Saturday, 15 November 2014 10:40

ወዴት እየሄድን ነው?!

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(6 votes)

         እንደ ሀገር እየተጓዝንበት ያለው ጎዳና ትክክል ነው ወይ? ጉዞዋችንስ? እውነት የያዝነው መንገድ ካሰብንበት ያደርሰናል? ወዴት እየሄድን ነው? ሠርክ በውስጤ የሚመላለሱ፣ አእምሮዬም መልስ ፍለጋ የሚደክምላቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እንድጠይቅ የሚያደርገኝ ደግሞ አንድም በየመስኩ እየተጓዝንበት ያለው ጎዳና እና የጉዞው ስልት በበቂ የተጠና ስለማይመስለኝ፣ አንድም ከማስተዋል ይልቅ በጥድፊያና በ“በል በል” ስሜት የተቃኘ ስለሚመስለኝ ነው፡፡ አስተያየቴ ግብታዊ ቢመስልም ዝግ ብላችሁ ስታስተውሉት እንደምንስማማ ተስፋ በማድረግ ጥያቄዬን ይዤ ልቀጥል፡፡ ወዴት እየሄድን ነው?!
ጥያቄውን የሚመልሱ የሚመስሉ (የሚመስሉ ነው ያልኩት) ንግግሮችን ከተለያዩ እቅዶችና አቅጣጫዎች ላይ አንብበን ወይንም ሲነበብ ሰምተን፣ እንዲሁም ከመንግስት ሹማምንት አንደበት ሲነገር አድምጠን ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው ለማመን መስማት አንዱ ምክንያት ቢሆንም የምንሰማው ከምናየው ጋር ካልሰመረ ግን ለማመን ይገደናል፡፡ (ደግሞም ከምንሰማው ይልቅ የምናየው ውሃ ይቋጥራልና የምናየውን እናምናለን፡፡) እናም ገለጻዎቹን በአንድም ሆነ በብዙ ምክንያቶች ለማመን እቸገራለሁ፡፡ ለዚህም አንድ ሁለት ምክንያቶችን ላንሳ፡፡
አንደኛ የአስተያየቶቹ ባለቤት “ጉዞውን የሚመራው” መንግስት በመሆኑ “ባስያዘን” ጎዳና ላይ በቂ ጥናቶችን ከማድረግ ይልቅ ለአላስፈላጊ ፕሮፓጋንዳዎች ትኩረት በመስጠት ላይ የሚጠመድ ስለሚመስለኝ ነው፡፡ ይህንንም በየጊዜው ትክክለኛ አቅጣጫዎች ናቸው ብሎ ካወጃቸው፣ አውጆም ከተገበራቸው ሆኖም (እሱ በገሀድ ባያምንም) ብዙም ሳይቆይ ከሰረዛቸው (ሲተቻቸው ባንሰማም) አቅጣጫዎቹና ተግባራቱ በተደጋጋሚ ታዝበናል፡፡
ሁለተኛ በየመስኩ የተቀመጡት ሕጎችና መመሪያዎች ለአንድ ግብ የቆሙ እንዲሆኑ ስለሚጠበቅ እርስ በርስ ሊመጋገቡና ሊናበቡ የሚገባ ቢሆንም ከዚያ ይልቅ እርስ በርስ የሚጋጩ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ አለመናበብና እርስ በርስ መጋጨት በአንድ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ክፍለ ከተሞች ውስጥ ወይንም በአንድ ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ውስጥ የተለያዩ ሕጎች/መመሪያዎች ተፈጻሚ ሲሆኑ እስከማየት ይደርሳል፡፡ አንዱ ጋ የሚፈቀደው ሌላው ጋ ክልክል ሊሆን ይችላል፡፡ አንዱ ጋ የሚያስቀጣው ድርጊት ሌላው ጋ ሊያስመሰግን ይችላል፡፡ ሌላም ብዙ! እናም ጥያቄዬ መልስ ይሻልና እጠይቃለሁ፡፡ እውነት ወዴት እየሄድን ነው?
እውነት እላችኋለሁ ነገራችን ሁሉ የተጠና እና የምር የታሰበበት አይመስልም፡፡ ስለሆነም ያለንበትን ጎዳና አላምነውም፡፡ የሚተገበሩትን ስልቶች አልመካባቸውም፡፡ ይህንን የሚያስረግጡ በርካታ አስረጂዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ጥቂት ብቻ ብናስተውል ብዙ ነገሮችን ልብ እንላለን፡፡ ብዙ ልክ ያልሆኑ ነገሮችን!
አንድ ተጓዥ ያሰበበት ለመድረስ ወደዚያ ሊያደርሰው የሚችለውን ትክክለኛ ጎዳና መምረጥ አለበት፡፡ በመረጠበት ጎዳናም በጽናትና በትጋት መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡ ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት ግን ጎዳናው እንደሚያደርሰው ፍጹም እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡ አለዚያ  እንኳንስ ለቀናት ለዘመናት ቢኳትንም ካሰበበት አይደርስም፡፡ መድረስን ይመኛል እንጂ አይጨብጠውም፡፡ ይህ የሚያስማማን ይመስለኛል፡፡ እናም እዚህ ላይ ቆመን ጥቂት ነጥቦችን እናንሳ፡፡
አንድ፦ እየሄድንበት ያለው ጎዳና ተገቢውና ትክክለኛው ነው? ትውልድና ሀገር የሚጓዙበት የመሆኑን ያህል ተገቢው ጥናት ተደርጎበታል? ተደርጎበታል ካልን ውጤቱ ምን ይመስላል? ጥያቄው በቅጡ ሊመለስ ይገባል፡፡ እርግጥ ነው ትክክለኛው እንደሆነ ጎዳናውን የመረጡት “የጉዞው መሪዎች” ደጋግመው ነግረውናል፤ እየነገሩንም ነው፡፡ ግን ደግሞ እነሱ ትክክል ነው ከማለት ውጪ ሌላ ሊሉን ይችላሉ? አይመስለኝም፡፡ ድክመታችንን እና ስህተታችንን ማመን ተራራን የመሸከም ያህል ያስፈራናል፡፡
ብዙዎች ራሳቸው የመረጡትን ነገር አያሄሱም፡፡ ራሳቸውን ቢያሄሱ የሚጠፉ ይመስላቸዋል፡፡ ሂስን የሚፈራ አያድግም! ደግሞም ጎዳናውም ሆነ አጓጓዙ ሌሎችን ስላደረሰ ብቻ እኛንም ያደርሰናል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእኛ ማንነት (ማንነት በርካታ ጉዳዮችን ይይዛል፡፡) ከሌሎች ይለያል፡፡ ከማንነታችን የሚሰርጸው አቅማችንም ከሌሎች አቅም ጋር አንድ አይደለም፡፡
ሁለት፦ የጉዞ ስልቶቻችንስ ምን ያህል ትክክል ናቸው? ሌላው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብዙም ሳንርቅ አንዳንድ ነገሮችን ለማስታወስ እንሞክር፡፡ እንደ ጦር ግንባር ተልዕኮ የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥቶአቸውና የጊዜ ወሰን ተበጅቶላቸው የተቀመጡ እቅዶችንና ተግባራትን እንዲሁም በዘመቻ የተቃኘ አፈጻጸማቸውን እናስታውስ፡፡ ውጤታቸው ምን ነበር? ቢያንስ ከፊሎቹ ውጤታማ እንዳልነበሩ እናውቃለን፡፡ ትክክል ከነበሩ ለምን ውጤታማ አልሆኑም?
እርግጥ ነው እቅድ ሁሉ መቶ በመቶ ውጤታማ እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ ያ ማለት ግን ግማሽ በግማሽ ውጤታማ አይሆንም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ሊከሰት የሚችለው አዋጪነቱ ያልተጠና እና በአስተማማኝ መልኩ ያልተፈተሸ እቅድ ከተተገበረ ብቻ ነው፡፡ እናም እላለሁ፤ አሁን እየተገበርናቸው ያሉትስ ስልቶች ካሰብንበት የሚያደርሱን ናቸው?
ሦስት፦ በጎዳናው ተጉዘን ያሰብንበት ለመድረስ ጉዞው የሚጠይቀው ጽናትና ትጋት አለን ወይ? ማንም ስለፈለገ ብቻ ያሰበበት አይደርስም፡፡ እርግጥ ነው መፈለግ አንዱና ቀዳሚው ግብአት ነው፡፡ ሆኖም መፈለግ ወደ ድርጊት እስካላደገ ድረስ አእምሮ ውስጥ ሲላወስ የሚኖር ምኞት ነው፡፡  ድርጊት ደግሞ ጽናትና ትጋትን ይጠይቃል፡፡
ጥያቄው ማቆሚያ ያለው አይመስልም፡፡ የጉዞው ተዋናዮችስ መድረሻው የሚገዳቸው ናቸው? ጉዞውን ለማሳካትስ ብቃቱና ፍላጎቱ አላቸው? ኃላፊነትስ ይሰማቸዋል? እነዚህን መፈተሽ፣ ፈትሾም እውነቱን መመስከር ይገባል፡፡ የዛሬው መከራችን ነገም እንደማይቀጥል መተማመኛ እንሻለን፡፡ የያዝነው ጎዳና እንደ ሀገር ከተቸነከርንበት  የችግርና የመከራ ማጥ ውስጥ መንጥቆ ያወጣናል ወይንስ ወደባሰ አዘቅት ይከተናል? እርግጡን ማወቅ እንፈልጋለን! እርግጡን ማን ይነግረናል?
ስለያዝነው መንገድ ተገቢ መሆን አለመሆን ብዙዎች ብዙ ቢሉንም ምንም እያሉን አይደለም፡፡ የዚህም ምክንያቱ እየነገሩን ያሉት አካላት ሊነግሩን የሚገቡት ስላልሆኑ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ስለ ጎዳናውና ጉዞዋችን የምንሰማቸው አስተያየቶች ሁለት ፅንፍ የወጡ ናቸው፡፡ ገዢው ፓርቲና ከእሱ ጋር የወገኑት “እንከን የሌለውና ፍጹም ውጤታማ ጎዳና” ላይ እንዳለን ሠርክ ሊሰብኩን፣ ሰብከውም ሊያሳምኑን ይሞክራሉ፡፡ (ልብ በሉ! እስከ አሁን ድረስ በአለም ላይ እንከን የሌለው ጎዳና አልታየም፡፡ እነሱ ግን የእኛ እንከን የለውም ይሉናል፡፡)
በሌላው ጽንፍ የቆሙት የሚሰጡት አስተያየት ደግሞ ከፊተኞቹ ፍፁም ተቃራኒ ነው፡፡ ለእነዚህኞቹ ጎዳናውና ስልቱ ፍጹም ጎጂ ነው፤ አንድም መልካም ጎን የሌለው ስህተትና ጥፋት፡፡ ማጠንጠኛቸውም ይሄ ቢስተካከል ሳይሆን ሙሉውን ቢቀየር የሚል ነው፡፡ አንዳንዴም “እኛ ካልጋገርነው እንዴት ጣፍጦ” ሲሉም ይሰማል፡፡ ሁለቱም አካላት ስላለንበት ጎዳና እርግጡን የሚነግሩን አይደሉም፡፡ አንዱ በፍጹም ፍቅር ሁለተኛው በፍጹም ጥላቻ ውስጥ ወድቀው እኛንም ሊጥሉን የሚሞክሩ ናቸው፡፡ ሦስተኞቹስ?
ወደ ሦስተኞቹ ጣቴን እቀስራለሁ፡፡ ወደ የመስኩ ምሁራን እና ባለሙያዎች፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ሀገራችን ለምሁራንና ለባለሙያዎች ያላት ክብርና የምትሰጠው ጆሮ  የሚያሳፍር ነው፡፡ ከእውቀት ይልቅ ድፍረት ነግሶአል፡፡ ከብቃት ይልቅ ቲፎዞ ነው የሚታፈረው፡፡ ማንም ባልዋለበትና ባልደከመበት መስክ ላይ ያሻውን በድፍረት ሲደሰኩር ቅንጣት ማመንታት አይታይበትም፡፡ በዚህ ትርምስ ውስጥ ምሁራንና ባለሙያዎች ቦታና ሰሚ አጥተዋል፡፡ ይህንን በሚገባ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ወደ እነሱ ጣቴን የምቀስረው ስለያዝነው መንገድ ከእነሱ የተሻለ ሊነግረንና ልናምነው የምንችለው አካል አለ ብዬ ስለማላስብ ነው፡፡
ምናልባትም ከእነሱ አንዱ ይህንን እያነበበ “ይቀልዳል እንዴ? ማን ሰምቶን ነው እኛ የምንናገረው?” በማለት በፌዝና በመገረም ፈገግ ይል ይሆናል፡፡ እኔ ግን እላለሁ፡፡ “ማንም ባይሰማህስ ለምን ይገደሀል?” ደግሞም አምናለሁ፤ የሚጮህ አንደበት እውነትን እስከተናገረ ድረስ አንድ ቀን ይሰማል፡፡ መሰማት ከጀመረ ደግሞ ማቆሚያ ያለውም! በፍጹም፡፡  የምናውቀውን ሁሉ የመግለጽ ሞራላዊ ግዴታ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ከእንጀራችን ባለፈ ለወገናችንና ለሀገራችንም ልንኖርና ልንደክም ይገባል፡፡
እነሆ ስላለንበት ጎዳና ሁለት ተቃራኒ ፅንፍ የሆኑ ሀሳቦች ሲነገሩን ዘመናት ላይመለሱ ነጎዱ፡፡ አንዱ ከፍጹም ፍቅር ሁለተኛውም ከፍጹም ጥላቻ የሚመነጩ በመሆናቸው ሚዛናዊ አይደሉም፡፡ ግባቸውም እንደሰባኪ ሁሉ ተከታዮችን ማፍራት ነው፡፡ ተከታዮችን የሚሻ ስብከትን ሳይሆን ሀቀኛና ገለልተኛ አስተያየትን መስማት እንሻለን፡፡ ጥያቄዎቹ ሊመለሱ ይገባል፡፡ ጎዳናው የት ያደርሰናል? ወዴትስ እየሄድን ነው?! እውነቱን ማወቅ እንፈልጋለን!! መልካም ሰንበት!!

Read 4309 times