Saturday, 15 November 2014 10:54

የጉራጌ አገር ጉዞዬ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኮንን-
Rate this item
(3 votes)

“እሼ እዛው ነዋሪ ገበሬ ነው፡፡ ሞቅ ይለዋል! አንዱ ገንዘብ ሰጥቶ ምግብ በሳህን አርጎ ሂድ ወደሚስትህ ይለዋል፡፡
ይሄዳል፡፡ ግን በጨለማ በቀጭኑ ድንጋያማ የዘሙቴ መንገድ ሲሄድ ገንዘቡ ይጠፋዋል፡፡ ሳህኑን መሬት አስቀምጦ ገንዘብ
ፍለጋ ይመለሳል፡፡ ገንዘቡ የለም፡፡

     ታሪኩ የተባለው የማህበሩ አባል ቡታጅራ አካባቢ ሌላ የጉራጌ በዓል አክብሮ ስንትና ስንት ኪሜ ብቻውን ነድቶ ዘሙቴ መጣ፡፡ ጉድ ተባለ! ለጥቂት ወራት ጀርመን ከርሞ የመጣ ነው፡፡ ለመስዋዕትነቱ ሁሉም አድናቆቱን ችሮታል! እጅግ ሞቅ ያለ ወንድማዊ አቀባበል ነው የተደረገለት! ቤቱ በብርሃናማ ፊቶች ተጥለቀለቀ፡፡ ታሪኩን፤ የዘሙቴ መንፈስ ኃይሉ የሳበው ይመስለኛል፡፡
ባለፈው ሳምንት ህይወታቸው ማለፉን የነገርኳችሁ አቶ ጃቢር ቱፈር ይህን ነበር ያሉኝ፡፡
“በየት ነው የሚሄዱት?”
“በቡታጅራ በኩል በዝዋይ ነው የምሄደው”
“ወዴት? ወደ አዋሳ ነው የሚሄዱ?”
“የለም ለኩ ነኝ! ከአዋሳ አልፋለሁ፡፡”
“በዓመት ነው የሚመጡት ማለት ነው?”
“አዎን - አዎ!”
“ስለዘሙቴ ማርያም ልጽፍ ነው” አልኳቸው፡፡
“ይባርክህ፡፡ የዘሙቴ አምላክ ይርዳህ፡፡ እኛንም የዓመት ሰው ይበለን - የዛሬ ዓመትም እንዳትቀር! ትውልድ እንዳይረሳ አድርጉ … እኔ ታደሰ ተክሌን ሁለት ኣመት እበልጠዋለሁ፡፡ ታሟል በጣም - እግዚአብሔር ይማረው፡፡” (የሰው ህይወት ይገርማል! አቶ ታደሰ በህይወት አሉ፡፡ እኒህኛው አለፉ ምን ይደረግ፡፡ ሁን ያላለው አይሆን!) ድምፃቸው እንዴት ጠንካራ፣ አካላቸው እንዴት ቀልጣፋ፣ እንደነበር አሁንም ይታወሰኛል (ነብሳቸውን ይማር ፈጣሪ!)
ልጃቸው መጥቶ እንሂድ ሲላቸው ተሰነባበትን!
ማታ የጉራጌ ጭፈራ ውድድር ተካሂዷል፡፡ በአብነት አጎናፍር ዘፈን ዳንስ ቀልጧል፡፡ ጤናዬና ታከለ፤ የእኔን አዲሱን መፅሀፍ “ስውር ስፌትን” ተሸልመዋል፡፡ የሚደንቅ ሞቅታና ድባብ ነበረው፡፡ ከምፕ ፋየር እንዳናደርግ ዝናብ ገቶን ነው ቤት ያረግነው፡፡
“ምን ያል ጭፈራ ነው፣ ይሄ ጉራጊኛ
መለየት አቃተን ዳንሱን ከዳንሰኛ!” አሰኝቶኛል፡፡
የማህበሩ አባላት መንፈስ
የማህበሩ አባላት፣ ደስታ፣ ፈንጠዝያ፣ ጨዋታ ይችላሉ፡፡ እርስ በርስ ሲተራረቡ በሳቅ ይገላሉ፡፡ ካርታ ሲጫወቱ ያለው ቀልድ የሚደንቅ ነው - ይህን ተገርሜ ሳይ አንዱ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ?
“አንዱ በካርታ ጨዋታ 500 ብር በልቶ ይፎክራል፡፡ ሌላው 2500 ብር የበላ ምንም የማይናገር ደሞ አለ፡፡
 ይህን ያየ ተራቢ “ፍየል አንድ ስትወልድ ጩኸቷ አገር ያስለቅቃል፡፡ አሳማ ግን መአት ስትወልድ ድምጿ አይሰማም!!” አለ፡፡
አንደኛው በጣም ዘና የሚያደርጋቸው ተራቢ አባል ካርታ ሊዘጋ ሲል ብድግ ይልና ጮክ ብሎ እንደሬስሊንግ አጫዋች “This is 500 kg from East Africa Ethiopia” ይልና ያሸነፈበትን ካርታ ጠረጴዛ ላይ ያነጥፈዋል፡፡ ካርታውን ስከታተል፤ ስለ እሼ ያወራሉ፡፡
“እሼ እዛው ነዋሪ ገበሬ ነው፡፡ ሞቅ ይለዋል! አንዱ ገንዘብ ሰጥቶ ምግብ በሳህን አርጎ ሂድ ወደሚስትህ ይለዋል፡፡ ይሄዳል፡፡ ግን በጨለማ በቀጭኑ ድንጋያማ የዘሙቴ መንገድ ሲሄድ ገንዘቡ ይጠፋዋል፡፡ ሳህኑን መሬት አስቀምጦ ገንዘብ ፍለጋ ይመለሳል፡፡ ገንዘቡ የለም፡፡
ሲመለስ ሳህኑን የት እንዳደረገው ያጣዋል፡፡ ቡድኑ በሙሉ በሱ ሁለት - አጣነት ጠዋት እንደጉድ ሲስቅ ያረፋፍዳል፡፡
ቀልደኛው፤ ካርታው ተጫዋች እየተጫወተ፣ ቀልድ ማውራት ልማዱ ነው - አሁንም ይቀልዳል፡፡
“Lack of money, lack of power ካለብህ skill ለማውጣት very hard ይላል፡፡ (ገንዘብም ሀይልም ከሌለህ ክህሎት አይኖርህም ማለቱ መሰለኝ) ይቀጥልና “እዚህ አገር የሚሰራው ሰው በጣም small ነው፡፡ እኛ ብቻ ነን የምንሠራው፡፡ ሌላው ተረት ብቻ ነው!”
“You know shit ነው! Shit is not አንሶላ! ገባችሁ?”
እንዲሁ ሲከራከር ሲሟገት የሚያድርም አጋጥሞኛል፡፡ ክርክርን እንደሱስ የሚይዙ ሰዎች እንዳሉ ተረድቻለሁ፡፡ ግን እንደጨዋታው ይረኩበታል፡፡ “ገባህ ወይስ ግራ ገባህ” ይላል ተናግሮ ተናግሮ፡፡
ካርታ ከሚጫወቱት ዙሪያ ያለው ቀልድ ይገርማል፡፡ “ዳያስፖራ” የሚባል የቅፅል ስም ያለው ከአሜሪካ የመጣ የማህበሩ አባል አለ፡፡ ካርታ ተበልቶ ተኛ!
ይሄኔ ያ ተረበኛ፤ “በዓለም ላይ በፋይናንስ እጥረት የተኛ የመጀመሪያ ዳያስፖራ አንተ ብቻ ነህ!” አለው፡፡ ዳያስፖራው በእልህ ብድግ ብሎ” እሺ ዶላር ወይም ዩሮ የሚመነዝረኝ አለ ልብ ያለው?!” አለ፡፡ ከዚያ 1200፣ 1400፣ እያሉ ቀለዱበት፡፡ ዋጋ አዋደቁበት!
ተረበኛው ይቀጥላል፡- “ማንም ሰው በ14 ዓመቱ ውጪ ካደረ ቁማርተኛ ነው የሚሆነው” ብሏል አርስቶትል፡፡ አንደበተ - ቀልጣፎችም አሉ፡፡ አንዱ ተናጋሪ አንዱን ሲገልፀው “ዕድሜው 65፣ ኪሎው 67 ነው፤ ጸሐይ መሞቅ ይወዳል፡፡
 ጆሮው አይሰማም፣ ቀዝቃዛ ነገር አይወድም፣ የሚበላውንና የሚጠጣውን አይመርጥም፡፡
ኪሎውን በየቦታው ይለካል …” ይለዋል፡፡ ደራሲ ከሚፈጥረው ባህሪ የላቀ አተራረብ ነው ያላቸው፡፡
ዘሙቴ ማርያም መዝናናት፣ መንፈሳዊነት፣ ክትፎ፣ አይቤ፣ ጎመን፣ ኖርማል ጎመን፣ ቅቅል (እንዲህ የሚጥም ቅቅል በልቼ የማቅ አልመሰለኝም) ማስቀደስ፣ መፀለይ፣ መመራረቅ … የጉራጌ አገር መስቀል ጧትም፣ ምሳም፣ ራትም ክትፎ መጠጣት ይመስለኝ ነበር፡፡ አይደለም! እንዲያውም እርካታው ልዩ ልዩ ምግብ መቅረቡ ነው! ከሁሉ የሚበልጠው ግን ፍቅሩና የደስታው መንፈስ ነው፡፡ ምግቡማ አዲሳባም አለ፡፡
የዚያን መንፈስ ኃይል ለመለካት አይቻልም፡፡ ከተፈጥሮ የፈለቀ ነው፡፡ ተፈጥሮ የሚያሰርጽብን መንፈስ ነውና ተፈጥሮ ጋ በመሄድ ብቻ የሚገኝ ነው!
በክትፎው ፏፏቴ መሀል ስለበዓሉ የጠየኳቸው አንድ መምህር ስለዘሙቴ ማርያምና ክብረበዓሉ ያለኝ መንፈሱን ያጠናክረዋል፡፡
“የእመቤታችን የቅድስተ-ቅዱሳን ድንግል ማሪያም በዓል ነው፡፡ ዕጥፍ-ድርብ ከመስቀል ጋር መገናኘቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለመስቀል ልዩ ቦታ አለን፡፡
ኢትዮጵያ በመፅሀፍ ቅዱስ 42 ጊዜ ተፅፋለች፡፡ ዋናው ግማደ-መስቀሉ ግሸን ማርያም እዚሁ አለ፡፡ ፅላቱም እዚሁ አለ፡፡ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሲሰቀል እመቤታችንን ከዮሐንስ ጋር ያስተሳሰረበት ዕለት ነው፡፡ የማሪያም መንፈስ እዚህጋ አለልህ!... የዘሙቴ ፀጋም እዚህ አለ፡፡
“እግዜሃር መኖሩ በፍጥረቱ ስለፍጥረቱ” ይታወቃል - ያለው ነው ሃዋርያው ጳውሎስ…” የአቶ አበበ ወልደማርያም ግቢ መንፈስ፣ ሁሉን በፍቅር ያስተሳሰረ፣ ሁሉን በሰላም ያቆራኘ፣ ይህ ወሰንህ ይህ ዲካህ የማይባል፣ በአዘቦት ሰው መለኪያ የማይሰፈር ነው፡፡
እንዲያው በረከት ነው፡፡ እንዲያው ፀጋ ነው፡፡ ከዓመት ዓመት ሁሉን በየፍላጎቱ ዙሪያ ያቀፈ መንፈስ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እኔን ከነዚህ ወዳጆቼ ያቆራኘን ዕፁብ መንፈስ ነው፡፡ ለአቶ አበበ፣ ለልጆቻቸው ለልጅ ልጆቻቸው እንዲሁም ለዘሙቴ ወዳጆች “ኬር!” ይሁን!!  
ስንመለስ ልክ ባለእግዚሃር ጋ መኪናችን ተበላሸ፡፡ እዛው ቦታ ሚኒባስ ባጋጣሚ መጣች፡፡ ተኮናተርናት፡፡ መኪናችንን ለመስራት እንዳረፍን እዛው አጠገብ ጣሳ ባጠና ላይ አየን፡፡ “አረቄ!” ካቲካላ አለ ማለት ነው፡፡
ተፈጥሮ ሁሉ ቦታ አማኙን አይረሳም፡፡ ኮመኮምነው፡፡ ዘሙቴ የጋበዘችኝ የወጪ መሆኑ ነው!! “ኬር” ብላ ሸኘችን ዘሙቴ!!



Read 4035 times