Saturday, 15 November 2014 11:06

የዲፕሎማት ሚስቶች ባዛር ያካሂዳሉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ ያሉ የዲፕሎማት ሚስቶች ቡድን በሚቀጥለው ቅዳሜ ዓመታዊውን የበጎ አድራጎት ባዛር በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
ከ25 ዓመት በፊት የተመሰረተው የዲፕሎማት ሚስቶች ቡድን፣ ከየአገሮቻቸው እያስመጡ የሚሸጧቸውን የተለያዩ ቁሶች ገቢ፣ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚውል የዘንድሮው የቡድኑ ፕሬዚዳንት በአፍሪካ ህብረት የአሜሪካ አምባሳደር ባለቤት ዶ/ር ሊላይ ስላሴ ገልጸዋል፡፡
ሴቶቹ ባዛሩን የሚያዘጋጁት በየተራ በተለያዩ ኤምባሲዎች ግቢና በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እንደነበር የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፣ በባዛሩ የሚሳተፉ የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ቁጥር እየጨመረ ስለሄደ፣ ሁሉንም ለማሳተፍ ከ2002 ጀምሮ ባዛሩ በሚሌኒየም አዳራሽ እየተካሄደ መሆኑንና ባለፈው ዓመት ከ10ሺህ በላይ ሰዎች መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት የባዛሩን ማዘጋጃ ስፍራ ክፍያና የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች በሙሉ ስፖንሰሮቻችን ስለሸፈኑልን ከመቶ ፐርሰንት ትርፍ ጋር ከባዛሩ ያገኘነውን ከሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ብር በላይ በመላ አገሪቷ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ከ25 በላይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሰጥቶናል ብለዋል፡፡
ሚስ ኤሪካ አሸር የድጋፍ ጠያቂ ድርጅቶች ፕሮፖዛል አጣሪ ኮሚቴ ኃላፊ ሲሆኑ በየዓመቱ ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች፣ በርካታ የተለያዩ የድጋፍ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡላቸው ጠቅሰው “የቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ለሴቶች፣ ለህፃናትና በኢትዮጵያ እጅግ ተጠቂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለሚያደርጉ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ነው” ብለዋል፡፡
የዲፕሎማት ሚስቶቹ ባለፉት ዓመታት የመማሪያ ክፍል ጥበት ላለባቸው ት/ቤቶች፣ የመማሪያና የመፀዳጃ ክፍሎች ግንባታ፣ ለቁሳቁስና ለመጻሕፍት መግዣ እንዲሁም ለክሊኒኮች የማዋለጃ አልጋና የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የውሃ እጥረት ላለባቸው ማህበረሰቦች የውሃ ጉድጓድ ማስቆፈራቸውን፣ መኖሪያ ለሌላቸው አረጋውያን ቤት መስጠታቸውን፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎች የምክርና የሕይወት ክህሎት መስጫና ከስጋ ደዌ በሽታ ለዳኑ አረጋዊ ሴቶች የሽመና ማዕከል ማቋቋማቸውን፣ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ለቀዶ ሕክምና አገልግሎት ድጋፍ ማድረጋቸውን የዘንድሮው የቡድኑ ተወካዮች አስረድተዋል፡፡
የዛሬ ሳምንት በሚሌኒየም አዳራሽ ከጧቱ 4 እስከ 10 ሰዓት በሚቆየው ባዛር፣ ከ60 በላይ ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃሉ ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ከአምናው የበለጠ ገቢ ለማሰባሰብ ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የባዛሩ ተሳታፊዎች በአገራቸው የታወቀና ለየት ያለ ነገር ይዘው በመቅረብ ይሸጣሉ ያሉት ዶ/ር ሊላይ፤ የተለያዩ ጌጣ ጌጦች፣ የየአገሮቹ ምግቦች፣ መጠጦችና የተለያዩ ምርቶች ይቀርባሉ ብለዋል፡፡ በዚሁ ቡድን ድጋፍ የተደረገላቸው ከ20 በላይ የማህበረሰብ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን አቅርበው እንደሚሸጡም ታውቋል፡፡
የባዛሩ መግቢያ ትኬት ከሕዳር 1 እስከ 12 ድረስ በሂልተን ሆቴል ከጧቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ለአዋቂዎች በ30 ብር፣ ለሕፃናት በ10 ብር እየተሸጡ ነው፡፡


Read 995 times