Saturday, 15 November 2014 10:33

ኢቢሲ የአልጀዚራን ፕሮግራሞች ማሰራጨቱ የአገሪቱን ገጽታ ይጐዳል ተባለ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

          የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ጣቢያ የአልጀዚራ የስፖርት ቻናሎችን በህገወጥ መንገድ ማሰራጨታቸው የአገሪቱን ገጽታ በእጅጉ እንደሚጐዳ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለፀ፡፡ ባለስልጣኑ ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የዕቅድ ሪፖርት ላይ እንደገለፀው፤ ኢቢሲና የኦሮሚያ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፤ የአልጀዚራ የስፖርት ቻናሎችን በህገወጥ መንገድ ከማሰራጨት እንዲታቀቡ ቁጥጥር ቢደረግም ህገወጥ ስርጭቱ ሊቆም አልቻለም፡፡ በአገሪቱ የውጭ ብሮድካስት ፕሮግራሞችን በክፍያ ለደንበኞች ለማድረስ የአገልግሎት ፍቃድ የወሰደው ድርጅት ከሚያቀርባቸው የዲኤስቲቪ ቻናሎች ውጪ በህገወጥ መንገድ የአልጀዚራ የስፖርት ቻናሎችን የሚቀበሉ ቢኑ ካርዶችና ዲኮደሮች ከውጪ በማስገባት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማሰራጨት ላይ የሚገኙ አካላት እንዳሉም ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
የውጭ ብሮድካስት ፕሮግራሞችን በክፍያ ለደንበኞች የማድረስ አገልግሎት (subscription) ፈቃድ የተሰጠው መልቲ ቾይስ ኢትዮጵያ ለተባለ ድርጅት ሲሆን ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ለደንበኞቹ የሚያቀርባቸው ቻናሎች ከተሰጠው ፈቃድ ጋር የሚጣጣም መሆኑ፣ የሚተላለፉት ፕሮግራሞች ይዘት የህፃናትን ስነልቦናና የወጣቶችን ደህንነት እንደማይጐዱ እንዲሁም የህብረተሰቡን ባህላዊና ሞራላዊ እሴቶች የሚጠብቁና የሚዲያ ህጉን ያከበሩ ስለመሆናቸው ክትትል አለመደረጉም በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡

Read 6799 times