ ይህን በማየቴ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል - አዛውንቱ፡፡
የአራት ልጆች እናትና የአቶ አሊ ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ አዜብ ሃጎስ በበኩላቸው፤ ሆቴሉ በዚህ ቦታ ይሰራ ሲባል ቀላል መስሏቸው እንደነበር፤ ነገር ግን ከተጀመረ በኋላ በርካታ ፈተናዎች እንደገጠሟቸው ይናገራሉ፡፡ “ባለፉት ስምንት አመታት ልጆችን ለብቻ ማሳደግ፣ አዲስ አበባ የሚገኘውን የከባድ ማሽነሪዎች አከራይ ድርጅት መምራት፤ ባለቤቴ  በሳምንት ሁለት ጊዜ ከአዲስ አበባ ሰመራ፣ ከሰመራ አዲስ አበባ መመላለሱ ከባድ ፈተና ቢሆንብኝም እንደምንም ተቋቁሜ ሆቴሉ ለዚህ በመብቃቱ ከልክ በላይ ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል፡፡
አቶ አሊ ግደይ፤ ለሆቴሉ ግብአት የሚሆኑ የጓሮ አትክልቶች፣ የስጋና የወተት ተዋፅኦዎች ለማምረት የአግሮ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ያወጡ ሲሆን 50ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ወስደው ለማልማት እየተዘጋጁ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

Read 3444 times